የውስጠ ፓርቲ ትግል
በተለይም የገዢ ፓርቲ የውስጥ ርስበርስ መተጋገል ባህል አመለካከቶችን የመቃኘት አዝማሚያዎችን እና የተሳሳቱ ተግባሮችን የማረም
ብልሹ አሰራሮችን የመከላከልና ሲፈጠሩም በፍጥነት የማረም አቅም አለው።
ይሄ የሚሆነው ፓርቲው
ውስጣዊ ባህሪው ለትግል የሚመቹ አሰራሮች ያሉት በግቡ ዙርያ መተጋገልን መሰረት ያደረጉና የአስተሳሰብ ፍጭቶችን ማስተናገድ የሚቸሉ
እንደሆነ ነው። አባላትም በነዚሁ የመታገያ ግቦች ዙርያ ለመታገል የሚገደዱበት ባህልና አሰራር የተፈጠረ እንደሆነ ነው።
በፓርቲው ውስጥ የሚታዩ
ውስጠ ትግልን የሚያሟሙቱ በግብ ዙርያ የሚሰባሰቡ ሳይሆን በአለቆችና አለቆች ሊያስገኙ በሚችሉት የሹመትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ዙርያ
የተሰለፉ ቡድኖች እንዳሉ መታዘብ ይቻላል።
በተለያዩ ግምገማዎች
እንደሚስተዋለው አንዲህ አይነቱን ተግባር በግልጽ ለማስኬድ የሚፈራ ቁመና ቢኖራቸውም በግል ጥቅማቸው ዙርያ ተሰባስበው አለቆችን
በማሞካሸትና በመከላከል የአለቆች ተቆርቋሪ መስሎ በመቅረብ ፍርፋሪ ሹመትና መሰል ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚሰሩ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው
አባላት አሉ።
እኚሁ አባሎች በአባልነት
ለመቀላቀል የነበራቸውም አነሳሽ ምክንያት ይሄን የጥቅም ርሀባቸውን የገዢው ፓርቲ አባል በመሆን ማሳካት እንደሚችሉ ማለማቸው ነው።
የትኛውም የድርጅቱ ግብ መሳካት አለመሳካት ቁብ አይሰጣቸውም። ዋናው አጀንዳቸው ጥቅማቸው ነው። ጥቅማቸው ደግሞ የሰፊው ህዝብ ጥቅም
ሲሳካ የኛም ጥቅም እግረመንገድ የሚጠበቅ ይሆናል በሚል እምነት የሚቀነቀን አደለም።
እንዲያውም ጥቅማቸውን
ለማስጠበቅ የሚሰሩት ግቡን በሚደፍቅ ማንኛውም አማራጭ ሁሉ ነው። ግባቸው ጥቅማቸው እንጂ ህዝባዊ ተጠቃሚነት አደለምና። በመሆኑም
ፓርቲው በከፍተኛ መጠን እያሰባሰበ ያለውን አባል በአገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ማሰለፍ የሚያስችለው ውስጣዊ መዋቅር በየግዜው እየከለሰ
አባላቱን እያታገለ ትግሉ ይበልጥ በተግባር እያነጻቸው እንዲሄዱ የሚያሰችል ውስጣዊ ሁኔታ መፍጠር መቻል ይኖርበታል። አንገብጋቢ
የወቅቱ ስራም መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ።
ከዚህ አንጻር የኢህአዴግን
ውስጣዊ ዲሞክራሲያዊ ትግልና አሰራር እያኮላሸ ያለውን ሰፊ የአድርባይነት ልምድና ተግባር ከበቀለበት መነሻ አስተሳሰብ ጋር ማክሰም
የሚያስችል ቅኝት መንደፍ ይህንኑ አተያይ የእለት ተለት ተግባራዊ መመርያ የማድረግ እና በሂደት ከማይናወጥ የፓርቲ መሰረታውያን
አንዱ ለማድረግ ትልቅ ስራ ያሻል።
ይህ አይነቱ ልምድ
ከፓርቲው አይነኬ ልምዶች መካከል የሚገባው ደግሞ በአተያይ ልቆ በተግባር ደምቆ የአሰራር መሰረቶች ተጥለውለት በማይናወጥ ማህተም
ዘላቂነቱ የተረጋገጠ እንደሆነ ነው።
በአድርባይ አሰራር
ተጠቃሚ የነበሩ ቀላል የማይባሉ አባላት በቀጥታ ለአድርባይነት በአደባባይ ባይታገሉም ውስጥ ውስጡን በትግል ላይ የሚመሰረተውን ግብ
ፈለቅ አካሄድ የማብጠልጠል ድክመቶችን የማጉላት አዝማምያ ሊከተሉ የሚችሉበት እድል አይኖርም ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል። በዚህም
በኩል የትግል አብነት መስሎ ለመምጣት የማያቅማሙ በመሆኑ ይሄን በንቃት መከታተል ተገቢ ነው።
የአድርባይነቱ መብቀያ
በኔ እይታ ለአድርባይነት
ለሙ መሬት መንግስታዊ እና ድርጅታዊ ስራዎች የሚመሩት ሀላፊዎች በሂደት የተጎናጸፉት ያሻቸውን ያለበቂ ምክንያት የመሾምና የማውረድ
ስልጣን ነው። ይሄ ረጅም እጅ ነው አድርባይነትን የሚያበረታቱ አስተሳሰቦችን እና ተግባሮችን እያነጸ ያለው።
በተግባር ይሄ አስተሳሰብ
ደግፈኝ ትሾማለህ ተቃወመኝ ቆመህ ትቀራለህ የሚል መፈክር ያለው ይመስላል። ይሄው ሁኔታ ለአድርባዮች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።በመሆኑም
ይሄ አሰራር በስፋት እስከቀጠለ ድረስ ይሄ አዝማምያ የመቃናት እድሉ ጠባብ ነው።
ሹመት ተለይቶ የሚታወቅ
ግልጽ ዝርዝር አሰራር እንዲኖረው ቢደረግና ከአባላት መሀከል የሚደረግ ሹመት ደግሞ ብቃትን እና የትግል አስተዋጾን መነሻ አድርጎ
በአባላት መሀከል በሚደረግ ግልጽ አሰራር በውድድር ወይም በሌላ ግልጽ አሰራር የማይፈጸም ከሆነ ካጫፍ ያለው ሀላፊ እጅ ርዝመትም
ከታችና ከመሀል ያለው ሰራተኛና አባልም አጎንባሽነት ማብቂያ የሚገኝለት አይመስለኝም።
ስለሆነም በአስተሳሰብ
ረገድ አባላት መተማመን እና ታማኝ መሆን ያለባቸው ለመስመር ለመታገያ ግቦች እንጂ ለወቅታዊ ተሿሚዎች መሆን አይችልም ከተሿሚ ጓዶቻቸው
ጋር በመከባበር እና በመተጋገዝ መስራት እንጂ ሌላ ንክኪ ሊኖራቸው አይገባም።
አባላት ስለ ላቀ ተጠቃሚነትም ያስቡም ከሆነ ጥቅም
ማግኘት ያለባቸው ግቡ በአጠቃላይ ከሚፈጥረው ውጤትና በዚያ ሂደት በነበራቸው አስተዋጾ ልክ እንጂ በሌላ መልክ በመሞዳሞድ መሆን
እንደሌለበት ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይሄ አስተሳሰቡ ነው ይሄን አስተሳሰብ የሚደግፍ ማስፈጸም የሚችል አሰራርና እየተገመገመ የሚቀጥል
አፈጻጸም እንዲኖር ማድረግ ይደር ይዋል የሚባል ስራ አይሆንም።
በኢህአዴግ ውስጥ
እየተስዋለ ያለው ለግለሰብ ታማኝ በመሆን ጥቅም የማግበስበስ አዝማምያ በቶሎ መልክ ካልያዘ በቀር በሂደት ፓርቲው በሹማምንት ዙርያ
በሚፈጠሩ የጥቅም ኪራይ ሰብሳቢ ቡድኖች መናጡ አይቀርም።
የላቀው ግብ መስመሩ መሆኑ ይቀርና ስሌቱ ሃላፊያችን ምን ያስደሰታቸው
ይሆን የሚል ጮሌ ቀመር ይሆናል። የዚ መጨረሻው ሁሉ ነገሩ ሀላፊዎችን ማደለብ ብቻ እንጂ ህዝባችንን እና የምንወዳትን ሀገር መሆን
ይሳነዋል።
ለአድርባይነት ያጎነበሰች
ህሊናችንን እና የደከመ ምርጫችንን ለመገምገም እና ለማረም ያብቃን። ኢህአዴግም በጉባኤው ቃል እንደገባው ይሄን የመፈጸም እድሉ
እንደሚኖረው ተስፋ አደርጋለሁ። የገባኤው ውሳኔ መነሻ እንጂ የችግሩ መፍቻ ቁልፍ እንዳልሆነ ስለሚታወቅ።
በሚቀጥለው ጽሁፌ
የአድርባይነትን መነሻዎችና ተጨባጭ መፍትሄዎች ለመጠቆም እሞክራለሁ።
No comments:
Post a Comment