Saturday, March 2, 2013

የአድዋን የድል መንፈስ እንቀስቅስ



አድዋ የቆራጥ ኢትዮዽያውያን አቅም በአግባቡ ከተመራ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ያመላከተ ገድል ነው$ በርግጥም ሰይፍ ከዘመናዊ መሳርያ ጋር ፊትለፊት ተጋፍጦ በአሸናፊነት የደመቀበት ነውና$ ያ ድል ፍትሀዊ የትግል መነሻና ቆራጥነት በተባ አመራር እስከተያዘ ድረስ አሸናፊነት የማይቀር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው$

ከአደዋ ምን እንማር
መንግስታዊ በሆነም ባልሆነም ተቋም አቅማቸው በፈቀደ የሚሰሩት የዛሬዎቹ ጀግኖች መመስገን ያለባቸው ሆኖ በአመዛኙ የዛሬዎቹ ኢትዮዽያዊያን ችግሩ ያለበትን ትክክለኛ ቦታ የማከክ እና የማረም ችግር አለብን$ አንደኛ ብዙዎቻችን የተሰጠንን ሀላፊነት ቦታው ምንም ይሁን በተለያዩ ኩርፊያዎችና ሱሶች ተጠምደን በአግባቡ የማንወጣ ነን$ ሌሎቻችን ደግሞ ሃላፊነታችንን በአግባቡ የምንወጣ ከቅጥራችን ውጭ ሰው እንኳ ቢገደል እንዴት እንዲህ ይሰራል ብሎ የመጠየቅ ወኔም የይመለከተኛል መንፈስ ያልፈጠረብን ግድየለሾች$

ደሞ ሌሎቻችን ኪሳችን የሚገባ ፍርፋሪ የሚገኝ ከሆነ ባልደረቦቻችንን ለማጥፋት እና ደንበኛን ከመዝረፍ የማንመለስ ጅቦች ነን$ እንዲያው የሚፈጸመው በደል የሚቆረቁረን ብዙዎች ደግሞ በየጥጋጥጉ ከማማት ባለፈ ፊትለፊት ስህተቱን የፈጸመውን ሀላፊ ተጠያቂ የማድረግ የመወያየት ወኔ ያልፈጠረብን ፈሪዎች$ ያው ግን ዝም ብለዋል እንዳይባል ምን አይነት ባለጌ ነው ባክህ እንዴት እንዲህ ይደረጋል የሚል ቅኝት በየሻይ ቤቱ የምንዘምር$ ደፈር ያልነውም የሚመለከተው ሀላፊ ተጠያቂ የሚሆንበትን ህጋዊ መንገድ ተከትለን በመድረክ ከመርታት ይልቅ በአንድ በሁለት ድንፋታ አድሏዊነት ሙስናና ዘረኝነት እንዲፈታ የምንመኝ የዋሆች ነን$

ለውጥ እንደ አድዋው ውጊያ ያንተ የሆነውን ለማስጠበቅ የህዝብ የሆነው ለህዝብ ይድረስ በሚል መንፈስ መስራትን ይጠይቃል$ እናም እንዲህ ያለ ህዝባዊ አላማ አንግተን ስናበቃ ደሞ አላማችንን የሚመጥን ትጥቅ አቅም ጉዳዩ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ በቁርጠኝነት የመቀጠል ድፍረት እና ዝግጁነት ይፈልጋል$

በየተቋማቱ የሚታዩትን ችግሮች በየመስሪያ ቤቱ ያሉ ሰራተኞች ካልፈሩ በቀር ከማንም በላይ ያቋቸዋል$ ከሆነ ደግሞ ስርአት እና ህግን ተከትሎ የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍሎ መታገልና መፍታት ነው$ የገንዘብ ሚንስትርን ችግር ለመፍታት የውሀ ሚኒስትር ሰራኞች አይሰለፉ የሸቀጣሸቀጡን ችግር በግንባታ ዘርፍ የተሰማራው ባለሀብት እንዲፈታው አይጠበቅ መሆን ያለበት በያለንበት ለደንበኛ የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ ሂደቱ የሚጠይቀውን ዋጋ መክፈል ነው$

ይሄ አገር የኖረው መሞት የሚጠይቀውን አድዋን በተጋፈጡ ጀግኖች ነው$ በርግጥ ለማን ብዬ ነው የምሞተው የሚሉ ብልጣብልጥ ነን ባይ ፈሪዎች በዝቷል$ ዛሬ ለመሆኑ ትግል የሚጠይቀውን ዋጋ የሚከፍሉት እነማን ናቸው ሁሉም ጥግ ይይዛል$ ሁሉም ለመኖር አይመችም በሚለው አገር አርፌ ልጆቼን ለሳድግ ይላል$ የማይመች ከሆነ ልጆቹስ ቢያድጉ ምን ዋጋ አለው ትግሉ መካሄድ ያለበት እንዲያውም ለልጆቻችን ሲባል ነው ለምቾታቸው የምትመጥን ሀገር ለመፍጠር$

መንግሰታዊ መዋቅሩና ህጉ የሚፈቅድልንን የመጠየቅ ፍትሀዊ አገልግሎት የማግኘት መብታችንን እንኳ ለመጠየቅ እዚግቡ የማይባሉ በተጨባጭ ስርአቱን መጠምዘዝ የማይችሉ ቢሮክራቶችን ፈርተን ጥግ ይዘናል እኮ$ ጎበዝ በዚሁ ባህሪ እኛ አሁን የአድዋ ልጆች የአድዋ አክባሪዎች ነን አድዋ እኮ ጥይት ለመጠጣት የማይፈሩ ጀግኖች ሀውልት ነው$ አድዋ እኮ የጥቁር አሸናፊነት ምልክት ነው$

በመሀላችን ያሉ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ተከታትለን ህጉ በሚፈቅድልን አግባብ ለመፍታት የማንነሳሳ ከሆነ የምር ለፍርሀታችን ምን ወሰን አለው$ በርግጥ ዛሬም ለጥይት ደረቱን ይሰጣል ኢትዮፕያዊው$ ግን ሁሌም ለድንበሩ ሲል መሆኑ ነው ችግሩ$ ድንበር ለመጠበቅ ጥይት የሚጠጣው ድፍረት የተመቸ የመኖሪያ የመስሪያ አካባቢ እና ለህዝቦቿ የምትመች አገር ለመፍጠር በሚደረገው ጉዞ ላይ ለምን በንቃት አይሳተፍም$

ይሄ ሀገርን ከውጭ ጠላት የመጠበቅ ጥንካሬ ለምን ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመፍታት ረገድ አይደገምም$ ምንም የሚጠይቅ ሰው የለም በየተቋሙ የሚታገል የለም እያልኩ አደለም$ ሆኖም አብዛኛው በፍርሀት የተሸበበ በመሆኑ በድምጽ ብልጫ በሚወሰን ጉዳይ ላይ እንኳ እንዲህ አይነቶቹን ታጋዮች ለመደገፍ እስከማይችልበት ሽባ መሆኑ ነው$ ህጋዊ በሆነ መንገድ መብትን ለማስጠበቅ ካለመንቀሳቀስ በላይ ምን ሌላ ፈሪነት ይኖራል ጃል$

የሚገርመኝ ደግሞ ፊትለፊት የምንሰራበትን ተቋም የስራ ሀላፊዎች እንኳ መጋፈጥ ለመቻል የየራሳችንን ፍርሀት ሳንረታ ሁሌም የሚቀናን በቸገረን ቁጥር የትችት ካብ መከመር ነው$ እውን ትችት ሌቦችን ያጠፋል? ወይስ እውን ዘረኛ በትችት ህብረብሄራዊ አስተሳሰብ ይኖረዋል? ወይስ እውን ክፉ ቢሮክራቶች በሻይ ቤት ጥጋጥግ ወሬ ይናዳሉ?

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በየተቋሙ የሚገኙ ክፉ ቢሮክራቶች የልብ ልብ የተሰማቸው በየጥጋጥጉ ከማውራት ባለፈ የተደራጀ የተጠና እና ተከታታይነት ያለው ትግል እንደማናደርግ ማወቃቸው ነው$ ተወው ያውራ ከስብሰባ አዳራሽ ሲወጣ ይረሳውል እኮ ነው የሚሉን$ እናም ህጉ የሰጠንን መብት ተከትለን የማንንም ክብርና መብት ሳንጥስ መብታችንን ማስከበር የማን ስራ ነው የኛ ወይስ ሌቦች ሙሰኞች የምንላቸው ሰዎች

ሌላው ገጽታ ለምን መንግስት አይፈታውም የሚለው ነው$ መንግስት ችግሮችን የመፍታት እድሉ ከፍ የሚለው እንዲህ በተደራጀ መንገድ የሚታገሉ በሳል ሰራተኞች ኗሪዎች እና ባለሀብቶች ባሉበት እንጂ እኛ እንደ ዜጋ ባንቀላፋንበት ሊሆን የሚችል አደለም$ መንግስት እንዲያገለግሉን ያስቀመጣቸው ሰዎች አይደሉም እንዴ እያጠፉ ያሉት ስለሆነም ተከታትለን ቅደም ተከተሉን ጠብቀን የሚበሉንን አፎች እና የሚቧጭሩንን ጥፍሮች ማስቆረጥ ያለብን እኛው ነን$

የአድዋው መንፈስ  ይሄ ነው$ ችግርን በትችት ናዳ የመፍታት ሳይሆን ችግርን በሚፈለገው የትግል አይነት የሚፈልገውን መስዋእትነት ከፍሎ የመፍታት አቀራረብ$ ከያኔዎቹ ጀግኖች አገር የሚማረው ይህን ነው$ በቁርጠኝነት ችግሮችን መጋፈጥ በጽናት ትግሉን በድል ማጠናቀቅ$

No comments:

Post a Comment