Thursday, April 25, 2013

አንድ ብቁ አማራጭ ብቻ የነበረበት ምርጫ


የባለፈው ምርጫ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በርግጥም በአማራጭነት የቀረቡ የፖለቲካ አቅሞች ሳይሆኑ የፖለቲካውን መድረክ ቅንጥብጣቢ ጥቅማጥቅም መሰብሰብያ ያደረጉት መሆኑን ያሳያል$

በአንድ በኩል ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ፓርቲዎች የተጠናና ጠንካራ የፖሊሲ አማራጮች አቅርበው ለምርጫው ይህ ነው የሚባል መነቃቃት ያላበረከቱበት$ በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግን ደከመ ብለው ለተቹበት ጉዳይ የሚያቀርቡት አማራጭ ደግሞ "ፈሪሀ እግዚአብሄር ያለን ፓርቲ ነን" ከሚል ግርድፍ ቃልኪዳን ማለፍ የተሳነው መሆኑን ታዝበናል$

ወደ ምርጫው ያለገቡት ፓርቲዎች ደግሞ በኔ እይታ በምርጫው ባለመሳተፍ አማራጭ የለለው ምርጫ ተከናወነ የሚል ቅኝት ሊያስደምጡን መቋመጣቸውን ታዝቤያለሁላለመወዳደር ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ ባብራሩባቸው መድረኮች የምርጫ አጀንዳቸውን ማራመድ አይችሉም ነበር የሚል ግምገማ የለኝም$

ለ33 ፓርቲዎች ሁነኛ አጀንዳቸው ላናሸንፍ ኢህአዴግን ከምናጅበው ያንንም ይሄንንም ጠቅሰን አንሳተፍም ተሳትፏችንን እንሰርዝ$ ምርጫው ሲከናወን ደግሞ አማራጭ የሌለው ምርጫ ስለመሆኑ እንስበክ በሚል ያከናወኑት የተዋጣለት የማጣጣል ድራማ ነበር$

በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ ድራማ የገባው ኢህአዴግ በምርጫው የሚይሳተፉ ተቃዋሚዎች ኖሩም አልኖሩም ህዝቡ የመምረጥ መብቱን የሚጠቀምበት እና በምርጫው ለውድድር ከቀረቡት እጅጉኑ የሚሻል በተግባር የተፈተነ ፖሊሲና አፈጻጸም ያለኝ መሆኑን የማሳይበት ህዝቡም በነቂስ ወጥቶ ይሄንኑ ፖሊሲና አፈጻጸም እውቅና እንዲሰጠው ለማድረግ እተጋለው በሚል መንፈስ ሰርቷል$

በርግጥም ይሄ እቅዱ ኢህአዴግ የሰመረለት ይመስላል$ በአዲስ አበባ እንኳ ከተመዘገበው መራጭ 65 በመቶው መርጧል$ መጀመሪያውንም መምረጥ ከሚችለው ከዚሁ ቁጥር የሚልቀው ተመዝግቧል$ በየትኛውም በዴሞክራሲ የላቀ ልምድ አለው በሚባል አገር ምርጫ ጋር ሲነጻጸር የተመዘገበውም የመረጠውም ህዝብ ብዛት ከፍተኛ ነው$

በኔ ትዝብት ኢህአዴግ አባላቱን እና ደጋፊዎቹን በየቤቱ እየሄዱ ነዋሪው በምርጫ እንዲሳተፍ የመቀስቀስ ልምድ እንዲያዳብሩ ማድረግ ችሏል$ ይሄ ልምድ ፓርቲው በሚያጋጥሙት የወደፊት ምርጫዎች በቅስቀሳ ዙርያ አባላቱ ሰፊ ልምድ እንዲቀስሙ ያስቻለ ነው$ ኢህአዴግ ወጣም ወረደም ተቃዋሚዎች ተሳተፉም አልተሳተፉም በያንዳንዱ ምርጫ የአባላቱን ምርጫ የማቀድ የመምራት የመቀስቀስ ነዋሪዎችን በየቤታቸው ሄዶ በማወያየትና እንዲመርጡት በመቀስቀስ ረገድ ሰፊ ልምድ እና ክህሎት እንዲቀስሙ በማድረግ ረገድ የተሳካ ስራ እየሰራ ነው$

በየሰው ቤቱ ሄዶ መቀስቀስ ከባድ ስራ ነው$ ያስፈራል ያሳፍራል ልምድ የሌለን ከመሆኑ የተነሳ$ ይሄን ሰብረው እንዲሰሩ ማድረግ መቻሉ ኢህአዴግ ቀላል ግምት የሚሰጠው አደለም$ ሌላው ደግሞ ይህንን በመሰለው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚያሳትፈው ከፍተኛ አመራሩንና መካከለኛ አመራሩን ሁሉ በማሳተፍ ጭምር መሆኑ በዚህ ረገድ ሰፊ ልምድ መቅሰም የቻለበት እንደሆነ ይታመናል$

እኔ የበርካታው ተቃዋሚ ምርጫን በማጣጣልና ባለመሳተፍ የሚገለጠው ልምድ ኢህአዴግ ዴሞክራቲክ አለመሆኑን ከማሳየት ይልቅ ሲመረጡም የተመረጡበት ሀላፊነት መውሰድ የማይችሉ በአመዛኙ ደግሞ በምርጫ ከመሳተፍ ይልቅ ምርጫ ባለመሳተፍም ጭምር ኢህአዴግን ማጣጣል የተጸናወታቸው ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ቀድሞውኑ ያመራውን አብዛኛውን ህዝብ በተቃዋሚው ጭራሹኑ ተስፋ እንዳይቆርጥ የሚል ስጋት አለኝ$

በኔ እምነት ኢህአዴግን ነጥብ ለማስጣል ምርጫን ባለመሳተፍ ጭምር የሚካሄደው የተቃዋሚ ሀይሎቻችን ትግል ተስፋ የማይደረግባቸው ተወዳዳሪ የፖሊሲ አማራጭ አቅርበው መሸናነፍ የማይችሉና የጋዜጣ ላይ ዘራፍ ባዮች ብቻ እየሆኑ እንዳይሄዱ የሚል ግምት አለኝ$

የሆነ ሆኖ አማራጭ ለኔ የቁጥር ብዛት አደለም$ ሲጀመር ያልተሳተፉት 33 ፓርቲዎች የአቋም የፖለሲ ልዩነት የፈጠራቸው ናቸው ወይስ እንደ እድር የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም የሚገኝ ሽርፍራፊ ገንዘብ ፍለጋ ነው$ የምር ለሀገራዊ ችግሮቻችን መፍትሄ ተብለው የቀረቡ ሀምሳ እና ስልሳ አማራጮች አሉ ወይስ በጉዳይ ዙርያ ሳይሆን በጥቅም ዙርያ የተሰባሰቡ  የምርጫ ቦርድን በጀት የሚከፋፈሉ ፓርቲዎች ናቸው ያሉን$

እንደኔ አንደኔ ከአብዘኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምሰማው አማራጭ ይልቅ ከፌስቡክ ጓደኞቼ እና ብሎገሮች የማገኘው አማራጭ ይልቃል$ እውነቱን ፍርጥ ካደረግነው አበዛኞቹ ፓለቲካ የማያውቁ ፖለቲከኞች ናቸው ዘርፉ የሚያበረክተውን ጥቅማጥቅም ለመቀራመት የተሰባሰቡ ቡድኖች$ ይሄ በርጥም የአገራቸው ጉዳይ አሳስቧቸው የምር አመራጭ ለማቅረብ እየሞከሩ ያሉትን አይመለከትም$

በኔ ግምገማ አማራጭ ያጣነው ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ህዝባዊ ጥያቄዎችን ሳይሆን በፓርቲ ዙርያ ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ ጥቅሞችን ለማሰባሰብ የተደራጁና ከዚህም አለፍ ሲል አማራጭ በማቅረብ ሳይሆን ከኢህአዴግ ይልቅ መፍትሄውን ማከናወን የሚችሉ ሀይሎች መሆናቸውን በማሳየት ሳይሆን ኢህአዴግን ራሱን በማጥላላት ለዚሁ የማብጠልጠል ብቃታቸው ሀገር የመምራት ሀላፊነት እንዲቸራቸው የሚፈልጉ ዋታቾች በመሆናቸው ነው$

ትጉህ አጣጣዮች ሆነው ሊሆን ይችላል የችግሩ መፍትሄ መሆናቸውን ግን ዛሬም ማስጨበጥ አልቻሉም$ አማራጭ ፓሊሲም የላቸውም$ በመሆኑም ዛሬም ያለው የተሻለው አማራጭ ኢህአዴግ ብቻ ሆኖ ቀጥሏል$ እኔ እስከሚገባኝ ኢህአዴግ አማራጭ አይፈጥርም ይልቁንም ኢህአዴግ ራሱን የተሻለው አማራጭ አድርጎ ያቀርባል$ ኢህአዴግ እስከሚያመቻችላቸው የሚጠብቁ ፓርቲዎች መቼም አማራጭ የመሆን እድል የላቸውም$

ይቆየን!

1 comment:

  1. ወዳጄ ለእየታህ ከልብ አመሰግንሃለው፡፡ መቸም አለመታደል ሆኖ ጠንካራ ተቃዋም ፓርቲ ማየት አሁን አሁን እየራቀን የመጣ ይመስላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንደተባለው የተስተካከለ ሌላው ዋጋ የከፈለበት ምርጥ ሜዳ ፈላጊ ቅምጥል ፖለቲከኛ የተበራከተ ይመስለኛ፡፡
    በትንሹ ሌላው ቢቀር ምን የፖሊስ አማራጭ እንዳለው ቀርቦ ማሳወቅ የማይፈልግ አልያም ደግሞ የማይችል፣ ነገር ግን ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር ተጣልቶ ወይም ተፋቶ በትረ-ስልጣኑን እንደምይዙ ተስፈ በማድረግ በማመንታት ጊዜያቸውን እየጨረሱ ያለ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን አንድ ነገር ቆም ቢለው ቢያዩ ደስ ይለኛል፡፡ መቸም በሰላማዊ ውድድር ውስጥ መሸነፍና ማሸነፍ እንዳለ በመቀበል ውድድሩ ላይ ብሸነፍም በእግረ መንገዱ ግን ልምድ በመውሰድ ለተከታዩ ምርጫ የአቅም ፍተሻ፣ የአካልና የአይምሮ ብስለት መለኪያ እንደሆነ መውሰድ ያለበት ይመሰለኛል፡፡ በርግጥ መማር ብቻል 97 ምርጫ ውጤት ተከትሎ ተቃዋም የወሰደው እርምጃ ጥሩ ተሞክሮ ሆኖ ሌሎች ተመሳሳይ እርምጃ ባለመውሰድ ራስን በተጨባጨ ሁኔታ ውስጥ በማሳለፍ ማየት አግባቢ ቢሆንም በተከታታይ የታየው ሁኔታ ጥሩ ያልነበረ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሁንም ልታሰብ ይገባል፡፡ እንደአገር በዚህ መልኩ የምናደርገው የፖለቲካ ጉዞ የዴሞክራሲ ጉዙዋችንን ላይ ትልቅ ጥቁር ነጥብ መሆኑ ግን አይቀረ ነው፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ በርግጥ ምን ማድረግ አለበት? ብዙ ጊዜ ለመተቸት የሚጀምሩ የውጭም ይሁን አገር ውስጥ ፀሀፍዎችና ተናጋሪዎች ከገዥው ፖርቲ የቀረውን ድርሻ አያሳዩም እኔም ማየት አልቻልኩም አልያ ደግሞ አልታደልኩም አላጋጠመኝም ማለት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ለምርጫ መዘጋጀት አንድ የእግር ኻስ ቡድን ወይም አትሌትክስ ቡድን ወደፍት ለሚኖረው ውድድር የሚደርገውን ጠቅላላ ዝግጅት አይኔት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት በሥራ ላይ የተመሰረተ ትልቅ መስዋዕትነት የሚጠይቅ አሰልች ተግባር መሆኑ አልቀረም፡፡ በመሆኑም ወገብ በየጊዜ እፈተሹ የጫወታውን ህግጋት ከማጥናት እስከ መተግበር እንዲሁም ብስለት ያለው የስነልቦና ዝግጅት ጭምር የግድ ይላል፡፡ እንደ እኔ እምነት እንዲህ ከተለፋበት ውጤታማ አገር ወዳድና ገንቢዎች እንሆናለን፡፡ ነገር ግን በጥሎ ማለፍ ወይም የዜሮ ድምር ፖለቲካ አይበጀንም እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

    ReplyDelete