ሀገሬን እውዳለሁ የሚል አንድ
ገጽ ወሬ ገልበጥ ሳይል እንኳ ሀገሩን የሚጎዳ ተግባር ሲፈጽም የምናየው ዜጋ ብዙ ነው።
የሀገር ፍቅር በአፍ አደለም
የሀገር ፍቅር በእጅ ነው። ስትጮህ አይሰማኝም በርግጥ ያደነቁራል ስትሰራ ግን አምንሀለው ነው ነገሩ። የሀገር ፍቅር ቀረርቶ አደለም።
የሀገር ፍቅር አንዲት ፍሬ ችግር ለህዝብህና ለራስህ መፍታት ከቻልክ በዚያ ይገለጣል።
የእህል እጥረት አለ እውነት
ነው። እርይ እርይ የእህል እጥረት አለ ማለት ግን የሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ስንኳንስና የላቀ ሚናው ተራ አጀንዳው አደለም። ሀገር
ወዳዱ አንዲት ጋት ይህን የእህል እጥረት መፍታት የሚችል ምርምር ከሰራ ዘመናዊ ማረሻ ካዘጋጀ የተሻሻለ አስተራረስ ለአርሶ አደሩ
ማሳየት ከቻለ የምርት አሰባሰብ በዘመናዊ መንገድ እንዲሰራ በማድረግ እስከአንድ ሶስተኛው ምርት የሚባክንበትን ሁኔታ ካስቀረ ወይም
ለማስቀረት ላይ ታች ካለ ይሄ በርግጥም ሀገር ወዳድ ነው።
ወይ የእህል እጥረቱን
ለማስቀረት የሚያስችሉ ዘይቤዎችን እንዳንሰማ ወይ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ እንዳንፈልግ በፋይዳ አልባ ጫጫታቸው
የሚረብሹን የዘወትር ከሳሾች መባከናቸው ሳያንስ ሌሎቻችንንም ሊያባክኑን ስለሆነ እንዳይጮሁ ማድረግ ባንችልም ጫጫታቸውን ቸል ብለን
በርግጥም የእህል እጥረቱን በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ ልናቱኩር ይገባል። እነዚህ ሀገር የሚጎዱ ሀገር ወዳዶች ናቸውና።
ሰው ስራ አይሰራም ሰነፍ
ነው ኡኡ ባለስልጣኑ ሌባ ነው ነጋዴውም ሆዳም ነው ጋዜጦቹን እኛ የማንፈልገውን ከተናገሩ አጭበርባሪዎች ናቸው። ጎብዝ ሀገር ሊቀየር
ከሆነ ሰልፍ ስንጠራህ ውጣ እነዚህ በወጉም ያልበቁህን ባሶች አቃጥል ስንልህ ያለማቅማማት አውድም እኛ ካልሰተሳተፍን ምርጫ አማራጭ
የለውም እኛ ካልተመረጥን ምርጫ ፍትሀዊ አደለም የሚሉህ ተቃዋሚዎች ሀገር የሚጎዱ ሀገር የሚወዱ ልጆችህ ናቸው። እነሱው ጻድቅ እነሱው
ፈራጅ እነሱው ጯሂ እነሱው ታማኝ።
ተሸነፍኩ ማለት ሞቱ የሆነበት
ተቃዋሚ ዴሞክራሲ ስላልገባው የቤት ስራውን እስኪጨርስ በምርጫው ባይሳተፍ እንደ ምርጫ ማጣት መታየት የለበትም። ሲጀመር በምርጫ
አያምንም ሲጀመር ሌላኛው አማራጭ ሊረታኝ ይችላል ብሎ ስለማያምን ተወዳዳሪ ሳይሆን የለየለት ያለኔ ተመራጭ ያለኔ አሸናፊ ያለኔ
ምሁር ማነው የሚል የአስተሳሰብ ህመም ያለበት ሀገር የሚጎዳ ሀገር ወዳድ ነው።
ኢህአዴግ የተሸነፈ ለት
ነው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የነበረው ኢህአዴግ ሲያሸንፍ የመጭበርበሩ ማሳያ ነው የሚል ሽንፈትን የማያምን ሁነኛ የአስተሳሰብ ስብራቱን
መጠገን የተሳነው የተመዘገበ የሚታወቅ አባል ሳይኖረው አቅሜን ፈርታችሁት ነው እያለ በየጋዜጣ የጫጫታ ቁመናው ራሱን በተሳሳተ መስተዋት
የሚያይ ከኔ ሌላ አማራጭ የለም የሚል ግን በተመሳሳይ ችግር ሌት ተቀን ኢህአዴግን የሚወቅስ በሚወነጅልበት ጉዳይ እንኳ ሳይቀር
የወደቀ ተቃዋሚ መያዝ ሀገር የሚጎዱ ሀገር የሚወዱ ግለሰቦች የመሸከም ማሳያ ነው።
የዚህ ሀገር ፖለቲካዊም
ሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በሰሞንኛ የጋዜጣ ጫጫታ የሚቋጩ አደሉም። የጠራ የመታገያ ግብ የጠራ ፖሊሲ በዚያ ዙርያ የተሰለፈ ገና
ከጅምሩ በዲሞክራሲያዊ አሰራር ውስጡን ያነጸ ፖለቲካ ይሻል። ለጥቆ በየሞያችን ሳናሰልስ ምርጥ የሚባለውን አስተዋጾ ማበርከት
የቻልን እንደሆነ ነው አገር የሚጠቀመው። አገርህን ስትጠቅም ሀገርህን መውደድህን እናውቃለን።
ሀገራችንን በተግባራችን ስለመውደዳችን
እርግጠኛ እንሁን እወዳታለሁ ማለትማ ምላስ ይላል ቁምነገሩ እጅህ የጨበጠው ጠቃሚ መሆን አለመሆኑ ነው።
No comments:
Post a Comment