=======================
በዚህ ትንታኔዬ የኔ የሚባሉትንም ከመተቸት ወደሁዋላ አላልኩም። እውነታውን በጋራ መጋፈጥና በሀቀኝነት ችግሩን ፈተን ሁላችንም በጥረታችን ልክ አሸንፈን እና እኩል ተጠቃሚ ሆነን የምንኖርበት አገር ካልፈጠርን መዘዙ አደገኛ ነው ብዬ ስለማምን የሚመስለኝን ሁሉ ድፍረትና ሚዛናዊነትን አጣጥሜ ላቀርበው ሞክሬያለሁ። መልካም ንባብ።
ስጀምር በኔ አተያይ እንደ ብሄራችን የታሪክ ትረካችን ይለያያል። ታሪኩን እምንዘክርበት ስሜትና ወግም በዚያው ልክ የተለያየ ነው። አንዱን ታሪካችንን ከደማችን እየቀዳን እያነበብን ብዙ አይነት አድርገን ግራ እንጋባለን፣ ግራ እናጋባለን።
ጥቅል ድምዳሜዬን የሚጎሉትን ጉዳዩች ሞልታችሁ እንደምታነቡ በማመን ለኔ እንደሚታየኝ ከሶስቱ ብሄሮች፦ ኦሮሞ፣ አማራና ትግሬ የሚወለዱ የታሪክ ነጋሪያን እና አመስጣሪዎች እንዴት ታሪካችንን እንደሚያነቡት ላስረዳ።
===================
1 የአማራው ታሪክ ተንታኝ፦
የአማራው ታሪክ ተንታኝ በአመዛኙ የኢትዮዽያን ታሪክ የኔ ብሎ የሚያስብ፥ በሀገሪቱ በተካሄዱ መሰረታዊና ወሳኝ ጉዳዩች ላይ የራሱ ብሄር የተለየ ግዙፍ ሚና አለው ብሎ የሚያስብ፥ በመሆኑም በተነጻጻሪ አማራ ስልጡን ብሄር ነው ብሎ የሚያምን እና ለዚህ ተወልጄበታለሁ ለሚለው ብሄሩ አገር ግንባታ ታሪካዊ ሪከርድ ተጋድሎ ለመፈጸም የቆረጠ፥ ማን እንደኛ እያለ ማስረዳት እሚቃጣው፥ በዚህም የተነሳ ራሱን የተሻለና የዚሁ የተሻለው ታሪክ አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ የሚያስብ ሆኖ የቆየ ነው።
አማራው እኮ ማለት የሚቀናው በቀጥታም አዙሮም የብሄሩን ታላቅነት ለመስበክ ወደሁዋላ የማይል ነው። የዚህን አገር ታሪክ የማንነቱ መገለጫና የአማራነቱ ክፋይ አድርጎ ስለሚያይ ብሄራዊ ማንነቱን ከታሪኩ ለይቶ ማየት የተሳነው ሊባል ይችላል። ይሄን ታሪክ ሊጠይቅ የሞከረውን ሁሉ ሀገራዊ ፍቅር የሌለው፣ ገንጣይ አስገንጣይ እያለ የሚፈርጅ ነው። የታሪክ አሳሳሉ ደግሞ አድናቂ እና አወዳሽ ከመሆን አይዘልም።
የዚህ የአማራ ታሪክ ተራኪ መሰረታዊ ስህተቶች ሁለት እንደሆኑ እረዳለሁ። አንደኛው የሀገሪቱን ታሪክ የአማራ ታሪክ ብሎ መውሰዱና ሁለተኛ ደግሞ የአማራን ማንነት እና ትልቅነት ከዚህ ታሪክ መወድስ ጋር አሰናስሎ የሰፋው መሆኑ ነው።
አማራው ከዚህም ታሪክ ጋር ይሁን አይሁን ክቡርነቱ እንዲያው ከተፈጥሮ እንደማንኛውም ህዝብ የሚቀዳ መሆኑን አይረዳም። በመሆኑም ለዚህ የታሪክ መምህር ታሪኩን መንካት አማራን መንካት፤ ይህን የሱን የታሪክ ትርክት አለመቀበል የአማራን የበላይነት እና የተሻሌነት አለመቀበል አድርጎ ይወሰደዋል። በቀጥታ ማንነቴ ተነካ ግን አይለንም። ሀገሬን ኢትዮዽያን የነካ እምዬ ኢትዮዽያን የደፈረ በሚል መፈክር ይህን የታሪክ ትርክት የተቹትን ያሳድዳል። ያኔም አሁንም።
በመሆኑም በኔ እምነት ሀገራዊ ታሪክ ሀገራዊ አንድነት እና ብሄራዊ ማንነቱ የተምታቱበት በመሆኑ የሌላውን የታሪክ ትርክት ለመስማት እንኳ እድል የማይሰጥ ይመስላል።