Wednesday, August 28, 2013

እውን ኤርትራን ማን አንገት አደረጋት?

ኤርትራ ክብር የሚገባቸው ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ የራሷን ጉዳይ በራሷ መወሰን ያለባት ሀገር መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ ሲያበቃ አንገት የሚያደርጋት ቁመና ያላት ግን አደለችም፡፡ ወደብም ኤርትራን አንገት አያደርጋትም፡፡ ምናልባት አንገት ትሆን የነበረው ኢትዮጵያውያን ከአሰብ ወደብ ብቻ ተቆፍሮ በሚወጣ ተአምረኛ ቁሳቁስ የምንኖር ቢሆን ነበር፡፡ 

ካልሆነ ግን ወደብ በሚታወቀው የገቢና የወጪ እቃ ማስተላለፊያነቱ ከተመዘነ ኤርትራ በማንኛውም ሚዛን አንገት አደለችም፡፡ ልትሆንም አትችልም፡፡
 
እንዲያውም ከሸቀጥ አንጻር ከታየ አንገት መባል የነበረባት ወደብ አልባዋ ኢትዩጵያ ናት፡፡ ኤርትራ በማታመርታቸው ጥሬ እቃዎች ጥሩ ላኪ አገር ሆና የነበረውም ከጦርነቱ በፊት ይህን ሀብታችንን ከኛ ገዝታ በመውሰድ ታቀርብ የነበረ በመሆኑ  እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ ጉዳዩ ከህዝቦች መብት አንጻር መታየቱ ከቀረ በሚል ያመጣሁት ንጽጽር እንጂ የሁለቱ ህዝቦች ጉዳይ ከሀብት አንጻር መመዘን አለበት ብዬ አላምንም፡፡
 
ወደቡን ስላጣነው ማጣጣል አለብን ብዬም አላምንም፡፡ ወደብ ራሱን የቻለ አስፈላጊነት እንዳለው አልዘነጋም፡፡ ለወደብ ሲባል ግን ወጣቱ እየታፈሰ ለጦርነት ሲማገድ መክረም አለበት የሚል ደካማ አማራጭም አልወስድም፡፡ ወደብ ዛሬ ባለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሲመዘን የሚኖረው ተጽእኖ ወደብ ወይም ሞት የሚያሰኝ አደለም፡፡
 
በተለያዩ ግዜያት ወደብ አልባ በሆኑ አስራ ስድስት የአፍሪካና 31 አለማቀፍ ደሀ አገሮች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው ወደብ አልባ አገሮች ወደብ ካላቸው አገሮች ጋር ሲነጻጸር ከትራንስፓርት እና ተያያዥ ወጪዎች አኳያ 50 በመቶ ከፍ ያለ ወጪ ለማውጣት ይዳረጋሉ፡፡

አንዳንድ ጥናቶችም ወደብ አልባ አገሮች ወደብ አልባ በመሆናቸው ብቻ አመታዊ ኢኮኖሚያ እድገታቸወ 0.5 በመቶ ድረስ የእድገት ምጣኔ ቅናሽ እንደሚያሳዩ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ግን በደሀ ወደብ አልባ አገሮች ሁኔታ አኳያ እንጂ ወደብ አልባነት ከዚህ ጋር የግድ የሚያቆራኝ ሆኖ አደለም፡፡

አንደኛ እነዚህ ደሀ ወደብ አልባ ሀገራት በደሀ ባለወደብ ሀገራት አጎራባችነት ያሉ በመሆኑ ያልዳበረ መጓጓዣ እና ትራዚት አገልግሎት ስላላቸው ወደብ አልባውንም አገር ራሳቸውንም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችል ቁመና ላይ የማይገኙ በመሆኑ ነው፡፡  

ወደብ አልባ ሆነው ሲያበቁ የርስ በርሱ ንግድ ልውውጥ በተጠናከረበት እና የትራንስፓርት ዘርፉ ባደገበት አካባቢ ያሉ እንደ ኦስትርያ ስዊዘርላንድ እና ቤልጂየም ያሉ አገሮች ምን ያክል መልማት እና የበለጸጉ ሀገሮች መሆን እንደቻሉ የምንታዘበው ነው፡፡
እነዚህ አገሮች ሸቀጥ ለማስገባት የግድ ወደባህር በር የማያዩበት ከበለጸጉት ጎረቤቶቻቸው የሚገበያዩበት የወጪ ንግዳቸውንም ወደብ በወሳኝነት ሳያስፈልግ ለጎረቤቶቻቸው የሚያቀርቡበት ሁኔታ ስላለ ለኛ ወጥመድ የሆኑ ሁኔታዎች ለነሱ እምብዛም ቁምነገራቸው ያልሆነበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 

የኛ ከባቢያዊ ሁኔታ ከዚህ አኳያ ያለውን በጎ ያልሆነ ተጽእኖ እንገነዘባለን፡፡ ለዚያ ነው ኢህአዴግ ጎረቤቶቻችን እንደ አቅም እንጂ እንደ ጠላት የማይፈርጀው፡፡ የሱማሌ የሱዳንና ሌሎች ከባቢያዊ ሁኔታዎችንና አህጉራዊ ሁኔታዎችን በትኩረት ኢህአዴግ የሚተጋባቸው የአህጉሪቱ ማደግ የኢትዩጵያ ማደግ የከባቢው መለወጥ የኢትዩጵያ ለውጥ መሆኑን በመረዳት ነው፡፡

በመሆኑም ከነዚ መነሻዎች ተነስተን ስንቃኝ ኤርትራ ለኢትዮጵያ አንገት የምትሆንበት ቤሳቢስቲን ተጨባጭ ማስረጃ የለም፡፡ ለኔ ወጣትን ለጦርነት ሲማግዱ ከመኖር የግድ የሚል ከሆነ 0.5 አመታዊ የእድገት ምጣኔያችንን ቀርቶብን በሰላም መኖራችን ሁነኛውም መለኛውም አማራጭ ነው፡፡ ይሄ ማለት ኢትዩጵያና ኤርትራ አንድ ሊሆኑ የሚችሉበት እድል ካለ ባፍጢሙ ይደፋ ማለት አደለም፡፡ ግን የሚሆነው በመግባባት እና በመተማመን ነው፡፡ በአንገትና በበድን የሰከረ አተያይ የሚመራ ፖለቲካ ለዚህ መሰሉ ስክነት የታደለ አደለም፡፡

ኢህአዴግ በለጋ እድሜው ይህን አማራጭ ተረድቶ ማቅረብና ማስተግበሩም በለጋ እድሜው የፈጸመው ሁሌም የሚታወስ በሳል እና ትልቅ አበርክቶው እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ከወንበሬ ብድግ ብዬ ለዚያኔዎቹ ወጣቶች ለአሁኖቹ ጎልማሶች አድናቆቴን እገልጻለኁ፡፡ በርግጥም ኤርትራ አንገት አልነበረችም ዛሬም ወደፊትም አንገታችን አትሆንም፡፡  

አሰብም እንደ ወደብ እንደ ወርቅ እየተቆረጠ የሚሸጥ ጸጋ አደለም፡፡ አገልግሎት ሲሰጥ ብቻ ነው ሀብት የሚሆነው፡፡ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለው ደግሞ ለኛ ብቻ ነው፡፡ እኛ ስንጠቀመው ለኤርትራውያኑ ግዙፍ ገቢ ይሆናል ትንሽ ቁጥር ያለው ህዝብ ከመሆናቸው አንጻር ትልቋ አገር የሚኖራት ትልቅ የወጪና የገቢ ንግድ የሚያስገኘው ዳጎስ ያለ ገቢ ስለሚኖር፡፡ እንዲያውም ኤርትራ በአካባቢው ተመሳሳዩን አገልግሎት ሊያቀርቡ የሚችሉ በርካታ ሀገሮች መኖራቸውን ተረድታ የተሻለ አገልግሎት ለመስጥትና ተመራጭ ወደብ ለመሆን ተፍ ተፍ ማለት ነበረባት፡፡
 
ለአንድ አገር አንገት የሚሆን ሚና ሊሆን የሚችለው የራሱ መንግስት የአመራር ሚናና የህዝቡ ተነሳሽነት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ነው የአንገትነት ታፔላ የተለጠፈላት ሀገርም ከሄደች በኋላ እቺ አገር በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡት ቻይናና ሕንድ ተርታ መግባት የቻለችው፡፡ አንገታችን ወዴት ነሽ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ 

አንገታችን ልማታዊ ስራዎቻችን ላይ ያነጣጠረ ትጉህ መንግስት ትጉህ ፓርቲና ትጉህ ህዝብ እንጂ ኖረንም ቀረም ወደብ አደለም፡፡ ወደብ ቢኖረው እሚጠላ የለም ኖረም ቀረም ግን የህዝቡን እና የመሪ ድርጅቶችን አይተኬ ሚና ለወደብ በመስጠት ራሳችንን አሳንሰን ልናይ አንችልም፡፡ ብናደርገውም ስህተት ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡

ኤርትራ በኤርትራውያን ውሳኔ አንድ ሆና ብትኖር የሚጠላ ያለ አይመሰለኝም፡፡ ቢሆን ደስተኛ ከሚሆኑት መካከል ኢህአዴግ አንዱ አንደሚሆን አምናለሁ፡፡ አንገት በሚል መንፈስ ግን አደለም፡፡ አንድ ሆኖ ለረጅም ግዜ እንደኖረ ህዝብና አብሮ መኖሩ ለሁለቱም ህዝቦች የሚያስገኘው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ስለሚኖረው ነው፡፡

ሁኔታ እንዳይፈጠር የተበላሸ ሚና የነበረው ደግሞ ዛሬም ትላንትም ኤርትራን እንደ አንገት የሚያየው የተቃውሞ ቡድን ነው፡፡ በዚህ በሰከረ ተመሳሳይ ስሌት ሲነዳ የነበረው ሻብያ ወደቡ የግመል ማጠጫ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው በተግባር ሲረዳ ደግሞ የገባበት አዘቅት አካባቢውን በማተራመስ ኢትዮጵያን የኤርትራ ብቻ ደምበኛ አድርጎ የማቆየት አዝማሚያ ነው፡፡ በሶማሌ ያሰገባው እጅ ከጂቡቲ ጋር በድንበር ስም ሊፈጥረው የሞከረው ቀውስ በሱዳን በኩል ሊፈጥር የሚሞክረው ቀውስ ተዳምረው ሲታዩ  እውነታውን ትቶ ራሱን እንደ አንገት ሲቆጥር የነበረው ሻብያ ከገጠመው ራሱን አልቆ የማየት ውርደት ለመውጣት የሚደርገውን መፍጨርጨር ነው፡፡  

ኤርትራ የሆነችውን እንጂ ያልሆነችውን ሆና በመታየት በኢትዮጵያ ላይ ልታደርስ የምትችለው ተጽእኖ አይኖርም፡፡ በመሆኑም ኤርትራ አንገት አደለችም ብቻ ሳይሆን ይሄ የወደብ አገልግሎት አቅርቦት ስራዋም በርካታ ተፎካካሪዎች ያሉበት በመሆኑ የተሻለ አገልግሎት በማቅረብ ከፍ ያለ ገቢ ለማግኘተ ቀና ደፋ የሚጠብቃት ሀገር ጭምር ናት ማለት ነው፡፡ በየትኛውም መስፈርት አካባቢውን በማመስ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የምትሰራውም ስራ ኢትዮጵያ ልትቆጣጠረው እማትችለው አይሆንም፡፡
 
በመሆኑም አንገት ተብላ የምትቀርበው ኤርትራም አንገት አደለችም ኤርትራን አንደ አንገት የሚያቀርቡልንም ያለኛ ለአገርና አንድነት አሳቢ የለም የሚሉንም ፖለቲከኞችም ለራሳቸው ከሚሰጡት ግምት በተቃራኒ የአገራችንን ፖለቲካና መፍትሄዎቹን በቅጡ ያልተገነዘቡ ናቸው፡፡ አገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች በውል ያልተረዱ በመሆኑም መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ፖለቲካዊ መፍትሄም ሊያቀርቡ የማይችሉ ሀይሎች ሀገሬ ሀገሬ ስላሉ ብቻ ራሳቸውን ጥሩ ፖለቲከኛ አድርገው ያዩበት እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህም መሰሉን የተሳሳተ ግንዛቤያቸውን ባለፉት 20 አመታት በላይ ሊያርሙት ያልቻሉ መሆኑ ደግሞ ከስህተታቸው ለመማር ይቅርና የለም ተሳስተናል ለማለት ያላቸውን ደካማ ስነምግባር የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ቁመና ሀገር የመምራት ሀላፊነት መረከብ ቀርቶ ለመረከብ ማሰብ በራሱ የሀገሪቱን ህዝቦች ህሊናዊ ብቃትና የምዘና አቅም መናቅ ይመስለኛል፡፡

ወደብን ወሳኝ ጉዳይ አይደለም ብሎ ስለተረዳ ብቻ ሳይሆን ለህዝቦች ውሳኔና ፖለቲካዊ ጥያቄ አክብሮት ስላለው የህዝቦችን ራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ያሰጠው ፓርቲ ከዚያ ለጥቆ የጠሩ ፖሊሲዎች በመቅረጽ ሀገር ወደማልማት ስራዎቹ ፊቱን አዙሯል፡፡ በዚያም በቃል ያብራራውን በተግባር አሳክቶ በማሳየት ባለወደቧ ሀገር ያላሳካችውን ወይም ያላሳኩትን የእድገት ምጣኔ ባለፉት አስርት አመታት ደጋግሞ ሀገራችን እንድታሳካ በሳል አመራር በመስጠት ድርብርብ ድል አጣጥሟል፡፡

በመሆኑም የወደብን ሚዛን በአግባቡ ያሰላ ወደብ ያላቸው ዙርያውን ያሉ የአፍሪካ ሀገሮች ያላሳኩትን ባለሁለት አሀዝ እድገት ላለፉት 9 አመታት በተከታታይ ያሳካ ፓርቲና በዚሁ ፓርቲ ዙርያ መተማመን የፈጠረ ሕዝብ የገነባን መሆኑ አኩሪ ሂደት ነው፡፡ ይህን ማሳካት የተቻለው ደግሞ ሁሉም ነገር ወደ ወደብ ወደ ጦርነት ግንባር የሚለው መፈክር በሁሉም ነገር ድህነትንና ኋላቀርነትን ወደ መናድ ግንባር በሚል ቅኝት በመተካቱ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment