Friday, April 19, 2013

̋ወያኔ ኢህአዴግ ካልጠፋ መከራችን አያበቃም̋ ̋




የወያኔዎቹ ፓርቲ ኢህአዴግ ካልጠፋ በቀር አገራችን ኢትዮዽያ መከራዋ የሚያበቃላት አይሆንም። የኛ የተቃዋሚዎች ዋናኛው ስራችን ችግሩን የሚፈቱ አማራጭ መፍትሄዎች ማጠናቀር ሳይሆን ኢህአዴግን መጣል መሆን ይኖርበታል።
 
በርግጥ ችግር የሚፈቱ መፍትሄዎች በማቅረብ ረገድ የረባ አማራጭ ማቅረብ የተሳነንም ቢሆን ተቃዋሚዎች ተረባርበን ኢህአዴግን መጣል ዋናው ስራችን ዋናው ግባችንም መሆን አለበት።

ይገባኛል እንዲህ ያለውን ኢህአዴግን የመጣል አጀንዳችንን ፍጻሜው የማይታወቀው ስርአት ወይም ለበለጠ አመጽ የሚያነሳሳ ሁኔታ መጀመርያ አድርጋችሁ እንደምትቆጥሩት እረዳለሁ። ለዚሁ ማረጋገጫ አድርጋችሁ የምታቀርቡት ደግሞ በተቃወሚ ፓርቲዎች መካከል ያሉትን የማይታረቁ ልዮነቶች ነው። አንዳዶቹ እንዳውም የኛን የተቃዋሚዎችን ህብረትና ስብስብ መቼም መጣጣም እንደማይችል የእንቧይ ካብ እንደሚያዩት አውቃለሁ።

የሆነ ሆኖ የተቃዋሚዎቹ ውል አልባ ጋብቻ ምንም ሆነ ምን በነዚህ ፓርቲዎች ምክንያት የሚፈጠረው ጣጣ ምንም ይሆን ምን የኢህአዴግን ግብአተ መሬት በተቻለን መንገድ ሁሉ ማፋጠን አለብን። ይህን አፋኝ ፓርቲ ይሄን ገዳይ ፓርቲ ይሄን የሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ጨፍላቂ ፓርቲ ማስወገድ ዋናው ስራችን ሊሆን ይገባል።

ይህን ማድረግ የቻልን እንደሆነ ነው የዚህ አገር መጻኢ እጣ ፈንታ አንጸባራቂ ተስፋዎች የሚኖሩት። ሀገር እንዴት ይመራል ፓሊሲያችን ምን ይሆናል ብሄር ተኮርና ሌሎች ፓርቲዎች ምን አስታራቂ መስመር ይኖረናል የሚለው ዝብርቅርቅ ስንደርሰ የምንጣድበት እንጂ ዛሬ የሚያሳስበን አይሆንም።

ዋናው ችግር አሁን ከኢህአዴግ የተሻለ ወይም ባይሻልም በአግባቡ የተደራጀ አማራጭ አለመኖሩ አደለም። ይልቅ አደጋው ኢህአዴግ ነው። አፋኝ አገር ገንጣይ ዘረኛ ከፋፋይ ሙሰኛ ገዳይ አሳሪ እና ሌላም የሆነውን ድርጅት ማውገዝና መጣል ነው ቁምነገሩ።


ድህነት እንዴት በተጨባጭ ይወገዳል? የአገልጋይነት መንፈስ እንዴት ይዳብራል? ኢኮኖሚው እንዴት የላቀ አፈጻጸም ይኖረዋል? ዜጎች እንዴት ልማታዊ እሴቶች ይኖሯቸዋል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለመመለስ ትልቅ ጉዳይ አደለም። አማራጭ በመሆን አለመሆናችን ላይ ችግር ቢኖረውም ለዛሬ መላ አቅማችን ማተኮር ያለበት ኢህአዴግ ሊያጣጥሉ በሚችሉ ወቀሳዎች እንጂ ለተጨባጭ ችግሮቻችን መፍትሄ በማፈላለጉ ላይ መሆን የለበትም።

ወያኔ ቤተመንግስት እያለ አማራጭ ቢኖረን እንኳ ተቃዋሚዎች ያንን አማራጭ ማቅረብ የምንችልበት ሚድያ የለም። ቢኖርም ህዝቡ ሊመርጠን ቢፈልግ እንኳ ወያኔ በተለመደ አፈናው የህዝቡን ምርጫ ከማምታታት ወደ ኋላ እንደማይል ይገባኛል።

ስማንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ ውበትና ጥንካሬ እንዲህ አይነቱን ደንቃራ ሁሉ አልፎ በአማራጭ ፓሊሲም በዲሲፕሊንም ልቆ በህጋዊ አመራጭ ማሸነፍ አደለም ወይ? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ እረዳለሁ። ሀሳቡ የሚካድ ባይሆንም በዚህ አማራጭ መሄድ በርካታ አስርት አመታት ግማሽ ክፍለ ዘመን አለያም አንድ ክፍለ ዘመን ሊወስድ ስለሚችልና ኢህአዴግ ይህን ያክል ግዜ በስልጣን አንዲቆይ ስለማንፈቅድ በማንኛውም አማራጭ ወያኔን በአጭር ግዜ መጣል  አለብን በሚል ጥድፊያ ተወጥረናል።

በርግጥ ይሄ ኢዴሞክራሲያዊነት አደለም ወይ? የዲሞክራሲ ሙርከኞች ከሆናችሁ የወሰደውንም ግዜ ቢወስድ ለምንድነው በህጋዊ መንገድ በጠንካራ አማራጭ የመርታት አማራጭ የማትወስዱት የሚል ተገቢ ክርክር እንደምታነሳ አልስትም። ለግዜው ያንን ህሊናዊ የስነምግባር ጥያቄ ትተን በእኔ እምነት ወያኔ ኢህአዴግን በማንኛውም አማራጭ በፍጥነት ልናስወግደው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

አንተ ሁሌም ታጋይ እኮ በትግሉ ሂደት ባጋጠሙት መሰናክሎች አቅሙ ይበልጥ እየጎለበተ አማራጭ ፖሊሲዎቹ ይበልጥ እየዳበሩ በብስለታቸው መጠን ተቀባይነት እያገኙ በዚያው ሂደት በጠንካራ ስነምግባር የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት እና አመራሮች እየፈሩ ይሄዳሉ የሚል ቅኝት አለህ። 

በዚህ መልኩ የማይመራ የፓርቲ ፖለቲካ ስልጣን በማንኛውም አማራጭ በአፋጣኝ ለመያዝ የሚጣደፍ የተቃውሞ ፖለቲካ በመሆኑ በሳል መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በመፍጠር ረገድ የሚኖረውን ሁነኛ ሚና ያመክናል የሚል እምነት እንዳለህ እረዳለሁ። ኢህአዴግን ከዚህ በላይ ልንታገሰው ስለማንችል ለግዜው ይህን አማራጭ መከተል አለብን ብዬ አላምንም።

እርግጥ ነው በዚህ መልኩ መሄዳችን በጠቀስከው መልኩ ታግለን ቢሆን ኖሮ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ሊጎናጸፍ የሚችለው ብስለት እና ለውጥ የጎላ አንደሚሆን ይታመናል። የሆነ ሆኖ ዴሞክራሲያችን በተፈጥሮ ባህሪው እንዲያድግ ስንሰራ እና በዚያ መልኩ ሁኔታዎች የምንመኛቸውን እስኪሆኑ ድረስ ኢህአዴግ ወንበሩን ለተጨማሪ አመታት እንዲያመቻች ማድረግ በመሆኑ ለግዜው ብንተወው የሚሻል ይመስለኛል። ኢህአዴግ በየቀኑ የሚያገኘው የመሪነት እድል ያንገበግበኛል እንደሚፈጽማቸው ከማውቃቸው ግፎች አንጻር።

ይሄን የሚያጫውተኝ የማከብረው የሚያከብረኝ በፖለቲካ እምነቱ ግን የማይመስለኝ የኢህአዴግ ተቃዋሚ የሆነ ወዳጄ ነው። ሀሳቡን አከብራለሁ። ሀሳቦቹና አቋሞቹ የሚያሳብቁትን የተዛነፉ መርሆች ግን አምርሬ እቃወማለሁ።

ይህን አስተሳሰብ ከዴሞክራሲያዊ እሴቶች አንጻር እንድትመዝኑት ለናተ ፍርዱን ልተው።

No comments:

Post a Comment