አንድነትም
መገንጠልም መመዘን ያለበት ከሚያስገኙት ጥቅምና ጉዳት አንጻር ነው እንጂ አንድነትንም በመናፈቅ መገንጠልንም በመፍራት መሆን የለበትም፡፡
ከጥቅምና ጉዳት አንጻር የተመዘነ እንደሆነ ነው ጉዳዩ በአግባቡ የሚፈታበት አማራጭ የሚነጥረውና ሰከን ባለ መልኩ ሊመራ የሚችለው፡፡
አንድነት
በማንኛውም ሚዛን ከመገንጠል የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ ባዶ አንድነት ግን ጸጋ አደለም፡፡ አንድነትን ለላቀ ተጠቃሚነት ማዋል መቻል
ይገባል፡፡ ያን ማድረግ የሚችል አመራርና የፖለቲካ ተዋንያን መፍጠር ይጠይቃል፡፡ ይሄ አለመሆኑ ግን ወዲያውና የግድ መገንጠልን
እንድንመኝ ይዳርገናል ማለት አደለም፡፡ ጠንቅ የሆነውን ስርዓት መታገል ሲገባ ደርሶ ካልተገነጠልን ማለት ነውረኝነት ነው፡፡
ህዝቡን
የጎዳው አንድነቱ አደለም፡፡ ህዝቡ የተጎዳው ሀብት መፍጠር የሚችልና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል መፍጠር ባልቻለ አመራር መኖር አለመኖሩ
ሊሆን ይችላል፡፡ ስህተቱ የሚጀምረው ችግሩ አንድነት ነው ወይስ ለህዝብ የሚመጥን አመራር መፍጠር ያልቻለ ስርአት መኖር አለመኖሩ
ነው የሚለው ጋር ነው፡፡
አንድነት
ይበጀናል አንድነት የላቀው አማራጭ ነው መገንጠል ግን አያጠፋንም፡፡ አንድነትን የሞትና የሽረት ጉዳይ ልናደርገው የማይገባንን ያክል መገንጠልን የበረከት መዝነብ አድርገን
ልናየው አንችልም፡፡ ስላልፈለግን አደለም ስላልሆነ ነው፡፡ አንድነትም ታምር አደለም፡፡ መገንጠልም መርገምት አደለም፡፡ ችግሩ የምንሰማውን
ማስፈራርያና የመበደል መንፍስ እንደወረደ የምንገዛ ከመሆኑ ነው፡፡
አንድነቱን
የጠበቀ ደሀ አገር የማይረባንን ያክል በረባ ባልረባው ካልተገነጠልኩ የሚልና በመገንጠሉ እያነሰ የሚሄድ አገር የሚረባን አይሆንም፡፡
ለመገንጠልም የሚራኮቱት በውድም በግድም አንድነቱን ለማስቀጠል የሚረባረቡቱ ቡድኖች ከንቱዎች የሚሆኑት ከህዝብ ጥቅም የሚመነጭ የትግል
ግብ የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡
እንገንጠል
የሚሉት ሁሉ የሚጋሩት አንድ ተልዕኮ ይህን አገር ለማመስ የማይተኙ ጠላቶችን አጀንዳ ያንጠለጠሉ መሆኑ ነው፡፡ ለመገንጠል ሎሌዎች
እንንገራቸው አንድም እናንተ ስለዘመራችሁ ዘራፍ ብሎ ልገንጠል የሚል የለም ቢኖርም አንርበደበድም በማንኛውም ህጋዊ አማራጭ አንድነት
በሁሉም ሚዛን ከመገንጠል እንደሚሻል በማስረዳት እንፋለማቸዋለን፡፡ መገንጠል መብት በመሆኑ ህገመንገስቱንና አለማቀፋዊ ድንጋጌዎችን
ጠብቆ ቢፈጸም አያከስመንም፡፡ የትኛውም ብሄር አገር ሆኖ መኖር ይችላል፡፡ ያንሳል ይቀጭጫል እንጂ፡፡
በአንድነቱ
የምናምነው ዜጎች በህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት አምነን ስናበቃ መገንጠል የወረደው አማራጭ እንደሆነ እንሞግታለን፡፡
ችግሩም አብሮነት ሳይሆን ብልሹ አስተዳደር ነው፡፡ ብልሹ ስርዓት ነው፡፡ መታረምም ያለበት ያ ነው፡፡ እኮ ለምን ያልበላንን ታካላችሁ
እኮ ለምን ያላመመንን ታክማላችሁ ብለን እንጠይቃለን፡፡
የስርዓት
ችግር በስርዓት ይፈታል፡፡ የብሄር ጉዳይ ጋር የሚያያዝ የአመለካከት ችግርም አስፈላጊ በሆኑ ተከታታይ ስራዎች ይፈታል፡፡ አመለካከቱም
ሁሉም ብሄሮች የሚጋሩት ችግር እንጂ ለተወሰኑ አካላት የሚተው አደለም፡፡
የሆነ
ሆኖ መገንጠልን በመፍራት አደለም ይሄን ተረክ የማደርገው፡፡ ይልቅም አንድነትን በተሻለ አማራጭነቱ በመውሰድ ነው፡፡ መገንጠልን
ከማይ ብሞት እመርጣለሁ አልልም፡፡ ጥያቄው የህዝብ ከሆነና ህጋዊ አግባብ ተከትሎ የሚገለጽ እስከሆነ አንድነቱን በአማራጭነት አቅርቦ
በመሞገት ለማሸነፍ መሞከር ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ሕገመንግስቱ የሚጠይቀውን ግዴታ አሟልቶ አለማቀፋዊ ድንጋጌዎችን ተከትሎ መለየት የመረጠ
ሕዝብ ግን ምርጫው ሊከበርለት ይገባል፡፡
ይሄ
በመሆኑ አንጠፋም፡፡ ይሄ ሲሆን የተገነጠለው ብሄር የሚያጣውን ያህል ሌላውም ያጣል፡፡ የተለያዩ ክልሎች የሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊና
ፖለቲካዊ ፋይዳ የተለያየ ቢሆንም አንዱ የሚያጣውን ያክል ሌላውም ያጣል፡፡ የሚጣጣሉ ጥቅሞች ይኖራሉ፡፡ ሆነም ቀረም ግን መጠፋፋት
አይሹም፡፡ አይገባምም፡፡
ከህዝብ
ብዛትና ከሚኖራቸው ስፋት አንጻር ኦሮምያና አማራ ግዙፍ ቢሆኑም እንደሚያንሱ ከሚያውቋቸው ክልሎች አብሮነት የሚያተርፉት ግዙፍ ትርፍ
አለ፡፡ ቢለያዩም ግን ሁሉም በሚያንስበት አንሶ ያለውን የላቀ ፋይዳ ይዞ ይቀጥላል፡፡
አንዱ
ሲገነጠል የሚለማና ብሄሮች ላይ ይደርሳል የሚለው ግፍ የሚቆም የሚመስለው ሌላው ደግሞ አንድ የሆነ ብሄር መገንጠሉ ሞት እኮ ነው
የሚል መርዶ ነጋሪ ካምፕ ነው፡፡ እንገንጠል የሚሉ ቡድኖች በመኖራቸው መደንገጥ የለብንም፡፡ በዚያ ፍርሀትም በመነዳት ወሳኝ አገራዊ
ጉዳዮችን ለመወሰን መንደርደር የለብንም፡፡
አንድነት
ወይንም ሞት አደለም አማራጩ፡፡ በአንድነታችን የምናምነው ዜጎች ተግተን የአንድነቱን አዋጭነት በመስበክ ጠባቦችንም ለጠባቦች ግብአት
የሚሆኑ ትምክህተኞችን እንታገላለን፡፡ የተሳካ ትግል እስካካሄድን የመገንጠል ደቀመዛሙርት መዳከማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ
ሲያበቃ ህዝብ እንደ ህዝብ አምኖበት ህጉን ተከትሎ መገንጠል ከመረጠ ይህን አይነቱን ህዝብ በሰላም መሸኘት ስልጡንነት ነው፡፡
ሀገራችን
ለዘላለም ትኑር አንድነታችንም ይጽና ብንነጣጠልም ግን እናንሳለን ተጽእኖ የመፍጠር አቅማችን ይኮሰምናል እንጂ እንኖራለን፡፡ ማንም
በማንም ጫንቃ አይኖርምና፡፡