Tuesday, April 2, 2013

አቤት ትችት ጠባሾች መፍትሄ ፈብራኪ ብንሆን ኖሮ!


                                                                                                        ዘርይሁን ካሳ
አለምን ሁነኛ በሆነ መልኩ የለወጧት ሀያስያን እና የትችት ጥማት ያለባቸው ቃላት ጠባሾች አደሉም$
አለምን እና ለምተው የምናያቸውን ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ የቀየሯቸው ችግር ስለመኖሩ የተረኩ ሳይሆኑ ችግሮች መኖራቸውን ተገንዝበው የችግሮቹን መሰረታዊ መነሻ ለይተው ተመጣጣኝ መፍትሄ ማበጀት የቻሉ ሰራተኞች ናቸው$ ትጉሀን ናቸው$

በርግጥ ይህን የመሰለ የፖለቲካና የቢዝነስ ስራ ማሳመን ይጠይቃልና ምላሳቸውን ሰዎችን ለማነሳሳት እና መፍትሄ ለማስገኘት ለሚያከናውኑት ስራ አጋር ለማሰባሰብ በታቀደና ሳቢ በሆነ መልኩ ተጠቅመውበታል$ ትችት ለመጥበስ ግን አደለም መፍትሄ እየጋገሩ ስለሆነ ትችት ለማሰናዳት ግዜ የላቸውም$

የተቸገረ ሁሉ መቸገሩንና ችግር መኖሩንማ ያውቃል$ ቁምነገሩ ችግር አለ ማለትና ችግሩ የነከሌ ነው የሚለው የማጥቆር ስራ አደለም$

ቁምነገሩ ችግሩን በቅጡ ለይቶ ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት በመፍትሄው ዙርያ የሚመለከተውን የህብረተሰብ ክፍል ማሳመን ማግባባት ለችግሩ መፈታት ለሚከናወነው ስራ የሚያስፈልግ ቁሳቁስና ገንዘብ ማሰባሰብ እና ያንኑ እቅድ በመተግበር መፍትሄውን ማስገኘት መቻል ነው$

የማያምር ፖለቲካ ካለ የሚያምረውን ፖለቲካ አምጣው$ ችግር የማይፈታ ፖለቲከኛ ከበዛ ችግር ፈቺው ፖለቲከኛ ሁን$ ዋሾ ከበዛ ሀቀኛው አንተ ሁን$ ሌባ በበዛበት አንተ ታማኝ ሆነህ ተገኝ$

ወዳጄ ይሄን ሀገር መላእክት አይሰሩልንም$ ይሄን አገር ሌሎች ሰዎች እንዲሰሩልንም አንማጸንም$ ይሄ አገር እንዲያምር መኮን ያለበትን እኔና አንተም መሆን አለብን$

ቢሰራ ጥሩ እንደሆነ የሚታየንን ሌሎች እንዲሰሩት መጠበቅ ሳይሆን እውነቱ የምንጠብቀውን ሆነን መገኘት ነው$ ጠያቂ ከመሆን ከምንጠይቀው ውስጥ የጎደለውን አንዱን ሆነን ተገኝተን ያንን ያክል ጉድለት መሙላት ብንችል በዚህ እንከብርበታለን$

የአርሶ አደሩ ልጅ የገጠሩ ልጅ ያለተማረው ፎርድ ሞተርና መኪና መስራት ከቻለ ጆሮው በአግባቡ የማይሰማለት ያልተማረው እና መምህሩ ደደብ ብሎ የሸኘው ቶማስ ኤዲሰን ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ፈጠራዎች ባለቤት ከሆነ

አንደበተ ጎልዳፋው ቸርቺል ያንን ችግሩን ተወጥቶ አገሩ እንግሊዝን ከጀርመኖቹ ወረራ በጠንካራ መሪነት መታደግ ከቻለ

ለአስርት አመታት በተደጋጋሚ ፖለቲካዊ ጥረቶቹ የወደቁበት ኤብርሀም ሊንከን አሜሪካን በፕሬዝደንትነት ከመምራትም በላይ የጥቁሮችን እኩልነት ማስከበር ከቻለ

ጸሀይ የማይጠልቅባትን ታላቅ ነኝ የምትለውን ብሪታንያን ሳይፈራ ጋንድሂ ታግሎ አገሩን ነጻ ማውጣት ከቻለ ማንዴላ የ28 አመታት እስር ሽባ ሳያደርገው ትግሉን ቀጥሎ ጥቁሮች ላይ የደረሰው በደል ልቡናውን ሳያቆሽሸው በይቅር ባይነት አዲስ አገር ደቡብ አፍሪካን ለመምራት ከበቃ

እኛም አገር ወጣቶች ትምህርታቸውን ትተው ጫካ ገብተው በአመታት ጥረት አደገኛ የነበረውን ስርአት ከቀየሩት

እኔና አንተ ዛሬ የምናያቸውን እጥረቶች ለዚያውም ደም የማይጠይቁ ለውጦች ለማከናወን እውን ምን ይሳነናል?

በኔ እምነት ቁምነገሩ የትችት ናዳ ማውረድ መቻል አደለም$ ቁምነገሩ ዛሬ የተጋፈጥናቸው ፈተናዎች የሚጠይቁትን ብቃትና ክህሎት የሚጠይቁትን ንባብና ትጋት ተላብሰን መፍትሄ አማጭ ሀይሎች የመሆን ያለመሆን ጉዳይ ነው$

አባቶቻችን ላላደረጉት መወቃቀስ ሳይሆን ታሪክ እየጠቀሱ ይህ እንዲህ መሆን አልነበረበትም ማለት ሳይሆን ታሪክ እኛም ትላንት ስንሆን እንዲያው ስለሚመዝነን ዛሬን እንደሚገባን እንኑር$ ዛሬ የሚጠይቀውን የስራና የትጋት ጀግንነት ከፍለን ለተጠራቀሙ ችግሮቻችን መፍትሄ እናብጅ$

የሀገር ፍቅር በትችትና በአቤቱታ ናዳ አይፈታም$ ቁምነገሩ አንተና እኔ የመፍትሄ ሰው መሆን አለመሆናችን ነው$

ትችት ጠባሾችን የመፍትሄ ሰዎች ያድርገን!

ይቆየን!  

No comments:

Post a Comment