ከህወሃት ሌሎች እህት ፓርቲዎችም ይሁኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊማሩት የሚገባው ጥንካሬ ይሄ
ነው - በአንድ የፖለቲካ አቋም ዙርያ ጠንካራ እምነት ያለው ሰፊ እና በቅጡ የተደራጀ ህዝባዊ መሰረት መገንባት። የትግራይን ህዝብ
ቀስበቀስ ግን አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ በማደራጀት ልጆቹን ለጦርነት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ያስተማመነ ጠንካራ ድርጅት ነው።
ለአላማው ሲል ሞትን እሺ በጄ ብሎ የሚቀበል ህዝባዊ መሰረት መፍጠር ግዙፍ ስኬት ነው።
ለዚያ ነው ከሶስት ሚሊየን የማይበልጠውን
የትግራይን ህዝብ አደራጅቶ ሀገር የሚመራውን ደርግን ያንበረከከ ሰራዊት እና አደረጃጀት በ17 አመታት ሂደት የፈጠረው ። ያ አደረጃጀት
እና ሰራዊት ደግሞ ራሱን ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ድጋፍ በሚሰጠው ሰፊ የትግራይ ህዝብ ድጋፍ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ
አሸናፊ መሆን ችሏል።
ዛሬም ድረስ አጋር ድርጅቶቹን በማጣጣል ህወሃት ነው ይሄን አገር የሚያሽከረክረው የሚባለው
አቤቱታ የሚሰማው ይሄን መሰሉ ህዝባዊ ድጋፉ የፈጠረለትን ጠንካራ አደረጃጀት ከመረዳት መሆኑ አይጠረጠርም።
አሁን መፍትሄው ለማንኛችንም ህወሃትን መጥላት አደለም። መፍትሄው እንደ ህወሃት ባላፊ
አግዳሚው ተቃውሞና ማዕበል እማይፍረከረክ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ፓርቲዎች ቀስበቀስ ግን አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ማነጽ ነው።
እንዲህ ያለው ጥንካሬ ደግሞ በሰሞነኛ ጫጫታ እንደማይፈጠር አውቆ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ህዝብ የሚያስተማምን ፕሮግራም መቅረፅ ያን
ደግሞ ሳይሰለቹ ለህዝብ ማስተዋወቅ እና በዚያ ዙርያ የተሰባሰበ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ማነጽ ይጠይቃል።
ይህን አይነት አደረጃጀት ሲኖርህ ከ33 ሚሊየን ከሚበልጠው ኦሮሞ እና ከ25 ሚሊየን ከሚበልጠው
አማራም ቢሆን የሚሻል ጥንካሬ ልትገነባ ትችላለህ። ቁምነገሩ በአስተማማኝ አላማ ዙርያ የተማመነ ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ ማቋቋም
አለማቋቋም እንጂ ብዛት እንዳይደለ ማን በነገረልኝ።
ለዚህ የሚተቸው ደግሞ ጠንካራ ሆኖ የተገኘው ህወሃት አደለም። ጥንካሬ ከሌላቸው ሊተቹ
የሚገባቸው በህወሃት ደረጃ እና ጥልቀት ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት መገንባት ያልቻሉት ሌሎች አጋር ፓርቲዎች እና የሚመለከታቸው ደካሞ
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው።
የካቲት 11 ይህን አይነቱን ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ ለመመሰረት ጠንሳሽ ቀን
በመሆኑ እናደንቃለን።
ነፍሱን ይማርና መለስ ዜናዊ አስር የተደራጀና የታጠቀ ሰራዊት አንድ መቶ የታጠቁ ግን
ያልተደራጁ ሀይሎችን ሊያጠፋ ይችላል ይል ነበር። ሳይደራጁ እንቡር እንቡር ማለቱን ትተን እስኪ ለሁነኛ ለውጥ ጠንካራ እና ሰፊ
ህዝባዊ መሰረት ያለው አደረጃጀት እንፍጠር።
ይህን ለመሰለ ህዝባዊ አደረጃጀት የተሰው ጀግኖችን ማሰብና ክብር እንደሚገባቸው መናገር
ከተግባራቸው ለመማር እና ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው ፓርቲ ከማቋቋም ሌላ
መሰረታዊ እና ሁነኛ ሚና የሚጫወት ፓርቲ መመስረት የሚቻልበት መንገድ ዝግ ነው።
ለዚህ ጥንካሬው ህወሃትን ከመተቸት የተሻለው አማራጭ ማድነቅና ያን ትምህርት ወስዶ የሚመለከተው
ሁሉ ጠንካራ ፓርቲ መገንባት እንዳለበት አምናለሁ። መራራ ድክመትን ተቀብሎ ማረም እንጂ ጠንካራውን ስለብርታቱ መጥላት የከፋው አደጋ
ነው - የመማር እድላችንን ዝግ ያደርገዋልና።
ህወሃትን መገዳደር ስታስብ ያንን ህዝባዊ መሰረቱን የሚፎካከር መሰረት ያለህ መሆኑን ደጋግመህ
እንድታስብ ትገደዳለህ። ህወሃት ብቻውን ግን በቂ አደለም። እነ ብአዴንም ኦህዴድም ደህዴንም በእንዲህ አይነት ህዝባዊ መሰረት ላይ
ራሳቸውን አጠንክረው መትከል ይጠበቅባቸዋል። የ97 ምርጫ የናጠው ያን አይነት አደረጃጀት ያልፈጠሩ ፓርቲዎችን መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ተቃዋሚዎች በሌሎቹ ክልሎች የሚያገኙትን አይነት ድጋፍም ማግኘት የተሳናቸው
አስተማማኝ መሰረት በተጣለበት ትግራይ መሆኑ አይሳትም።
ጨዋታው የቁጥር እና የብዛት አደለም። ጨዋታው የተሳካለት አደረጃጀት የመፍጠር አለመፍጠር
መሆኑ አይሳት። ያን አይነት መሰረት ደግሞ ለፖለቲካው መረጋጋት እና ለፍትህ መንገስ ትልቅ ሚና አለውና ለሁላችን የሚተው የቤት
ስራ ነው። ከመደንፋት ባሻገር ያለው ያልተወጣነው ስክነት እና ጠንካራ እንዲሁም ተከታታይ ስራ የሚጠይቀው
ተግባር ይሄ መሆኑ አይሳት።
በመጨረሻ ቁምነገሩ ህወሃት እንዲዳከም ከመስራት እንደ ህወሃት ጠንክሮ መገኘት የሚሆነውም ለዚህ ነው። ይህን ሀቅ
ስንረዳ ደግሞ ህወሃትን ለዚህ ያበቁትን የመለስ ዜናዊን የመሳሰሉ ጭንቅላቶች አንዘነጋም። በርግጥም ክብር ይህን መሰል አደረጃጀት
እና ታጋይ ድርጅት መፍጠር ለቻሉ ሰማዕታት። አድንቅ ከምታደንቃቸው ጠንካሮች ተምረህ ደግሞ ተመሳሳዩን ቁመና ፍጠር። ሲተቹ ከመኖር
ግዜ ወስዶ ጠንካራ ሆኖ መታነጽ ይሻላል ባይ ነኝ።
No comments:
Post a Comment