Tuesday, September 3, 2013

ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል- ክፍል ሁለት




ክፍል አንድ ካነሳናቸው ጉዳዩች የሚለጥቁ ራስን ማስተዳደር እንደ መለያያ ስትራቴጂ 1983 ሀገራችን የሚሉና ሌሎች ጉዳዩችን የሚዳስሰው የጹሁፉን ሁለተኛ ክፍል እነሆ

መብት እንደ ጥርጣሬ መፍጠርያ

አንዳንዶች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተከበረው ይሆነኝ ተብሎ ህዝቦችን ለማንኳሰስና በመሀላቸው ጥርጣሬ ለመፍጠር ነው የሚል ክስ ያቀርባሉ፡፡ አለመተማመኑን ኢህአዴግ የሚፈልገው ወጥና ጠንካራ ተቃውሞ እንዳይገጥመው ነው በሚል ክሱን ያጠናክራሉ፡፡ ይህ ደግሞ እድሜውን ለማራዘም ያገለግለዋል ብለው ያምናሉ፡፡


አንደኛ በተፈጥሮአዊ ባህሪያቸው እነዚህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዴት ነው አለመተማመን የሚፈጥሩት ብሎ መጠየቅን ያሻል፡፡ በየክልሉ ያሉ የተለያዩ ብሔሮች ሰሜኖች እየመሩን የሚኖሩት እኛ ራሳችንን ማስተዳደር ተስኖን ነው ወይ በሚል ቁጭት የሚንገፈገፉበትን ጉዳይ ነው የመለስው፡፡ በርግጥም ትክክል ናችሁ አዎ ራሳችሁን ማስተዳደር ትችላላችሁ ሰሜኖቹም የማስተዳደር ስራውን ለናንተ እንዲያስረክቡ ህገመንግስቱ በሚጠይቀው መሰረት ተደርጓል ነው የሚለው፡፡ ሰሜኖቹም የማስተዳደር ተፈጥሯዊ አቅምና መብት አላቸው አካባቢያቸውን በዚያው መሰረት ያስተዳድራሉ የሚል ፍትሀዊ ድንጋጌ ነው፡፡


ይሄ በርግጥም የመብቶችን በተሟላ መንገድ መከበር ይገልጻል እንጂ በምን ሚዛን ነው ጥርጣሬ በህዝቦች መካከል የሚያነግሰው፡፡ በመላው ሀገሪቱ ፍትሀዊ ነው ተብሎ ሊወስድ ቢችል እንጂ በምንም ሚዛን መጠላላት እና ጥርጣሬ የሚከስት ሆና አላገኘውም፡፡ በባህሪው ያን የማድረግ አቅም የለውም፡፡


ይልቅ ለአካባቢው ማህበረስብ የማስተዳደር ሀላፊነቱ ሲመለስ ከዚያ ቀድሞ በነበረው ግዜ በአመራር ቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች የመሪነቱን ቦታ ሲያጡ አብሮ የሚደርቅ እና የምረዳው የሚያጡት ጥቅም ይኖር ይሆናል፡፡ ያ በቤተሰብ እና በግለሰቦች አንጻር ሲመዘን ጉዳት እንዳለሁ እረዳለሁ፡፡ ግን ድንጋጌው ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር እና ነጻነት ከሚያጎናጽፋቸው መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች አኳያ ሲመዘን እዚህ ግባ የሚባል ጉዳይ አደለም፡፡ የለውጡም አላማ ይህን የመሰሉ ግለሰቦች ጥቅም ማሳጣት ሳይሆን ራሱን የመምራት ተፈጥሮአዊ ብቃት ያለውን ህዝብና ዜጋ መብት ማክብርና ማስከበር ነው፡፡


በዚህ ሂደት አማራው የተጎዳ በማስመሰል ለማቅረብ የሚሞከርበት አዝማሚያ ሌላው ነው፡፡ በጋሞ ጎፋ አርባምንጭ ተወልዶ እንዳደገ አማራ የሆነውን አውቀዋለሁ፡፡ በአመዛኙ ከሰሜን እና ከሸዋ በመጡ ሰዎች የተያዘው የሀላፊነት እና የመሪነት ቦታ በአካባቢው ተወላጆች ተወስዷል፡፡ ያ ግን በዋናነት የሚያሳየው የአካባቢው ሰው የስልጣን ባለቤት መሆኑን እንጂ ይሆነኝ ተብሎ በቀድሞዎቹ መሪዎች እና ዜጎች ላይ የደረሰን በደል አደለም፡፡


አማራውም ትግሬውም ሸዌውም በአካባቢው ራሱን የመምራት መብት እንደ ተጎናጸፈ ኁሉ ሌላውም ብሄር ራሱን የመምራት ሀላፊነትን እንደ መብትነቱ መጎናጸፉ ምንም ክፋት የለውም ብቻ ሳይሆን ተገቢና ትክክል ነው፡፡ ምን ያክል እርካታም በጋሞጎፋ ተወላጆች ዘንድ እንደፈጠረ አውቃለሁ፡፡


መተቸት ያለበት እንዲህ ያለውን ራስን የመምራት ሃላፊነት በአካባቢው በሚኖሩ ሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ላይ ጉዳት እና አድሎ ለማድረስ የሚጠቀሙበት ሀላፊዎች እና ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች የሚኖሩ ከሆነ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች እንዳይኖሩ ማድረግ የሚቻል ባይመስለኝም እንዲህ አይነት ጠባብ አመለካከታቸውን ሲተገብሩት ያለርህራሄ ማድረቅ ግን ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል- ክፍል አንድ


ባለፈው ግዜ ከነጃወር የተንሸዋረረ የማንነት እና የዜግነት ጥያቄ በመነሳት እቺ አገር ያለችበትን ሁኔታ የሚዳስስ ጽሁፍ ለማቅረብ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ በዚያው መሰረት ሀገራችን ሳትገነጣጠል ልትቆይ የሚያስችላትን አማራጭ በኔ እይታ አቅርቤዋለሁ፡ እንምከርበት እንሟገት፡፡

እንደ መግቢያ
በጥሬው ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል ማሰብና በአንድነት አጽንቶ በእድገት አልቆ ሊያስቀጥል የሚችል ስርአትና አመራር መፍጠር የተለያዩ ናቸው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የሚመርጠው መሆኑ አነጋጋሪ አደለም፡፡ አንድነት ተጠብቆ ሊዘልቅ የሚችልበትን አማራጭ በመምረጥ ረገድ ግን ልዩነቶች ይስተዋላሉ፡፡


በወሳኝነት በፖለቲካው መድረክ ከዚህ አኳያ የሚፋለሙት አስተሳሰቦች ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ ኢህአዴግ ያቀረበው ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል አማራጭ ሲሆን ሌላኛው የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀነቅኑት በብሄር ሳይሆን በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እንዲተዳደሩ የሚለው አማራጭ ነው፡፡ ይህ አማራጭ ከክልሎቹ መዋቅር እስከ ፌደራል መንግስት መዋቅር ባህርያት ድረስ ቁርጥ ያሉ አማራጮች ያበጀ አይመስልም፡፡ በግርድፉ የሚያቀርበውን ሀሳብ ግን እንየው፡፡


ጂኦግራፊያዊ የፌደራል ስርአት አማራጭ
እንደ ኢዴፓ ያሉ ይህን አማራጭ የሚያቀርቡ ፓርቲዎች ህዝብ ብሄራዊ ማንነቱ ከግምት ሳይገባ እንደ አቀማመጡ አመቺነት ወሎ ጎጃም ሲዳማ ሀረርጌ አይነት ብለን  እንደ አመቺነቱ እናስተዳድር የሚል አማራጭ አይነት ነው የሚያቀርቡት፡፡ አማራጩ በርግጥ ጥርት ባለ መልኩ ተብራርቶ ባይቀርብም እነ ልደቱን ከመሳሰሉ ፓለቲከኞች ከሰማሁት ገለጻ ተነስቼ ስናገር በጂኦግራፊ ተከፍሎ ሲያበቃ የብሄሮችን በገዛ ቋንቋቸው የመጠቀም መብት ግን ያከበራል ይላሉ፡፡


በተጨማሪም የመሪዎች ምርጫ በህዝቡ የሚካሄድ ስለሚሆን በጂኦግራፊ መከፈሉ ችግር አያመጣም ይላሉ፡፡ ይሁንና ይህ አይነቱ ውሳኔ እንደ ኦሮምያ ሶማሊያና አፋር ለመሳሰሉ በርካታ ሌሎች ብሄሮች አርኪ መልስ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ጥያቄ ዋናው የማንነት እና የእኩልነት ጥያቄ ነውና፡፡ ይህ አማራጭ አጀንዳውን ተራ የፌደራል ስርአት የመመስረት እንጂ ከማንነት ራስን ከማስተዳደርና ከእኩልነት አንጻር ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር በማስተሳሰር ያጤነው አይመስልም፡፡


እንዲያውም ይህ አይነቱ አተያይ በጠባብ ከባቢያዊ አስተሳሰብ ድጋፍ ለሚሰበስቡ ፓለቲከኞች የሚያበረታታ አጀንዳ የሚፈጥርላቸው ይመስላል፡፡ የመገንጠል አጀንዳ የሚያቀነቅኑትም ዛሬም ቢሆን ራስህን ማስተዳደር ያልተፈቀደለህ ስለማትታመን ነው ዛሬም መብትህ አልተከበረም በሚል ዝማሬ ለማነሳሳት ይጠቀሙበታል፡፡ በጣም ቢዳከሙም ዛሬም መሰል የመገንጠል አስተሳሰቦች የራስ አስተዳደር በተከበረበትም ሲራመዱ የምንታዘበው ይህን የህዝቡን ፍላጎት ጠምዞ ለአጀንዳቸው ለማዋል ታስቦ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

መፍትሄ ፈብራኪ ወይስ ወቀሳ ጠማቂ


ነጻ የወጣ ህሊናና ህዝብ አብይ ተግባር ኢኮኖሚያቸውን መቀየር ነው፡፡ ዲትሮይቶቹን እና ሲሊካን ቫሊዎቻቸውን ማነጽ፡፡ ነጻነታቸው ከሚያስጀምሯቸው ሁነኛ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ኢኮኖሚያዊ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ነጻነትም አብይ ፋይዳ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት መቻሉ ነው፡፡ የህዝብ አብይ ጥያቄዎች ዞሮ ዞሮ ኢኮኖሚያዊ ናቸውና በተለይ እንደኛ ባለ ደሀ ሀገር፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎችም አብይ ፋይዳ ኢኮኖሚያዊ ነጻነቶችን ማረጋገጥ መቻል መሆኑ ይታወቃል፡፡


ኢኮኖሚውን ማንደርደር ወይስ ፓለቲካውን ማንተክተክ
በብዙ መልኩ ሲመዘን የኛ ሀገር ፖለቲካ ያለበት ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩችን ወደፊት በመግፋት ላይ የሚያተኩር ሳይሆን በመብት ላይ የተንጠለጠለ ከመብትም ደግሞ በተሟላ መንገድ ያሉ ጭብጦች ላይ ሳይሆን በየወቅቱ ከሚወጡ ደንቦችና ህጎች ውስጥ በተወሰኑ ለወቀሳ ያመቻሉ በሚባሉ በወጉ ባልተላመጡ ጉዳዩች ላይ ተንተርሶ ገዢውን ፓርቲ ለማጣጣል ከመሞከር ባለፈ በሀራችን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውን በወጉ በተጠኑ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙርያ የማያደራጁ በየወቅቱ በሚኖሩ ክርክሮች ላይ ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ በድክመትም ቢሆን እያነሱ ሲያስተዋውቁ የሚውሉት ኢህአዴግን  የሆነብት ሁኔታ ነው ያለው፡፡


በዚህ ሂደት የፖለቲካውን ሙቀት ከመጨመር በዘለለ ምናልባትም በተወሰኑ ጉዳዩች ላይ ገዢውን ፓርቲ ከማብጠልጠል ባለፈ በሀገሪቱ ወሳኝ ስለሆነው የኢኮኖሚ እድገት ወዴትነት እንዴትነት በምን አማራጭ ሊያድግ እንደሚችል በማመላከት ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ግብአት እስከማይኖራቸው ደርሰዋል፡፡


በዚህ የተነሳ በኢኮኖሚው ላይ ፓርቲዎቹ የሚሰጡት ትንታኔ ግለሰቦች ከሚሰጡት የአሉባልታ ትንታኔ የተሻለ ብስለት የማይታይበት እና ወትሮም ገዢው ፓርቲ እያሳደገው ያለውን ኢኮኖሚ እንዴት በላቀ የእድገት ምጣኔ እንደሚያሳድጉት ሊያመላክቱን ቀርቶ አሁን ባለውም ቁመናው እንዴት እንደተደራጀ ምን ለውጥ እያስገኘና ምን እጥረቶች እየፈተኑት እንዳሉ እንኳ በወጉ የማይገነዘቡ ፓርቲዎች የተጠራቀሙበት ምህዳር በመሆን ቀጥሏል፡፡


ይሄ የሆነው እና እየሆነ የቀጠለው ተቃዋሚዎቹ ወደ ፖለቲካው ጎራ ከተፍ የሚሉት አንድም በፖለቲካ ፓርቲ መሰባሰብ ያስገኛል የሚሉትን ጥቅም ለመቀራመት በሌላም ይህ ካልሆነ ደግሞ ኢህአዴግን በሚረባም በማይረባም ጉዳይ ስለሚጠሉት ብቻ ይሆንና ተቃውሞ የጥላቻ መልእክት ከመቀመር እና አቤቱታ ከመዘመር የተሻለ ቁምነገር የሌለው ሆኖ ያርፋል፡፡ ለዚህ ነው የሀገራችን የተቃዉሞ ፖለቲካ ከአቤቱታ ከፍ የሚል ሚና መጫወት የተሳነው፡፡

እዚህ አገር ብዙ ችግር አለ




አዎ እዚህ አገር ችግር አለ፡፡ ችግሩን ደግሞ በየእለቱ በየሰአቱ በየደቂቃው እየኖርነው ነው፡፡ በአንድ በኩል የመሰረተ ልማት እጦቱ መሰረተ ልማቱ ሲኖርም በአግባቡ አለመስራቱ የሚፈጥርብንን ምሬትና ጉዳት በሌላ በኩል በየለቱ የሚሞቱት ሕጻናት እና እናቶች በየግዜው መመገብ ያልቻልናቸው ነገሮችና ልናገኝ ያልቻልነው የህክምና አገልግሎት የበለጠ ያሳምመናል በቀላሉ፡፡ ልናገኝ ስንችል ያላገኘነው መንግስታዊም ግለሰባዊም አገልግሎት ይጎዳናል ያስመርረናልም፡፡


ቁምነገሩ ግን እንደማንኛውም አንድ ግለሰብ ማማረርና የችግር አለ ትርክት ማሳመርና ማስዋብ አደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በፖለቲካውና በኢኮኖሚው በንቃት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሁነኛ ሀላፊነት የችግሩን ምንጭ በአስተማማኝ ጥናት መለየት ምንጮቻቸው ለታወቁ ችግሮች ተገማች እና ሳይንሳዊ መፍትሄ መቀመር እና ይሄው መፍትሄ ተተግብሮ እሚፈለገው ለውጥ እንዲገኝ ማድረግ ነው፡፡


ከመደበኛው ማህበረሰብ እኩል ችግር አለ እያሉ ለማስተጋባት ከሆነ በፓርቲ ደረጃ የምንሰባሰበው ይሄ ፋይዳ የለውም፡፡ መሰባሰብ እንደ ፓርቲ መቆም የፖለቲካ አጀንዳ ነድፎ መንቀሳቀስ ጠቃሚ የሚሆነው መደበኛው ግለሰብ አጥንቶ ሊደርስባቸው የማይችላቸውን ጉዳዩች በተደራጀ መልኩ አከናውኖ ችግሮች የሚፈቱበትን አግባብ የሚቀመር ከሆነ እንጂ ከመደበኛው ግለሰብ እኩል ችግር አለ ለማለትማ በፓርቲ ደረጃ መሰባሰብ አያስፈልግም፡፡ ያንማ ሰለማዊ ሰለፈኛም ያደርገዋል፡፡ ቁምነገሩ መፍትሄውን አፈላልጎ ማግኘት በዚያ ዙርያ ድጋፍ አሰባበስቦ ሕዝብን አሳምኖ ምርጫ ማሸነፍና የመሪነቱን ሚና ተቀብሎ ሕዝብ ይገባዋል የምንለውን ጥቅም ማሳካት መቻል ነው፡፡


በምን ስሌት ነው ችግር አለ ብሎ የምናውቀውን ችግር ስለተረከልን አንድን የፖለቲካ ድርጅት ሀገር የመምራት ሀላፊነት የምንሰጠው፡፡ ጥያቄው የመፍትሄ እንጂ የችግሮች መኖርን ክሽን ባለ ቋንቋ የማቅረብ ያለማቅረብ ጉዳይ አደለም፡፡ ችግር እንዳለ ኑሯችንን ጠቅሰው አስረዱን እንበል ይሄን ማድረጋቸው የሚባለውን ችግር የመፍታት ሁነኛ መነሻውን የመለየት እና የተበጀውን መፍትሄ የመተግበርና የማስተግበር ድርጅታዊ አቅማቸውንና አቋማቸውን ሊያሰየን ይችላል እንዴ? አይችልም፡፡ የፓርቲ ሁነኛ አላማም ህዝብ የሚማረርበትን ችግርና አሁን ካለው ቁመና አንጻር ወደፊት ሊገጥሙት የሚችሉትን ተገማች ተግዳሮቶች በመተለም ችግር የሚፈታና ሀብት መፍጠር የሚችል አመራር መስጠትና ማስተግብር እንጂ ችግር ተራኪ ድምጽ መሆን አደለም፡፡

የፖለቲካ ሀላፊነት እንደ ችግር መፍቻ ቃልኪዳን




አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለህዝብና ለደጋፊዎቹ የሚገባው ቃልኪዳን ለውጥ ነው፡፡ በተገማች እና በሳይንሳዊ ዘዴዎች መመላከት ማሳመን ማነሳሳት የሚችሉ የለውጥ ቃልኪዳኖች፡፡ እንዲህ ያለ ቃልኪዳን መግባት ደግሞ አላማ ይጠይቃል፡፡ ሀገር የመለወጥ አላማ፡፡ ሀገር ለመለወጥ የተነሳሳ በዚያው አላማ ዙርያ መሸ ጠባ ሊተጋ ይገባል፡፡ ይህን በመሰለ አላማ ዙርያ የማይሰራ ያን ማሳካት የሚችሉ ጥቅል ፍልስፍናዎች ከዚያ የሚቀዱ የረጅም ግዜ የመካከለኛና የአጭር ግዜ እቅዶች ነድፎ በነዚያ ዙርያ ህዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው የማይተጋ ፓርቲ የሚቀረው መንጠልጠያ ትችት ብቻ ነው፡፡ ትችት ጌጡ ሆኖ የሚያርፈው እንዲህ አይነት ትልም የሌለው ፓርቲ ነው፡፡


ይሄን መሰሉ የፓርቲ ቁመና የጠራ አላማ እና ከአላማ ለአፍታም ቢሆን አይንን አለመንቀል ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ባለ ትኩረት የሚሰራ ቡድን በርካታ የሚያቅዳቸው የሚያነሳ የሚጥላቸው ጉዳዩች ስለሚኖሩት ስለራሱ በማውራት የራሱን ፕሮግራም በማነጻጸር ይጠመዳል፡፡ የሌሎቹን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አማራጮች አዋጭ አለመሆን የሚያነሳው አማራጩን ሲያስተጋባ በማሳያነት ወይም በማነጻጸሪያነት ሲያነሳው እንጂ ነጋ ጠባ ስለባላንጣው ሲያወራ የሚከርምበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡


ስለ ባላንጣቸው በማውራት የሚጠመዱ ፓርቲዎች ዋነኛ ችግር ስለባላንጣቸው ያላቸው የከፋ ጥላቻ አደለም፡፡ ትልቁ ችግር ለሀገራቸው የሚያቀርቡት አማራጭ ራእይ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ አጀንዳ ያለው ቡድን ስለሌሎች ለማውራት ግዜ አይኖረውም፡፡ በሚያገኛት የተወሰነች የሚዲያ አጋጣሚ የፓርቲዉን መልእክት በማስተላለፍ ስራ ላይ ብቻ ይጠመዳል፡፡ በተቃራኒው ላይ የሚያተኩር ቡድን ውድቀት እንደ ፓርቲ የሚታገልበት ጥርት ያለ አላማ እና የተተነተነ እቅድ አለመኖር ነው፡፡