Thursday, May 16, 2013

ገለልተኛውን ጋዜጠኛና ሚድያ ፍለጋ

አንዳንድ ወዳጆቻችን ሚድያና ጋዜጠኛ አቋም የለሽ ገለልተኛ መሆን አለባቸው አቋምም ይኖራቸው ከሆነ ገለልተኝነታቸው መሆን አለበት የሚል ትርክትና እምነት አላቸው$ አለማቀፍ ተሞክሮው የሚመሰክረው ግን የተለየ ነው$ ብዙ መዘባረቅ ሳያስፈልግ ስመጥሮቹን አለማቀፍ ሚዲያዎች እነ ቢቢሲ አልጀዚራ እና ፍራንስ 24 ብንወስድ ጥቅል የአጀንዳ መረጣቸውና የሚያስተላልፉት መልእክት የየተፈጠሩባቸውን ሀገሮች አላማና የሚከተሉትን የፖለቲካ እምነት የተከተለ ስለመሆኑ አያወያይም$

በቅርቡ የተፈጠረውንና እስካሁንም ያልበረደውን የአረቡን አለም የጸደይ አመጽ አዘጋገባቸውን ብናስተውል ሚድያዎቹ የሚያሰራት ዜና ከሀገሮቻቸው ፖለቲካዊ ጥቅም አንጻር ስለመቃኘቱ የሚያወላዳ ነገር የለውም$ በቱኒዚያና በግብጽ የነበረውን አመጽና ያን ለማስቆም በወቅቱ የነበሩ የሀገሮቹ መሪዎች የሚፈጽሙትን ግድያ ቢቢሲም ይሁን የአሜሪካውያኑ ሚድያዎች ሲያቀጣጥሉት አልነበረም$ ይሄ የሆነው በሁለቱ ሀገሮች መሪዎች የነበሩት ግለሰቦች የምእራባውያኑ ወዳጆች በመሆናቸው ነው$ ሚዲያዎቹ የመንግስቶቻቸውን ወይም የሀገሮቻቸውን አቋም ተከትለው ሲዘምሩ ነበር$ ገለልተኛ አልነበሩም መሆንም አይችሉም$ ሲጀመር ለጽድቅ አልተቋቋሙም ለጥቅም እንጂ$

በዚያው ተመሳሳይ አመጽ ላይ የኳታሩ አልጀዚራ የነበረው ሚና ቀድመን ከጠቀስናቸው ሚድያዎች የተለየ ነበር$ አመጹ የተለየ ስለነበረ ሳይሆን ኳታር የተለየ አላማ ያላት በመሆኑ አልጀዚራም ያን የኳታር የተለየ አላማ ማስፈጸም በሚችልበት አንግል መስራት ነበረበት$ ኳታር በአረቡ አለምም ይሁን በክፍለ አህጉሩ ተጽእኖዋን ማሳደግ የምትሻ በመሆኑ ግዙፏን ግብጽን የሚያዳክም አማራጭ ሲገኝ ያንን በማቀጣጠል ማትፈር ትፈልጋለች$

በመሆኑም የቱኒዚያውንም ይሁን የግብጹን አመጽ አንዳንዴ ከሚድያ ስነምግባርም ውጪ በሆነ መንገድ ዘግናኝ ፊልሞችንና ስእሎችን ጭምር በአረብኛውም በእንግሊዘኛውም ቻናል በመልቀቅ የጸደዩን አመጽ አልጀዚራ ቤንዚን አርከፍክፎበታል$ አልጀዚራ የኳታርን መንግስት ሁለቱን መንግስታት ገፍቶ የመጣል አላማ ለማሳካት በተደራጀ መልኩ ማስኗል$ የሚድያው ሚና የኳታርን በቀጠናው የበላይ የመሆን ፍላጎት የሚመግብ እና ይህንኑ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት አንድ አካል ነው$ ገለልተኛውን ሚድያ እዚህም አናየውም$

ቢቢሲ ፍራንስ 24 እና አልጀዚራ ከየሀገራቸው ጥቅም አንጻር የቱኒዚያውን እና የግብጹን አመጽ በመዘገብ ስራቸውን አገባደዱ ቀጠሉና በተባበረ ክንድ ድሮም የማይዋጥላቸውን የሊቢያውን ጋዳፊን የየሀገራቸውን መንግስታት ተልእኮ በመቀበል የአመጽ ጥሪውን ከውጭ አቀጣጠሉበት$ እነ ሆስኒ ሙባረክን የወሰደው ማእበል እሱንም በአጋጣሚው አብሮ እንዲጠርገው$ እነዚህ ሚዲያዎች በሊቢያ ወታደሮች በኩል የምትደረገውን እያንዳንዷን ጉዳይ ሲዘግቡ ከአማጽያኑ ጋር ተቀላቅለው የሊቢያ ወታደሮችን ይወጉ ስለነበሩ ወታደሮቻቸውና ሀገሮቻቸው ስለሚያቀርቡት የመሳርያ አቅርቦት ትንፍሽ አይሉም ነበር$

በተመሳሳይ መልኩ በባህሬን እና በየመን የነበረውን ሁኔታ ግን ፈጽሞ በተለየ አግባብ ነው የዘገቡት$ በየመን የአሸባሪ ስጋት ስላለ በቋፍ ያለውን መንግስት መደገፍ እንጂ ማዋደቅ አልመረጡም$ ሚዲያውም በዚያው መልኩ ሄድ መጣ የሚል የየሀገሮቹን የሸምጋይነት ሚና ከመጫወት ባለፈ ስለሰባዊ መብትና ስለነፍስ ግድያ በግብጽ በቱኒዚያና በሊቢያ ለተለያየ አላማ ሲያራግበው የነበረው አጀንዳ እዚህ ጋ ጠፍቶት አደለም$ የሀገሮቹን ጥቅም የሚያስጠብቀውን አማራጭ በመከተል ነው ዝምታን የመረጠው$

ባህሬን ያ ሁሉ ሰው ሲገደል ያን ያክል ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ የወፍ ነፍስ ስለነበር አደለም ለደን ቢራቢሮ ነፍስ ሁሉ ተቆርቋሪ ነን የሚሉት ምእራባውያንና ሚዲያቸው ማዳፈንን አማራጭ ያደረጉት$ ይልቁንም ሊያዳክሙት የሚፈልጉትን የሺአ ሙስሊም ይዞታ ለመስበር እንጂ$ ሳውዲ ጦሯን የላከችው የባህሬን ሰላም አሳስቧት ሳይሆን በባህሬን አናሳ የሆነው ሱኒ ስልጣን መነጠቅ በሳውዲ ነዳጅ አምራች አካባቢ ለሚገኘው የሳውዲ ሺአ ቢንዚን እንደሚሆን በመረዳታቸው ነው$ ይህን መሰሉ ሁኔታ ደግሞ ኢራን የሱኒውን ቀጠና ለማዳከም ያላትን ፍላጎት እንደሚመግበው በማወቃቸው ነው የዴሞክራሲ መዘምራኑም የነሱ አፎች የሆኑት ሚድያዎቻቸውም ዝምታን የመረጡት$

የሶርያውን ጉዳይ ከወዲያ ወዲህ የሚያቀጣጥሉት የምእራቡ ሚድያዎች በዩርዳኖስ እና በባህሬን ያለውን ሁኔታ ግን ይደብቁናል$ ቢዘግቡትም አላሉም እንዳይባሉ ያክል ነካ ለማድረግ ታክል ነው$ እንዲያውም የባህሬኑን ጉዳይ ከመኪና ውድድር መካሄድ አለበት የለበትም የሚል ለበጣ ጋር እያያዙ ያቀርቡበት የነበረው መንገድ ሚድያዎቹ ምንያክል የተጠኑ ስራዎች እንደሚሰሩ ያመላክታል$ ታዲያ የምንናፍቀው ገለልተኛው ሚድያና ጋዜጠኝነት ምን ውሀ በላው?

የቻይናውን ኦሊምፒክስ ዝግጅት በየምክንያቱ ሲያጣጥል የነበረው ቢቢሲ ያን ያደርግ የነበረው የቻይና ታላቅነት እንዳይደነቅ እና እንዳይወሰድ በማድረግ ምእራቡ አለም ያለውን ተጽእኖ ለማስጠበቅ መሆኑ አይሳትም$ አንዴ የሰብአዊ መብት ሌላ ግዜ የአየር ብክለት ጉዳይ በማንሳት የቻይናን መጥፎ ገጽታ ለማጉላት ያላሰለሰ ሚና ተጫውቷል$ ይህም ከሀገሩ ጥቅም አንጻር የሚያደርገው ነው$ ሚዛን የሚደፋው የቻይና ገጽታ ያ ሆኖ አደለም$

በተቃራኒው በለንደን ኦሊምፒክስ ወቅት ቢቢሲ ሁነኛ ቃል አቀባይ በመሆን ለንደን ኮሊንግ ወይም ለንደን ትጣራለች በሚል ዜማ በየደቂቃው የሚወቀር መልእክት ቀርጾ የለንደንን ተጎብኚ ቦታዎች አጠር ባሉ ፕሮግራሞች እያስተዋወቀ ነው የሰነበተው$ ሀገራዊ ጥቅም ነው$ ገለልተኛ የሚባል ነገር የለም$

በሌላ ገጽታ ደግሞ ፕሬስ ኒውስን ብንመለከተው የኢራንን አላማዎች ማሳካት በሚችል መልኩ የተቀረጸ ነው$ ከምእራባውያኑ ከተሞች ለፕሬስኒውስ የሚሰሩት ግለሰቦች የምእራቡ ስርአት ተቃዋሚ የሆኑና ያን የሚያጣጥሉ መሆኑን ማንም መታዘብ ይችላል$ በተመሳሳይ እነ ሲሲቲቪና ሺንዋ ደግሞ የቻይናን በሀገሮች ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አካሄድ ተከትለው ነው መልእክቶቻቸውን የሚቀርጹትና የሚያስተላልፉት$ ሁሉም የሚያሳካት ሀገራዊ አጀንዳ አላቸው$

እንዲያውም በባሰ መልኩ የአሜሪካ ሚድያዎች በፓርቲ ዙርያ ተከፋፍለው የሚሰሩ ናቸው$ በአዋጅ ፕሮሪፐብሊካን ወይም ፕሮዴሞክራቲክ ፓርቲ አቋም ነድፈው$ ፎክስ ኒውስ ለይቶለት የሪፐብሊካኑ ሁነኛ አቀንቃኝና አፈቀላጤ ነው$ እንደ ኤቢሲ ሲቢኤስ እና የመሳሰሉት ሊብራል በመሆናቸው ዴሞክራቲክ ፓርቲውን ይደግፋሉ$ MSNBC እንዲያውም የለየለት የዴሞክራቲክ ፓርቲው ደጋፊ ነው$ ብዙዎቹ ጸሀፊዎችም የሚታወቅ የፖለቲካ ወገንተኝነት ያላቸው ሲሆን ብቃታቸውና ሚዛናዊነታቸው የሚመዘነው በሚያቀርቡት መረጃ ብስለት እና አዋጭነት ነው$

ፈጽሞ ያለአላማ የሚፈጠር ሚዲያ የለም አንድም የተፈጠረበትን መንግስትና ህዝብ አለያም ያቋቋሙትን ባለሀብቶች ጥቅም ማስጠበቅ ሁነኛ ስራው ነው$ ለዚህ እኮ ነው የኒውዮርክ ታይምስ የረጅም ግዜ ዋና አዘጋጅ የነበረው ግለሰብ ኮርፖሬት ሚዲያውን የሚያገለግለውን ጋዜጠኝነት ባለሀብት በፈለገ መጠንና ግዜ ያሻውን ነገር የሚያሰራው ሞያዊ ሽርሙጥና ነው ብሎ የገለጸው$ ሚዲያው የሚመራው ኮርፖሬት ወይም ፖለቲካዊ አጀንዳ ስለመኖሩ የሚጠራጠር ሰው የዋህ ነው$ እንዲያውም እንዲያ የሚያስብ አመለካከት ሞኛሞኝ ነው ሊባል ይችላል$

መልእከቴ አጭር ነው ሲያሻን ወደ ምስራቅ ሲያሻን ወደ ምእራብ ብናይ ጥቅም የማይመራው የተቀረጸ የፖለቲካና የኮርፖሬት ጥቅም የማያራምድ ሚዲድያና ጋዜጠኛ አለመኖሩን ማብሰር$ ቁምነገሩ ይህው እያለ በጨዋ ደንብ በድፍረት በመረጃ የሚያምኑበትን ጉዳይ ለሀገር እና ህዝብ በሚጠቅም መልኩ ማራመዱ ነው$

ገለልተኛ የሚባል ጋዜጠኛም ገለልተኛ የሚባል ሚዲያም የለም$ እንዲያ የሚመሰክር ካለም እየዋሸ ነው ወይም እውነታውን አያውቀውም$ ይቆየን$

1 comment: