ፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የሚያቀርቡ ሲሆኑ ህዝብ በአዲስ ጉጉት ይወጠራል፡፡
በአዲስ ተስፋ ይሳባል፡፡ አዲሱ ምርጫ ስቦት ነባሩን ገዢ ፓርቲ በአዲስ ስለመተካት ያሰላስላል፡፡ ቃል የተገባለት የተሻለ ነገር
አሁን ያለውን ጥሩ አማራጭ ለመተካት ያነሳሳዋል፡፡ ይሄኔ ነው ማጓጓት የሚቻለው፡፡ ይሄኔ ነው አማራጭ መኖሩ የሚታወቀው፡፡ ጉጉት
የተሻለ ነገር ከመናፈቅ የሚፈጠር ስህበት ነው፡፡
እንዲህ ያለ የሚያጓጓ አማራጭ ባለበት መከፋትን በመጠንሰስ ቂም በቀል
በማስረጽ የሆን ተብሎ ተበደልክ ተገለልክ ስብከት በማስለፈፍ ድጋፍ መፈለግ ይከስማል፡፡ ቁምነገሩ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ
ያን የሚያሳካው መንገድ ደግሞ የተዋጣላት እና በወጉ የተቀመረ ፕሮግራም ይሆናል፡፡
እሚያጓጓ ፕሮግራም ያበጀ ፓርቲ በተበዳይነት ስሜት (ቪክቲም ሜንታሊቲ)
ወይም በቂም በቀል ፖለቲካ የሚጣድበት ምንም ምክንያት ስለማይኖረው አብይ አጀንዳው ሳቢና አስተማማኝ ፕሮግራሙን በስፋት በማስተዋወቅ
ድጋፍና የምርጫ ካርድ መግዛት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡
ይህን መሰሉን በራስ መተማመን እና ልምድ የተላበሰ ፓርቲ ማቋቋም ደግሞ
የበሰሉ ፕሮግራሞችን መንደፍ ሀገራዊ ውርደቶቻችንን የመቀየር እና ሀገራዊ ድሎቻችንን የማስቀጠል በመሆኑ በዋናነት ከተቃውሞ ጋር
ሳይሆን ሀገራዊ መፍትሄዎች እና ሀብት ፈጠር አቅሞች ከማዳበር ጋር ይሰናሰላል፡፡
በመሆኑም ሆድ የማስባስና ተፎካካሪ ፓርቲን የማስጠላት ድውይ ፖለቲካ
ዋናኛ መነሾ አማራጭ አልባ ሆኖ በጥላቻ ፖለቲካ ተመርዞ ፖለቲካውን መቀላቀል ነው፡፡ ይህን መሰሉ ፖለቲካ ለሀገራቸው ሀገራዊ ችግሮች
መፍትሄ ለመፈለግ ሳይሆን በፖለቲካ መድረኩ ላይ ለሚያዩዋቸው ግለሰቦች ያላቸውን ጥላቻ ለመግለጽ በሚገቡ ግለሰቦች የሚፈጸም ነው፡፡
ፕሮግራም የሌለው ቡድን ደግሞ የሚቃወመውን ቡድን ፕሮግራም እያነሳ
ከማላዘን የተሻለ አማራጭ ሊኖረው አይችልም፡፡ ቂም በቀልና ጥላቻ የመዝራት ተልእኮ ይዘው በፖለቲካው መድረክ የሚርመሰመሱ ቡድኖች
አብይ መገለጫም ይሄው ነው፡፡ ማጣጣል ማሳበብ መውቀስ ይህን መሰሉን ወሬ ነጋ ጠባ መደጋገም እና ይሄው የፖለቲካ ፕሮግራም ሆኖ
ኢህአዴግ ባያጭበረብር ኖሮ በዝረራ ይሸነፍ ነበር እያሉ መጎረር ነው አጀንዳቸው፡፡
በመሆኑም የበሳል ፖለቲካ አንዱ መገለጫ ለሀገራዊ ችግሮች ያበጃቸውን
መፍትሄዎችና ለሀገራዊ ሀብቶች መፍጠርያ ያበጃቸውን አማራጮች በማስተዋወቅ ህዝብ በፕሮግራሞቻቸው በመተማመን በሚልቀው አማራጫቸው
ጉጉት አነሳሽነት እንዲመርጣቸው ማስቻል ነው፡፡
ይህን መሰሉን ባህሪ በማዳበር እንዲህ አይነቱን ባህሪ የሚያላብስ ፕሮገራም
በመቅረጽ ኅዝብን በጉጉት የሚስቡ ፓርቲዎች ለማግኘት መብቃት ይገባል፡፡ ይቻላልም፡፡ ቁምነገሩ በሀገራዊ ችግሮቻቸን መፍትሄ እና
ሀብት ፈጠራ ዙርያ ለመስራት መሰባሰብ መቻል ነው፡፡