ዘርይሁን ካሳ
የሳውዲው ልኡል በአረብ ህዝብ ጥቅም ላይ ያነጣጠሩ ለራሳቸው የረባ ጥቅም የማይገነቡ ይሆነኝ ብለው የአረቡን አለም ለመጉዳት የሚያሴሩ ኢትዮዽያዊ ጣቶች እንዳሉ ነግረውናል:: ልኡሉ እሳቸው ደጃፍ በአረቡ ህዝብ ስም የሚቦካው ለአረቡ አለም ህዝብ ፋይዳ የሌለው ያረጀ ጎረቤትን በማደህየት የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚጥር ፖለቲካዊ አተያይ የማይገባን መስሎአቸው
ከሆነ ስተዋል::
ኢትዮዽያንና የአፍሪካን ቀንድ የሚያምሰው የነማን ረጅም እጅ እንደሆነ እንረዳለን:: ይህ ረጅም እጅ መደፈቅ ያለበት ያረጀ የግብጽ ፖለቲከኞች ቁማር ነው:: ሁሌም የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ጎረቤት በማተራመስና በማዳከም የሚያምን ደሀ አመለካከት:: እንዲህ ያለው አመለካከት ነው አስቦና ተጠቦ ሞቶ ከሰማንያ በመቶ በላዩን ዉሀ የምታበረክተውን አገር አንዳች ጠብታ ውሀ የማትጠቀምበትን ስምምነት ያሰረው::
ይሄ ያረጀው የግብጽ ፖለቲከኞች ቁማር በውጤታማ ዲፕሎማሲ ሲረታና ውሀው ፍትሀዊ ክፍፍል ሊደረግበት ጫፍ ሲደርስ የማይቀረውን ለማስቀረት ባለበሌለ ሀይሉ እየተፍጨረጨረ ነው:: የግብጽ ህዝብ ኢትዮዽያ እየተራበች እኛ እንብላ የሚል ኢፍትሀዊ አቋም አለው የሚል እምነት የለኝም::
የሳውዲው ልኡል ሲሆን ሲሆን ወደ በራችን ያመጡትን ጣት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ጥሩ ነበር:: ጣታቸውን በወሳኝ ብሄራዊ ጉዳያችን ውስጥ ሰንቅረው ሲያበቁ እንዲህ ለነተበ የማጋጨትና የማተራመስ አጀንዳ የተጠቀሙት መሆኑ ሀሳባቸውን ያኮስሰዋል ያረክሰዋልም::
በርግጥ ራሳችንን እንዴት መከላከልና ጥቅማችንን እንዴት ማስከበር እንዳለብን የምናውቅ በመሆኑ የልኡሉ አይነት የተረገሙ አስተያየቶች አያሰጉንም:: ያም ሆኖ በቀጠናችን ያረጁ የፖለቲካ ጓዳዎች የሚቦካውን እና እንደሚቦካ የምንጠረጥረውን የመከላከያ ባለስልጣኑ ስላበሰሩን እናመሰግናቸዋለን:: የሱዳኑ የዜና ምንጭ በትክክል እንደጠቆመው ይሄ ንግግር ከጀርባው ሌላ ጉዳይ እንዳለው ተረድተናልም::
በቅርቡ ሙስሊሙ ያነሳውን የውሰጥ ጉዳይ አስታከው ሀገር ወዳዱን ሙስሊም ይሸውዱት ይመስል ከጥያቄው ጀርባ ምን ሊሰሩ ይተጉ እንደነበር ተደርሶበታል:: አሁን ልኡሉ እንደነገሩን አጀንዳው ኢትዮዽያ ስታድግ ያመናል የኢትዮዽያ ማደግ ግብጽን ይጎዳል በሚል የሚቀነቀን እና በፍትሀዊው አገር ወዳድ ሙስሊም የውስጥ ጉዳይ በመግባት ኢትዮዽያ የማያባራ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ በመመኘት እየሰሩት እንደሆነ እናውቃለን::
ያ መረብ ነው የተበጠሰው መረቡ ከኢጋድ ቀጠናዊ መዋቅር ጀምሮ በሌሎች አካላት እይታ ውስጥ መውደቁን ሲያውቁ ከዋሽንግተን እስከ ካይሮ ከካይሮ እስከ ሪያድ ያሉ የዚሁ ሴራ መረቦች ሁነኛ መልካቸውን እና አጀንዳቸውን ፍንትው አድርገው ይነግሩን ጀምረዋል:: የግብጻዊው ሰባኪ የጂሀድ አዋጅ በሀገር ወዳዱ ሙስሊም ስም ነው ፊልም የተሰራበት:: ኢትዮዽያዊው ጁሀርም ሀይማኖት ተንተርሶ የመጣው ሴራ አላማ የኢትዮዽያን መንግሰታዊ መዋቅሮች ማውደም እንደነበር በተባ ምላሱ ነግሮናል:: የሳውዲው ልኡል በዚሁ ማእቀፍ የሚታይ ነው::
ልኡሉ እቺ አገር የማይጠቅም ግድብ እየሰራች ያለችው ይሆነኝ ብላ የሱዳንን እና የግብጽን ጥቅም ለመጉዳት ነው የሚል ተረታቸውን ነው የነገሩን:: ልኡል ሆይ 6000 ሜጋ ዋት ሀይል ለርስዎ ፋይዳ ቢስ ከሆነ ከጪሳሙ ነዳጅ ኤሌክትሪክ እንደሚያገኙ በመተማመኖ ሊሆን ይችላል:: ለኛ 6000 ሜጋ ዋት ማለት እስካሁን የምናመርተውን ኤሌክትሪክ አቅም በሶስት እጥፍ የሚያሳድገው መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን:: የማይጠቅም ግድብ የሚሆነው በርሶ የተቃወሰ ምዘና ካልሆነ በቀር ይህን የመሰለ ጥቅም የለም:: የማይጠቅመውስ የርሶ የርጎ ዝንብነት የርሶ ጣት የማይመለከታትን መጠንቆሏ ነው:: ሌላው የማብራሪያዎ ዉበት ግድቡ ከፈረሰ ካርቱምን ይጠራርጋታል አስዋን ግድብንም ያሰጋዋል የሚለው ቅኝትዎ ነው::
ልኡል ሆይ አስዋን ቢፈርስስ ካይሮ አትጥለቀለቅም እንዴ? ከሆነ ደግሞ መሰራት አልነበረበትም ማለት ነው እንደርስዎ ገለጻ:: የሆነ ሆኖ ሞት ተፈርቶ መተኛት ስለማይቀር ተሰራ:: የኛ ሲሆን ካርቱምን ስለሚያጥለቀልቅ አይሰራም የግብጾቹ ሲሆን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ነው አደል?! ልኡልነትዎ አይዞት ቢፈርስ እንኳ ከአስዋን ቀድሞ አይፈርስም:: ከፈረሰም አስዋን ከሚያስከትለው የበለጠም የተለየም ጉዳት አያደርስም:: እናም በርስዎም እርባናቢስ መከራከሪያ ቢሆን ግድባችን ፍትሀዊ ነው::
ልኡል ሆይ ሲፈርስ የሚከሰተው ያሳስቦታል? ባለመገንባቱ ኢትዮዽያና ቀጠናው የሚያጡት 6000 ሜጋ ዋት ሀይል አያስጨንቆትም? ይልቅ ልኡልነትዎ የሚሻለው ግድቡ እንዳይፈርስ የምእራቡን አለም ባንክ ያጣበበውን ገንዘባችሁን ብታበድሩን ኖሮ ግድቡን ይበልጥ ጠንካራ አድርገን እንገነባው ነበረ:: ለነገሩ ከናንተ የጀርባ ውጋትነትም ጋር ቢሆን አስተማማኝ እና ጠንካራ ግድብ ነው እየሰራን ያለነው:: ሲፈርስ ካርቱም ስለምትጠፋ ብቻ ሳይሆን ከግድቡ የሚገኘውን ሀይል ዘላቂ ማድረግ ስለምንፈልግ:: ከደቃቃው አቅማችን የተሰበሰበውን ሀብት ማባከን ስለማንፈልግ እንዲያውም በመገንባቱ የሚጎዱ ያስመሱሏቸውን ግብጽንና ሱዳንን ስለሚጠቅምም ጭምር::
ልኡልሆይ አስዋንን እና የኛን ግድብ ምን ይለየዋል? የኛም ግድብ ለመብራት ሀይልና ለአሳ ምርት ቢያገለግል ነው ልክ አስዋን ለግብጾቹ እንደሚያደርገው:: ወይስ ኢትዮዽያ ውስጥ ናይል ሲገደብ ለአሸባሪ ፈንጂና ቦንብ የምናመርትበት አስመሰሉት:: የኔ ጌታ እኛም ጋ ዉሀ ሲገደብ ሀይል አሳ እና በተወሰነ ደረጃ መስኖ ሊሆን ቢችል ነው:: በባህሪው የአባይ አቀማመጥ ኢትዮዽያ ውስጥ ለመስኖ የመዋል እድሉ ጠባብ ቢሆንም::
በርግጥ ጉዳዩን ለማብራራት ቀናነት ብቻ ሳይሆን እውቀትም ይፈልጋል:: ቀናነቱ እንደጎደሎት አስተያየትዎ ያመለክታል የእውቀትም ችግር ያለብዎት መሆኑን ግን የሚያቀርቡት መከራከሪያ ደካማነት ያመለክታል:: ኢትዮዽያውያን ትሁት ነን ከተነካን ግን ያውቁታል:: እርሶ የማንበብ እድሉ ካለነበረዎት ሌሎችን ይጠይቁ:: ዛሬም ያ አቅማችን አብሮን አለ እንዲያውም ዘምኖና ተሻሽሎ ጭምር:: ሁሌም ለሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ቅድሚያ የምንሰጥ ቢሆንም::
ለነገሩ አለቆችዎ ልኡል አፋቸውን አድጧቸው ነው ብለዋል:: የሆነ ሆኖ እሚከካ እሚቦካውን መጠርጠራችን ከዚያም አልፎ እንዲህ በአደባባይ ቀረርቶ ማረጋገጣችን ደስ አስኝቶናል:: የምር እንኳን አፎን አዳጦት አጀንዳ ፈጥሮልናልና:: ሁሌም ስለአረብ ሲነሳ ስለ ኢትዮዽያ ሙስሊም የተነሳ የሚመስላቸው ደምና ሀገርን ከሀይማኖታዊ መመሳሰል ጋር የሚያስተሳስሩ ደካሞች አሉ:: አዎን ሙስሊሞች ኢትዮዽያ ውስጥ አሉ ግን ኢትዮዽያዊ ሙስሊሞች ናቸው:: ሳዉዲአረብያዊ ወይም ግብጻዊ አደሉም:: ሀይማኖታቸውን በሀገራቸው ይኖሩታል ሀገራቸውን ለሀይማኖታቸውም ጭምር ሲሉ ይጠብቁታል::
ለአብነት የቅርቡን ግዜ ሰላማዊውን የሙስሊሙን የውስጥ ጉዳይ እኚሁ የውጭ ሀይሎች ለአሸባሪነት አጀንዳቸው እንዴት ይፈትሉት እንደነበር እናስታውሳለን:: በአንድ በኩል ለሙስሊሙ ከራሱ በላይ ያውቅለት ይመስል መንግስት በጉዳይህ እየገባ እየፈተፈተ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ ይነዛሉ:: በሌላ ገጽታው ደግሞ ከሀገር ወዳዱ ሙስሊም ጀርባ ከቅጥረኞቻቸው ጋር በመተባበር አሸባሪ ድርጊታቸውን ለመፈጸም ሳያሰልሱ ይሰራሉ:: ያም ሆኖ የከፋ ችግር ሳይፈጠር ሁኔታው መልክ እየያዘ ነው:: የሚቀሩትም ነገሮች በሂደት ኢትዮዽያዊው ሙስሊም በራሱ መንገድ የሚፈታቸው ይሆናሉ::
ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሰላማዊ ጥያቄውን በራሱ መንገድ መፍታቱን አያቆምም:: ያ አንድ ነገር ሆኖ ሲያበቃ በሌላም በኩል ልኡል ሆይ እርስዎን እና ግብጻዊውን ሼክ የመሳሰሉ ሰባኪዎችንም ከመሰረታቸው መንጥሮ ከቅጥሩ ያወጣል:: ይቅርታ ያድርጉልን ጌታዬ ኢትዮዽያዊው ሙስሊም ዜግኑትን ወዶ የሚኖር እንጂ የተጋተው አደለም:: አገሩን በፖሊስ ያስጠብቃል የመስጊዱን ሰላም በፖሊስ ያስጠብቃል እንጂ ማንነቱ ተጠርጥሮ ፖሊስ በገባበትና በወጣበት የሚጠብቀውም አይደለም::
ልኡሉና መሰሎቻቸው ኢትዮዽያዊው ሙስሊም አባይን ብርና እውቀቱን ሰውቶ እየገነባው እንደሆነና በቀጣይም በማያሰልስ ትጋቱ እንደሚገነባው የገባቸው አልመሰለኝም:: ይሄ ኢትዮዽያዊ ሙስሊም ሀገራዊ ፍቅሩ ደሙ ጋር የተሰናሰለ መሆኑን አያውቁትም:: ሀይማኖታዊ ተመሳስሎው እና አምልኮቱን በየዋህነት ለአሸባሪና አውዳሚ እቅዳቸው የሚያውለው ይመስላቸዋል::
አይ አለማወቅ ኢትዮዽያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይቀይር ቢያውቁ በበጃቸው ነበር!!! እነዚህ ተከታታይ ድርጊቶች በእምነቱ ቅጥር ስር ሊሰሩ መሞከራቸውን የተረዳው ሙስሊም ኢትዮዽያዊ ነብር ሆኗል:: አይነካም አይደፈርም:: ብሄራዊ ጥቅሙን አሳልፎ አይሰጥም:: በተለይ በመስገጃና በአምልኮ ቦታው ሰላሙን የሚነሳው የውጭ ሀይል አይፈነጭበትም የቀረውን በተግባር ትማራላችሁ::
መጋረጃው ተቀደደ መልካችሁንም አወቅነው ግብጻዊው ሼክም ሳውዲው ልኡልም ሌሎች ግብጻዊ የጥፋት ሰረገላዎችም ቀላሉን አማራጭ መተባበርን መወያየትን ምረጡ:: ለነገሩ በመረጣችሁት መንገድም ቢሆን ተጋግጣችሁ ጭምር አዋጩ መተባበር መሆኑን ትማራላችሁ::
ይቆየን!!!