Tuesday, September 3, 2013

ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል- ክፍል ሁለት




ክፍል አንድ ካነሳናቸው ጉዳዩች የሚለጥቁ ራስን ማስተዳደር እንደ መለያያ ስትራቴጂ 1983 ሀገራችን የሚሉና ሌሎች ጉዳዩችን የሚዳስሰው የጹሁፉን ሁለተኛ ክፍል እነሆ

መብት እንደ ጥርጣሬ መፍጠርያ

አንዳንዶች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተከበረው ይሆነኝ ተብሎ ህዝቦችን ለማንኳሰስና በመሀላቸው ጥርጣሬ ለመፍጠር ነው የሚል ክስ ያቀርባሉ፡፡ አለመተማመኑን ኢህአዴግ የሚፈልገው ወጥና ጠንካራ ተቃውሞ እንዳይገጥመው ነው በሚል ክሱን ያጠናክራሉ፡፡ ይህ ደግሞ እድሜውን ለማራዘም ያገለግለዋል ብለው ያምናሉ፡፡


አንደኛ በተፈጥሮአዊ ባህሪያቸው እነዚህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዴት ነው አለመተማመን የሚፈጥሩት ብሎ መጠየቅን ያሻል፡፡ በየክልሉ ያሉ የተለያዩ ብሔሮች ሰሜኖች እየመሩን የሚኖሩት እኛ ራሳችንን ማስተዳደር ተስኖን ነው ወይ በሚል ቁጭት የሚንገፈገፉበትን ጉዳይ ነው የመለስው፡፡ በርግጥም ትክክል ናችሁ አዎ ራሳችሁን ማስተዳደር ትችላላችሁ ሰሜኖቹም የማስተዳደር ስራውን ለናንተ እንዲያስረክቡ ህገመንግስቱ በሚጠይቀው መሰረት ተደርጓል ነው የሚለው፡፡ ሰሜኖቹም የማስተዳደር ተፈጥሯዊ አቅምና መብት አላቸው አካባቢያቸውን በዚያው መሰረት ያስተዳድራሉ የሚል ፍትሀዊ ድንጋጌ ነው፡፡


ይሄ በርግጥም የመብቶችን በተሟላ መንገድ መከበር ይገልጻል እንጂ በምን ሚዛን ነው ጥርጣሬ በህዝቦች መካከል የሚያነግሰው፡፡ በመላው ሀገሪቱ ፍትሀዊ ነው ተብሎ ሊወስድ ቢችል እንጂ በምንም ሚዛን መጠላላት እና ጥርጣሬ የሚከስት ሆና አላገኘውም፡፡ በባህሪው ያን የማድረግ አቅም የለውም፡፡


ይልቅ ለአካባቢው ማህበረስብ የማስተዳደር ሀላፊነቱ ሲመለስ ከዚያ ቀድሞ በነበረው ግዜ በአመራር ቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች የመሪነቱን ቦታ ሲያጡ አብሮ የሚደርቅ እና የምረዳው የሚያጡት ጥቅም ይኖር ይሆናል፡፡ ያ በቤተሰብ እና በግለሰቦች አንጻር ሲመዘን ጉዳት እንዳለሁ እረዳለሁ፡፡ ግን ድንጋጌው ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር እና ነጻነት ከሚያጎናጽፋቸው መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች አኳያ ሲመዘን እዚህ ግባ የሚባል ጉዳይ አደለም፡፡ የለውጡም አላማ ይህን የመሰሉ ግለሰቦች ጥቅም ማሳጣት ሳይሆን ራሱን የመምራት ተፈጥሮአዊ ብቃት ያለውን ህዝብና ዜጋ መብት ማክብርና ማስከበር ነው፡፡


በዚህ ሂደት አማራው የተጎዳ በማስመሰል ለማቅረብ የሚሞከርበት አዝማሚያ ሌላው ነው፡፡ በጋሞ ጎፋ አርባምንጭ ተወልዶ እንዳደገ አማራ የሆነውን አውቀዋለሁ፡፡ በአመዛኙ ከሰሜን እና ከሸዋ በመጡ ሰዎች የተያዘው የሀላፊነት እና የመሪነት ቦታ በአካባቢው ተወላጆች ተወስዷል፡፡ ያ ግን በዋናነት የሚያሳየው የአካባቢው ሰው የስልጣን ባለቤት መሆኑን እንጂ ይሆነኝ ተብሎ በቀድሞዎቹ መሪዎች እና ዜጎች ላይ የደረሰን በደል አደለም፡፡


አማራውም ትግሬውም ሸዌውም በአካባቢው ራሱን የመምራት መብት እንደ ተጎናጸፈ ኁሉ ሌላውም ብሄር ራሱን የመምራት ሀላፊነትን እንደ መብትነቱ መጎናጸፉ ምንም ክፋት የለውም ብቻ ሳይሆን ተገቢና ትክክል ነው፡፡ ምን ያክል እርካታም በጋሞጎፋ ተወላጆች ዘንድ እንደፈጠረ አውቃለሁ፡፡


መተቸት ያለበት እንዲህ ያለውን ራስን የመምራት ሃላፊነት በአካባቢው በሚኖሩ ሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ላይ ጉዳት እና አድሎ ለማድረስ የሚጠቀሙበት ሀላፊዎች እና ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች የሚኖሩ ከሆነ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች እንዳይኖሩ ማድረግ የሚቻል ባይመስለኝም እንዲህ አይነት ጠባብ አመለካከታቸውን ሲተገብሩት ያለርህራሄ ማድረቅ ግን ያስፈልጋል፡፡


ከዚህ በመለስ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች እንደ ዜጋ ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርት እስካሟሉ ድረስ በመረጡት ዘርፍ ተሰማርተው ሀብት የማፍራት የመስራት መብታቸው ሕገመንግስታዊ እውቅና ያገኘና ሊከበር የሚገባው መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በየግዜው ኢህአዴግ ጠባብነት ትምክህተኝነት ጎጠኝነት ቡድንተኝነት የሚሉ የግምገማ መስፈርቶች በማበጀት አመራሮቹን እና አባላቱን የሚገመግመው ይህን መሰሉን የአባላቱን እና የአመራሮቹን የባህርይና የልምድ ክፍተት ለመሙላት ነው፡፡


ሕዝቦችን የማባላት እንጂ መብት የማክበር አጀንዳ አደለም የሚለው የመከራከርያ ነጠብ ከዚህ ሀቅ አኳያ ሲመዘን ባዶ ጉንጭ ማልፊያ ሙግት መሆኑን ከላይ የተጠቀሰው የክርክር ሀሳብ ያሳያል፡፡ ይልቅ ክርክሩ ሰሜኖቹና ሸዌዎቹ በክልላቸውም ከክልላቸውም ውጭ አመራር ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል በሚል ቢቀርብና ብንወያይ ይሻላል፡፡ ከዳዊት ዘር ከሰለሞን ዘር የሚለውን መከራከሪያ ሀሳብም ይዞ መቅረብ ይቻላል፡፡


በርግጥ አንድ ሰው ተወላጅ ባልሆነበት ክልል ማስተዳደር የሚያስችል ሰብአዊ ብቃት አለው፡፡ ያን ማድረግም ይቻላል፡፡ አሁን ያለውም ህገመንግስት ዜጎች ከክልላቸው ውጭ መሾም አይችሉም አይልም፡፡ የሆነ ሆኖ በአካባቢው ህዝብ ምርጫና ውሳኔ ይሁን ነው፡፡


ለምሳሌ በቅርብ በማውቀው አማራ ክልል የሌላ ብሄሮች ተወላጆች የሆኑ ግለሰቦች ከከተማ እስከ ክልል ባሉ ከፍተኛ ሀላፊነቶች ላይ ሲሰሩ አያለሁ፡፡ ይሄ ግን የክልሉ ሕዝብ የመረጣቸው በመሆኑና ወይም ተመራጮቹ ሃላፊነቱን መወጣት ይችላሉ ብለው ስላመኑባቸው እንጂ በጫና የሚሆን አደለም፡፡ ተመሳሳዩ ተግባር በሂደት በሁሉም ክልል መከሰት ይችላል፡፡ ህዝቡ ወይም የክልል መንግስታት እምነት የሚጥሉባቸውን ግለሰቦች ለማስቀመጥ ሲወስኑ፡፡


እስካሁን ባለው ሂደት ተወጥሮ የነበረው የብሄር ፖለቲካ ከህገመንግስታዊ ድንጋጌዎቹ መተግበር በኋላ እየረገበ የመጣበት ነው፡፡ በሂደት ሰው ጥሩ አገልጋይ የሚሆነው በደሙ ምክንያት ሳይሆን ጠንካራ ስነምግባር ስላለውና ለስራው ብቁ ስለሆነ ነው የሚለው እምነት እየጠነከረ ሲሄድ ህዝቡ የግድ የኔ ብሄር ደም ካልሆነ የሚል መስፈርት ይዞ ይቀጥላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ራስን በራሰ ማስተዳደሩ እንደቀጠለ በሚበዛው የክልሉ ተወላጅ መሀል የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ለህዝቡ የሚሰሩ ጠንካራ አመራሮችን መርጦ ማሰራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ያ ግን በሂደት መተማመን በመፍጠር ግለሰቦችን በተሟላ የአቅምና ስነምግባር መለኪያዎች መለካት የሚያስችል የግንዛቤ ደረጃና አሰራር ስር እየሰደደ ሲሄድ የሚደረስበት ነው፡፡


ሲጀመር ከዚህ ብሄር ስለሆንክ ተንቀሀል ዛሬም የሚመሩህ ሰሜኖች ናቸው ያንተ አካባቢ ሰዎች ለይስሙላ ነው የተቀመጡት የሚለው የጦዘ ዘረኛ አተያይ በቀጠለበት ይህ መሰሉ ብስለት በቀላሉ እንዲፈጠር መጠበቅ ፓለቲካን በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ የዋህነት ይመስለኛል፡፡


የብሄር ጥያቄና ኢህአዴግ
ያለፉትን አንድ መቶ አመታት በላይ ታሪክ ስንቃኝ የብሄር ጥያቄ ሊኖራቸው የማይችለው ምናልባት አማራና ትግሬ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኣማራ ክልል ሌላ ማንም ብሄር ባህሉን ቋንቋውን ማንነቱን በሚንድ አማራጭ ተጽእኖ አድርጎበት አያውቅም፡፡ በመሆኑም አማራው ይህን የመሰለ ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄ የለውም፡፡ ጥያቄው ኖሮት የማያውቀው ደግሞ መሰል በደል ደርሶበት ስለማያውቅ ነው፡፡


ከመላው ሀገሪቱ የሚነሳውን የማንነት እና የብሄር ጥያቄ ግን የማይረዳና ያልታገለበት ደግሞ አደለም፡፡ እነ ዋለልኝን የመሳሰሉ ያን መሰሉን የብሄር ጥያቄ ይታገሉበት የነበረ ከመሆኑ አኳያ ሲታይ ደግሞ የሀገሪቱ ህዝቦች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አማራ ባዳ ያልነበረ መሆኑን እናያለን፡፡ ቀጥሎም ኢህዴን/ብአዴን ተመሳሳዩን የህዝቦች ጥያቄ በማክበር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታው በወሳኝነት የብሄር ጥያቄንም የተሟላ መልስ የሚሰጥ እንዲሆን ተጋድሏል፡፡


በርግጥ የአማራ ህዝብ የዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ትግሉ ከብሄር ጥያቄ በመለስ ቢሆንም ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ያላቸውን የብሄር ጥያቄ ግን የሚረዳ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ ኢህአዴግ የፈጠራቸው ሳይሆኑ መብቶቻቸው የተገፈፉባቸው ህዝቦች መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት የረጅም ግዜ ትግላቸው ውስጥ ውስጡን ይብላላ የነበረ ታሪካዊ ጥያቄ በመሆኑ፡፡


ይህ ሁሉ የሆነውና ወደ ሽምቅ ውግያ ትግልነት የተሻገረው ከዛሬው ጎልማሰው ኢህአዴግ መስራቾች ህወሀት/ኢህዴን መመስረት ቀድሞ ነው፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግን በብሄር ጥያቄ አነሳሽነትና አጋጋይነት መክሰስ ትክክል አደለም ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ረገድ ያደረገው የተለየ ነገር ጉዳዩን የተረዳበትና ፖለቲካዊ መፍትሄ ያበጀበት አግባብ ብቻ ነው፡፡


አማራጩ ከአዲስና ከነባር አማራጮች የተለየ በመሆኑ የተለየ አማራጭ ሲያቀርቡ ለነበሩ ቡድኖች እና ግለሰቦች ላይዋጥላቸው እንደሚችል መገመት ከባድ አደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ኢህአዴግ ጥያቄውን ማፈን ሳይሆን ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ያም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲወሰን የማድረግ በመሆኑም በህዝቦች መካከል ቅራኔ ይፈጥር የነበረው ጉዳይ እንዲከስም አስችሏል፡፡


የእኩልነት ጥያቄ ከምንም በላይ ራስን በማስተዳደር ይገለጣል፡፡ ራስን ማስተዳደር መቻል የእኩልነት መገለጫ አናት ተደርጎ ይታያል፡፡ በመሆኑም ያን ኢህአዴግ ማስከበሩ ሀገሪቱን በመበታተን እና አንድ ሆኖ በመቀጠል መሀል ይጎትቷት የነበሩ ጉዳዩችን እንዲያከስም አስችሎታል፡፡


ራስን የማስተዳደር ጉዳይና ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታዊ መዋቅር መዘርጋቱ ከፍም ሲል የመገንጠል ጥያቄ ሊቀርብበት የሚችል ሰፊ ፖለቲካዊ ምህዳር ማበጀት ተጋግሎ የነበረውን የብሄር ጥያቄ ያስተነፈሰ በወጣቱ ኢህአዴግ የቀረበ በሳል ዴሞክራሲያዊ አማራጭ እንደነበር አለመረዳት የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ በወጉ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ መሬት ያለውን ችግር ሳይሆን ህሊናዊ ህልማችንን ከማንበብ የሚመነጭ ድክመት ነው፡፡


ይህን የማይረዱና ይህን መሰሉን መፍትሄ የማይገነዘቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉ ችግሩ የኢህአዴግ ሳይሆን በቅጡ የማያውቁትን ፖለቲካና ሀገር ችግር እንፈታለን በሚል ወደመድረኩ የመጡ ፖለቲካ ሀይሎች ነው፡፡ በማንኛውም መስፈርት ህዝቡ ራስህን በራስህ ማስተዳደርህ ይከፋሀል ወይ ተብሎ ቢጠየቅ የሚሰጣቸው መልስ ለምን እንደምታገል ምን ያንገበግበኝ እንደነበር አታውቁም ማለት ነው ይላቸዋል፡፡


ይልቅ መታገል እንዲህ ያለውን ራስ ማስተዳደር ሌሎች ብሄሮችን ለመበደል እና ለአድሏዊ አሰራር እንዳይውል ነው፡፡ በአንድነት ስም የብሄሮች መብት የታፈነውን ያክል በራስ አስተዳደር ስም ሌሎች ብሄሮች እንዳይበደሉ ጠንካራ የአመራር ስራ ማስፈን ይጠይቃል፡፡


ከዚህ በተረፈ ህዝብ ህሊናዊ ተፈጥሯዊ አቅሙን የሚመጥነው የራስ አስተዳደር መመስረቱ በምንም መስፈርት የጥርጣሬ እና ያለመተማመን መንፈስ አይፈጥርም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው በአቅሜ በማንነቴ በቋንቋዬ እንድሰራ የሚያምን ህገመንግስት መደንገጉ የቅቡልነቴ እንደ  ህዝብ የመከበሬ ማሳያ በመሆኑ በዚህ ህገመንግስት ዙርያ ወደልማት የምንገሰግስበት የቀሩንን እና የጀመርናቸውን ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ይበልጥ እየገነባን የምንሄድበት ሁኔታ ነው ያለው የሚል መተማመን ይፈጥራል እንጂ ተቃራኒውን አያመጣም፡፡ ያ ያለፈው ዘመን የሰጠን ችግር ነበር እሱንም ለመናድ ነው ይሄ መፍትሄ የተበጀው፡፡ አረዳዱ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡


የ1983ቷ ኢትዮጵያ
እስቲ ጨመር አድርገን ዛሬ በስልሳዎቹ መጀመሪያና በሀምሳዎቹ መጨረሻ ያሉት የኢህአዴግ አመራሮች በአብዛኛው በሰላሳዎቹ መጀመሪያዎችና በሀያዎቹ መጨረሻ በነበሩበት ለጋ እደሜያቸው ያቀረቡትን መፍትሄ በነጻ ህሊና እንገምግመው፡፡
ለአስርት አመታት ኤርትራን ለመገንጠል ሲዋጋ የነበረው ሻቢያ ልክ እንደ ኢህአዴግ ሁሉ በመሳሪያ የተዋደቀለትን አላማ ለማስከበር የሚሻውን አማራጭ ለማስፈጸም የተፋጠጠበት ነበር፡፡


ደርግ በውድም በግድም አንድ አድርጎ ለማቆየት የተከተለው አማራጭ በሌሎች አማራጮች በጉልበት የተረታበት እና ኢትዮጵያ ሻብያ ኦነግ ኦብነግ እና ሌሎች የታጠቁ ቡድኖች ሁሉ ከነነፍጣቸው በተሰለፉበት አማራጭ እየፈለገች ያለችበት ሁኔታ ነበር፡፡
ለነዚህ መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች በመሪነት አማራጭ እየፈለገ ያለውና መፍትሄው በህዝቡ ይሁንታ እንዲፈጸም ሲወጣ ሲወርድ የነበረው ደግሞ የወጣቶቹ ፓርቲ ኢህአዴግ ነበር፡፡ ኢትዩጵያ አንድነቷ በማንኛውም ምክንያት ለብተና መዳረግ የለበትም የሚሉ ቡድኖች በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ መገንጠል እንጂ ሌላ አማራጭ የለም የሚሉ ቡድኖች በተፋጠጡበት ወጣቱ ኢህአዴግ የሁሉንም ወገኖች ጥያቄ የሚያስተናግድ አማራጭ ማቅረብ ነበረበት፡፡


በአንድ በኩል ኤርትራውያኑ አዲሲቱ ኢትየጵያ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን አክብራ የምትቀጥልበት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲፈጠር ሳይሆን በደማቸው ያስከበሩትን እና ልክ እንደ ኢህአዴግ ሁሉ በመሳርያ የተቆጣጠሩትን ድንበር የአለማቀፉ ህብረተሰብ እውቅና ሊሰጠው በሚችለው አግባብ ሀገሪቱ እንድትደመድምላቸው የሚጠይቁበት


በሌላ በኩል ደግሞ መገንጠል ሳያስፈልግ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ አማራጮች ሀገሪቱ አንድነቷን ጠብቃ ልትሄድ የምትችልበት አማራጭ በውድም በግድም እንዲፈጸም እንጂ ሌላ ማንኛውንም አማራጭ ሀገር እንደ መሽጥ የሚቆጥሩ ቡድኖች የተሰባሰቡበት
በዚሁ መሀል ግን ወጣቱ ኢህአዴግ የህዝቡን ይሁንታ ያገኘ መፍትሄ እንዲበጅ ሁለቱንም ቡድኖች በማረጋጋት መፍትሄ የማፈላለግ እና በዴሞክራሲያዊ አኳኋን እንዲፈጽም መስራት ነበረበት፡፡ መፍትሄ ፈላጊው ራሱ በአስገንጣይነት/ገንጣይነት በሚከሰስበት ግን ምንም አይነት ዴሞክራሲያዊ አማራጭ ቢያስቀምጥ ከመፍትሄው ባህሪ አንጻር ሳይሆን በውጤቱ በማይሳማሙት ሁለቱም ቡድኖች የሚከሰስበት ሁኔታ መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡


ምንም ይሁን ምን ግን ለዚህ ሀገራዊ ጥያቄ ወጥና ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ ማበጀት ይገባ ነበርና ወጣቱ ኢህአዴግ መፍትሄውን ለአጠቃላይ ሀገራዊ ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ መፍትሄ በሚሰጥበት አግባብ መፍታትን መረጠ፡፡ በመሆኑም ተረስተናል ተትተናል ተንቀናል እንዲህ ባልተከበርንበት አገር የሚኖረን ከራሞት በአግባቡ መፍትሄ ባላገኘበት አንቀጥልም የሚል ድምጽ ወዲህም ወዲያም ለሚያሰሙ በተደራጀ መልኩ ለሚታገሉም ለማይተገሉም ግን ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ላላቸው ህዝቦች ሁሉ መፍትሄ የሚሰጥን አግባብ ተከተለ፡፡


የወጣቱ ፓርቲ ወጣቶቹ አመራሮች በሳል መፍትሄ የሚሰጡበትን አማራጭ መከተላቸው የሚያመለክተው ከእድሜያቸው ለጋነት ውጭ ለሀገራዊ መሰረታዊ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች መፍትሄ ሊሰጡ በሚችሉበት አግባብ ስክነት ያሳዩበት ህዝቡ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ያላቸው ቁርጠኝነት የእውቀትና የመረጃ ክፍተታቸውን የሚሞላበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡


በመሆኑም ጉዳዩ ፈጦ ለወጣው በጦር መሳርያ መልስ አግኝቶ ህጋዊ ምላሽ ለሚጠይቀው የኤርትራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ህዝቦች የመብት ጥያቄ መልስ ሊሰጥ በሚችል አግባብ እንዲፈታ ህገመንግስታዊ አማራጭ ቀረበ ህዝቡም ለዚህ ህገመንግስታዊ አማራጭ እውቅና ሰጠው፡፡


ይሄ ማለት ግን በአማራጭ መፍትሄው የተበሳጩ እና እስካሁን በመፍትሄነቱ የማያምኑበት የሉም ማለት አደለም፡፡ ሆነም ቀረም ግን መፍትሄው ለመላው የሀገሪቱ ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ሁነኛ እውቅና የሰጠና ለህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ተፈጥሮአዊ አቅምና ፍላጎት ወሳኝ መላ ያበጀ ውሳኔ መሆኑ አጠራጣሪ አደለም፡፡


ይህን ውሳኔ የሚቃወሙትም ቡድኖች ይህን የመሰለውን የህዝቦች አቅም የማይገነዘቡና ህዝቦች ራሳቸውን ማስተዳደራቸው ስህተት ነው ብለው ስለሚያስቡ አደለም፡፡ ይልቁንስ ህዝቦች ራሳቸውን ማስተዳደራቸው መገንጠል ለሚፈልጉ ቡድኖች አመቺ ነው ከሚል ፍርሀት ስለሚነሱ ነው፡፡


በእኔ አተያይ ሕዝቦች በአንድነት ዙርያ ተሰባስበው የሚኖሩት የራሳቸው አስተዳደር ሊመሰርቱ እንደማይችሉ በህገመንግስት ስለተከለከሉ ሳይሆን አንድነት ከመገንጠል የተሻለው አማራጭ ስለሆነ እና አንድ የሚሆኑት ራሳቸውን ስላስተዳደሩ ስላላስተዳደሩ ሳይሆን አንድነትን የሚያስችሉ ወይም የሚያቋቁሙ መሰረታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዩች ስላሉ ነው፡፡


በኔ እምነት ለሻብያ አመራሮችም ቢሆን ኢህአዴግ ሀገሪቱ አንድ ሆና መቀጠል እንድትችል ብቻ ሳይሆን አንድነታችን የየትኛውም ጭቆና መነሻ ምክንያት እንዳልሆነ  በማብራራት በአንድነቱ ውስጥ የተሻለች ኢትዮጵያን መመስረት የሚቻልበት አግባብ እንደሚኖር ያልተመካከሩ አይመስለኝም፡፡ ሆነም ቀረም ግን ራሱን የኢትየጵያ አንገት አድርጎ ለሚያይ ቡድን ያለ አሰብ ኢትዩጵያ ፋይዳ አይኖራትም ብሎ ለሚያስብ ሀይል እንዲህ ያለው አማራጭ የሚዋጥለት አይነት አደለም፡፡


እንዲያውም እቺን ከንቱ አገር ምን ያክል ወሳኝ እንደሆንን እናሳያታለን በሚል እብሪት ሻብያ ሊመረዝ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ከመገንጠሉ በኋላ ወደነበሩ አይንአውጣ ቅጥፈቶች ባልገባ ኢትዮጵያን ታክል አገር ድንበር እነጥቃለሁ ብሎ ጦርነት ባልከፈተ ነበር፡፡


ያው የኛ አገር በአንድነት ዙርያ በርካታ የተሳከረ አቋሞች ይራመዱባት የነበረች ከመሆኗ አንጻር ሲመዘን ሻብያ ያን ያክል መወጣጠር ውስጥ ቢገባ አይገርምም፡፡ ኤርትራ አንገታችን ናት አንገታችንን መቆረጥ የለብንም የሚል ስብከት የሚያሰሙ የአንድነት የሚመስሉ ግን የማይገባና የሌለ ግዝፈት ለኤርትራ የሚሰጡ ዜማዎች ባሉበት ከጠዋቱም መገንጠል አለብን ብሎ ለሚያስብ ቡድን ሁኔታው ምን ያህል የሚያኩራራ መሆኑን መገመት አይሳነኝም፡፡


ይህ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ ግን የብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች መብት ራስን ከማስተዳደር ጀምሮ እስከ መገንጠል የተከበረ መሆኑ በአስር ሺዎች ወጣቶች ለዘመናት የተገበሩበትን የኤርትራን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላውን ህዝብ መብት ያከበረ ሆኖ መደንገግ የመፍትሄውን ወጥነት እና ዘላቂነት የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የብሄር ጉዳይ በአግባቡ ባልተፈታበት ሌላ ኤርትራዎች ጋር ወደ ውጊያ እንደማነገባ ማስተማመኛ አይኖረንምና፡፡


በመሆኑም ጉዳዩ ያፈጠጠውን የኤርትራን ጥያቄ ብቻ በመመለስ ሳይሆን የአጠቃላይ የሀገሪቱን አብይ አጀንዳ መፍታት በሚያስችል መልኩ መመራቱ ወጣቱ ኢህአዴግ ከእድሜው ከፍ የሚል መለኝነትና ቁርጠኛነት የተላበሰ መሆኑን ያሳብቃል፡፡
የሰሜኖች የበላይነት በተለይ ደግሞ የአማራ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት በዝቷል ተብሎ በሚታመንበት ኢትዮጵያዊነት ራሱ አማራው የፈበረከው ሸክም ተደርጎ እስካሁን በአንዳንድ የብሄር ጠበቃ ነን በሚሉ በሚቀነቀንበት ሁነኛው መፍትሄ ለማንኛውም ምክንያታዊ ህሊና ሁሉም ብሄር ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር መፍቀድ መሆኑ እሙን ነው፡፡


ራስን በራስ ማስተዳደር ተፈጥሮአዊም ፍላጎት ጭምር ነው፡፡ የነጻነት ጫፍ ሆኖ የሚታየው ምልክትም ራስን በራስ ማስተዳደር መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በመሆኑም ይህ መፍትሄ ኤርትራውያኑም በድምጽ ብልጫ ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት ሌላውም ሀገሬ መብቱን አስጠብቆ ሊኖር የሚችልበት አማራጭ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ በዚህ ሁኔታ አዲሲቱ ኢትዮጵያ መብቱን አስጠብቃ መቀጠል ከተሳናት ደግሞ ልክ እንደ ኤርትራ ሁሉ በህዝብ ውሳኔ መለያየት የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን እና ነፍጥ የሚታጠቅለት ሁኔታ ያበቃ መሆኑ የተበሰረበት ውሳኔ ነው፡፡


በማንኛውም ሚዛን ኢህአዴግ የኤርትራ ጉዳይ ከመገንጠል በመለስ ባሉ መፍትሄዎች እንደማይፈታ ስለሚያምን ነው ያን አማራጭ ያቀረበው ብሎ ማመን ቁልጭ ያለ ስህተት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ያ ካልሆነ ብሎ በተፋጠጠ ለዘመናት ባዳማ ጉዳይ ፊት ጉዳዩ ደስ በማያሰኝ ግን በመገንጠል ቢቋጭም እንኳ የህዝብን ድምጽ አክብሮ በህዝብ ውሳኔ እንዲቋጭ ማድረግ ብቻ ነበር አማራጩ፡፡ ያ ሆነ ኤርትራ ተገነጠለች፡፡ ኢህአዴግ ጮቤ አልረገጠም፡፡ ግን ለህዝቡ ጉዳዩን በምርጫ እንዲወስን በማስቻሉ ወደ ፊት ከዚህ ህዝብ ጋር በሚኖሩ ግንኙነቶች ረገድ የሚኖረውን ፋይዳ በመመዘን የተካሄደ የነበረው ብቸኛ ዴሞክራሲያዊ አማራጭ ነበር፡፡


በአንድ በኩል ነፍጥ አንስተው ለመገንጠል ሲዋጉ ለነበሩና ለማስገንጠል የሚፈልጉትን አካባቢ ተቆጣጠረው አለማቀፉ ማህበረሰብ እውቅና በሚሰጠው አግባብ ህጋዊ ፍቺ ለሚጠይቁት መልስ የተሰጠበት በሌላ መልኩ ደግሞ ለሌሎች መሰል ጥያቄ ላላቸው ቡድኖች አዲሲቱ ኢትዮጵያ ይህን መሰሉን ጥያቄ በጦርነት የመፍታት አጀንዳ የሌላት መሆኑ የተረጋገጠበት፡፡ ይልቁንም ያን ለመሰለ የህዝቦች ጥያቄ በማያዳግም መልኩ በህገመንግስቷ እውቅና የሰጠች መሆኑ የታወጀበት ነበር፡፡


ህዝቦች ይህ እውቅና በተሰጠበት ነፍጥ የሚይዙበትም ይሁን ነፍጥ ለሚያነሳ ድጋፍ የሚሰጡበት ሁኔታ ከሰመ፡፡ ሁሉም ብሄር በየአካባቢው ራሱን የሚያስተዳድርበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በፌደራል መንግስት የሚኖረውም ቦታ በኮታ የሚፈጸምበት አግባብ እውን ሆነ፡፡ ማንኛውም ብሄር እነ አገሌ ተጫኑኝ ሊል የሚችልበት ሁኔታ ተናደ፡፡ በመሆኑም በመላው ሀገሪቱ ህዝቦች ወደራሳቸው የሚያዩበት ለልማቱም ለውድቀቱም ራሳቸው ተመስጋኝ ራሳቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በመተባበር እና በመከባበር መንፈስ የሚሰሩበት አግባብ ተፈጠረ፡፡


ይህ የምስራች ለተወሰነው ቡድን ሀገራዊ ውርደት ነበር፡፡

አውን ኤርትራ ማን አንገት አደረጋት የሚለው ጽሁፍ ከዚህ ለጥቆ ሊታይ ይችላል

No comments:

Post a Comment