Hiwot Emishaw በፌስቡክ በምታስኮመኩመን
ጽህፏ እንዲህ ብላ ነበር "አንዲት የተቻኮለች ሴት ልጅ አጠገቤ ስትቁነጠነጥ ግራ በመጋባት ጠየኳት የመለሰችልኝ መልስ ግን መልሼ እንድተክዝ
አደረገኝ ያን ያህል ታክሲው ቶሎ እንዲሄድ የተጣደፈችው ብታረፍድ ከዚያው ለወር ቀለብ እና ለቤት ክራይ ከማይበቃት ደሞዟ እንዳይቆረጥባት
በመስጋቷ መሆኑን ነገረችኝ" ይላል ጥቅል መንፈሱ።
ይሄ ትዝብቷ ሁላችንም ጓዳችንን መለስ ብለን እንድናይ
ኪሳችንን እንድንፈትሽ የሚያስገድድ አይነት ነው። በርግጥም የአብዛኞቻችን ኑሮ ይሄው ነው። ይሄን መልሼ ማንሳት የመረጥኩት መተከዝ
በቂ ባለመሆኑና ይህን መራራ ሀቅ ለመቀየር ማድረግ ስላለብን ቁምነገር ሀሳቤን ማጋራት በመፈለጌ ነው።
እውቁ ባለሀብት የሶፍትዌሩ ኢንጂኒየር ቢል ጌትስ
እንዳለው ደሀ ሆኖ መወለድ አይነወርም። መወለድን መምረጥ አይቻልምና። መወለድን በምንም መልኩ መወሰን የተወላጁ ፈንታ አደለምና።
ደሀ ሆኖ ማርጀትና መሞት ግን የያንዳንዳችን ምርጫ ውጤት ነው። ያ መሆኑም የሚያሰጠይቀው እኛኑ ይሆናል በዋናነት። ማለቴ ለመቀየርም
ላለመቀየርም ኳሱ በኛ ሜዳ ነው።
ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት እድሉን ካገኙት ሚሊዮኖች
መካከል በድግሪ ለመመረቅ የበቁት ጥቂቶች በቅጡ ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉ ከሆነ በርግጥም አገራችን የሚያሳፍር ኢኮኖሚ ባለቤት
ናት። እኛም ዜጎቿ በአለማቀፉ ገበያ ተወዳዳሪና አሸናፊ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ የተሳነን በመሆኑ የምናሳፍር ነን። የሚያስቆጭ
ውርደት የሚያንገበግብ ሀቅ ነው።
ኤኮሶም ሞቢል የአሜሪካው የነዳጅ ድርጅት የተጣራ
የ2012 የሶስት ወር ገቢ አሁን ባለው ምንዛሪ መንዝሬው 288 ቢሊየን ዶላር ይሆናል። ይሄ እንግዲህ ከኛ ሀገራዊ የዘንድሮ በጀት
ከመቶ ቢሊዮኖች በላይ የሚልቅ ነው። አመታዊ በጀታችን ከሶስት ወር የአንድ ትልቅ የንግድ ተቋም የተጣራ ገቢም እጅግ የሚያንስ ነው።
ተመሳሳይ ምሳሌ ብንወስድ የሳምሰንግ የተመሳሳይ
ግዜ የሶስት ወር የተጣራ ገቢ 133 ቢሊየን ብር ገዳማ ነው። ይሄ እንግዲህ በአመታዊ ትርፉ ሳምሰንግ አራት ኢትዮዽያን የሚያክሉ
አገሮች በየአመቱ ማስተዳደር ይችላል ማለት ነው።
የቢቢሲ አመታዊ የ2012 በጀት ለዚያውም በገጣማቸው
ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ ቅናሽ ተደርጎበት ወደ 96 ቢሊየን ብር ገደማ ነው። ይሄ ማለት ኢቲቪን ለሚመስለው የህዝብ ሚዲያ
60 ሚሊየን ገዳማ ህዝብ ያላት ብሪታኒያ የምትመድበው በጀት በሀገራችን የዘንደሮ በጀት ሲለካ በየሁለት አመቱ የሀገራችንን የአመት
በጀት ይሸፍናል እንደማለት ይሆናል።
ሌላ ማነጻጸርያ እንውሰድ የብሪታኒያ ማእከላዊ
መንግስት አመታዊ የትምህርት በጀት ባሁኑ ምንዛሪ ወስደነው ከ700 ቢሊየን ብር በላይ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ አመት
በጀት ስሌት የአራት አመት የኢትዮዽያን በጀት መሸፈን የሚችል ገንዘብ ለትምህርት ዘርፉ ብቻ ይመድባሉ ማለት ነው። ይሄ ቁልጭ አደርጎ
የድህነታችንን ልክ የሚያሳብቅ መረጃ ነው።
የጠቀስናቸው ካምፓኒዎችና ብሪታኒያ ሀገራችን የምትገኝበትን
የድህነት ጥልቀት የሚያመላክቱ ናቸው። እናም ማፈር መተከዝ የሚገባ ነው። ወደ እልክ እና ቁጭት ካለተቀየረ ግን አይረባንም። አስተዋጿችን
እስካላቀ አቅማችን እስካልጎለበተ እና የተሻለ ምርትና አገልግሎት መስጠት እስካልቻልን ድረስ ከዚህ መራራ ህይወት የሚያስለቅቀን
ስለማይኖር።
ከአንድ ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚከፈላቸውን የቢቢሲ
ምርጥ ጋዜጠኞች የሚመጥን ደሞዝ ለማግኘት እነሱ የሚያቀርቡትን ያክል ጥራት ያለው የሚዲያ አገልግሎት ማቅረብ እና ግዙፍ ገቢ መሰብሰብ
ይጠይቃል። እናም የማይበቃን ደሞዛችን የማያረካ አገልግሎታችን እና ምርቶቻችን ግልባጭ መልክ ነው። ገቢው የመረረውና ኑሮው ያማረረው
የኔ ቢጤ አቅሙን ሲልም ስራውን በላቀ ጥራት የመፈጸምና ራሱን ተፈላጊ የማድረግ በዚሁ ሂደት ጥቅል ሀገራዊ አቅማችንን የማሳደግ
ሀላፊነት አለበት።
እናም ከመራራው ኑሯችን ጀርባ ከደቃቁ ደሞዛችን
ጀርባ ያላደገው ብቃታችን የማያምረው አገልግሎትና ምርታችን ፊታችን ይደቀናል። ስለሆነም የምንመኘውን ኑሮ የሚመጥን ጠንካራ የስራ
ባህል እና አርኪ ውጤት መፍጠር አለብን። ያን ለማድረግ ደግሞ አቅማችን በተከታታይ መገንባት የሚሰቀል ሰርተፊኬት ለመያዝ ሳይሆን
ለደንበኛ የሚመጥን ውጤት ማቅረብ የሚያስችል ትምህርት መቅሰም ያሻል።
ስር የሰደደውን ድህነታችንን ወይም የማያረካውን
ኑሯችንን ለመቀየር ያለው መፍትሄ ከመተከዝ ከፍ ይላል። የላቀና ተከታታይ ስራም ይጠይቃል። ደቃቃ አገራዊ ኢኮኖሚ ለተመሳሳይ ሰራ
የሚከፍለው ክፍያ ከለማ ድልብ ኢኮኖሚ እጅጉኑ አናሳ መሆኑ ሁሌም ኗሪ ሀቅ ነው። ማማረር አይፈታውም ወቀሳ አይፈታውም ቁጭትም አይፈታውም።
ከቁጭት የሚመነጭ የታለመ ተከታታይ ጠንካራ ተግባር ግን በሂደት አሳምሮ ይለውጠዋል።
አብሮን የኖረው አሮጌው ድህነት በአሮጌው ተግባራችን
እንደማይፈታ በመራራው ኑሯችን አሳይቶናል። አዲስ ትጋት አዲስ አተያይ አዲስ ተግባር አዲስ እልክ ያሻናል። የምሬት መድሀኒቱ የተመረጠ
የታቀደና ተከታታይ ተግባር ብቻ ነው። አዎ በውድቀትም መሀል ነጥሮ እንደኳስ የሚነሳ የማያባራ ተግባር። ትካዜ የምን ይሻለናል መጀመርያ
ነው ትካዜ የመፍትሄው ጫፍ አደለም የሚል እምነት አለኝ።
ከትካዜ የሚመነጭ እቅድ ከትካዜ የሚመነጭ እልክ
ከዚሁ የሚንደረደር የማያሰልስ ተግባር መሰረታዊ ይሆናሉ። አለበለዚያ እስከዛሬ የኖርነውን ድህነት ገና ነገም በከፋ መልኩ እያጣጣምነው
እንቀጥላለን። ድህነት የሚበቅለው በያንዳንዳችን የተበላሸ ምርጫ በዚያው ከሚመራው ተግባር እና በዚያው ተግባር በሚታነጸው ድግግሞሽ
ወለድ ተልካሻ ልምድ ነው። ድህነት የሚከስመውም ያ ደሀ ልምድ ባለጸጋ በሆኑ ልምዶች የተተካ እንደሆነ ነው።
ሄዊ ትካዜውን እዚህ አድርሼዋለሁ አንቺ ወይም
ሌላ ሰው ደግሞ ትንሽ ፈቅ አድርጉት። ድህነትን እንግፋው ጎበዝ ይናዳል!
ይቆየን!
No comments:
Post a Comment