አንባቢዎቼ በወያኔ
ኢህአዴግ ካልጣፋ መከራችን አያበቃም በሚለው መጣጥፌ ላይ ሬገን ሶሎሞን የተባለ አንባቢዬና የፌስ ቡክ ጓደኛዬ የሰጠውን አስተያየት
እንደሚከተለው ያለምንም መጨመርና መቀነስ አቅርቤዋለሁ$ ቈንጆ ሙግት ነው አንብቡት$
ውድ ዘሪሁን ካሳ
በቅድሚያ በዚህ ወር ሃሳብህን ስላካፈልክባቸው መጣጥፎችህ ምስጋናዬ ይድረስህ $ በሁለቱ ላይ ሀሳብ መስጠት እንዲያስችለኝ ሁለቱንም በጥሞና አንብቤያለሁ$ እናም በመሰረታዊው ሃሳቦችህ ላይ በተለይ ከአንዱ ጋር እስማማለሁ$ ሁለቱ መጣጥፎችህ ወያኔ ኢህአዴግ ካልጠፋ ና መለስ ተኪ የሌለው መሪ አይደለም የሚሉት ናቸው$ በሚቀጥለው ጊዜ መለስ ተኪ የሌለው መሪ አይደለም ለሚለው መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ$ ከዚህ በታች የተሰጠው አስተያየት ግን ወያኔ ኢህአዴግ ካልጠፋ ለሚለው መጣጥፍህ አንኳር ትችቶችህ የተሰጠ የመልስ ትችት ነው$
በመጀመሪያ በተቋዋሚው /ሰብ እኔን ጨምሮ ወያኔ ኢህአዴግ ካልጠፋ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም ወይም መከራችን አያበቃም የሚለው ቅዠት መኖሩን አምናለሁ$ ይህ ሀሳብ የሚነሳበት ዳራ ወያኔ ኢህአዴግ የችግሮቻችን ሁሉ መሰረት ነው ብሎ ከሚያስብ ነገር አቅላይ አተያይ ነው$ ቅዠት ነው የሚያስብለኝም ለዚያ ነው$ ነገር ግን ለድርድር የሚያመች ሁኔታ ቢኖርና ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የሚሳተፉበት ስርዓት መፍጠር ቢቻል በግሌ ደስ ይለኝ ነበር$ ብዙ ተቃዋሚዎችም ይህ እንደሚያስማማቸው አውቃለሁ$ በፕሮግራማቸውም ሳይቀር ይህንን ያወጁ ወይም ያስቀመጡ አሉ$ ያም ሆኖ አንተ የገለጽከውን አይነት ዝንባሌ አለ$ ለዚህ ግን ተጠያቂው ተቃዋሚው ብቻ አይመስለኝም$ የአንተም መጣጥፍ አተያዩን መኮነኑ ደግ ሆኖ ለመቸከላችን ምክኒያቱ ተቋዋሚው ነው ወደሚል ድምዳሜ የሚያንደረድረውን ሃሳብ አልስማምበትም$
ሁለተኛ አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስንል ደረጃዎችና የሚቀርብበትም ከዚያ የሰፋ ከባቢ አለው$ በኔ አተያይ ከፖሊሲና ስትራቴጂ በፊት ሀገራችንን ወዴትና እንዴት እንደምንወስዳት ባለው ራዕይና ተልኮአችን ላይ የጠራ ስምምነት የለም$ ከዚያ ሲቀጥል ደግሞ እንደ ሀገር ለመቀጠል ስጋትና አደጋ የሚሆኑን ጉዳዮች ተብለው የተቀመጡት አጀንዳዎች አንገብጋቢነታቸው የተመዘነበት ዕይታ ከሀገሪቱ ህልውና ይልቅ የህወሀት ኢህአዴግንና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለውን መስመሩን የበላይነት ለማስጠበቅ የተቀረጹ ናቸው$ በዚህ ውስጥ አማራጭ ብሎ ነገር የለም$ አማራጭ የሌለውና ብቸኛ እንዲሆን ተገፍቶ ተገፍቶ እዚህ ደርሷልና$ አማራጭ የሚኖር የነበረው ከመሰረቱ ሁሉንም አካላት ያሳተፈና ተቀባይነት ያለው አስማሚ ባይሆን እንኳ ሁሉን ለማቀፍ ክፍት የሆነ ራዕይና ተልኮ ተቀርጾ ይህን ግብ እዳር ለማድረስ ስጋቶቻችንና አደጋዎቻችን ላይ ከሞላ ጎደል አብዛኛው ሰው የሚስማማበት አካሄድ ቢመረጥ ነበር$ ይህን ሁኔታ ስታስብ ከመጠጋገን ይልቅ አፍርሶ መስራት ትክክል ነው የሚለውን አተያይ ለመኮነን እንዲህ ቀላል አይመስለኝም$
ሌላው አንዳንዱ ነገር ለምሳሌ ሐገር የምትመራበትን መርህ መድብለ ፓርቲ ወይስ የአንድ ፓርቲ የበላይነት መርህ ይሁን የሚለው በኢትዮጵያ ሁኔታ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም$ በህገ መንግስቱም የተቀመጠ ነው$ ኢህአዴግ ይህ እንዳይኖር ወይም ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሲብስም የህዝብን የመቃወም መብት በሚጥሱ ህጎችና አስተዳደራዊ እክሎች የበላይነቱን ስለማስጠበቅ ይሰራል$ እየሰራም ነው$ ይህን በአጠቃላይ ፍሬሙ ውስጥ ያላስገባህ እንደሆን አተያይህን ሸውረር ያደርገዋል$
እንደዚሁም ሁላችንም እንደምናውቀው የኢህአዴግ ሃሳብና ተግባር አማራጭ ሃሳቦችን በእንጭጩ ማጥፋት ነው$ እንዲህ አይነቱ ተግባር ቀድሞ በአስተዳደራዊና በቢሮክራሲ መሰናክሎች ባስ ሲልም በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ጭምር ሲፈጸም ነበር$ አሁን አሁን ከዚህ ተግባር በተጨማሪ ከህገ መንግስቱ የሚጻረሩ የህግ ማዕቀፎችና ማስፈጸሚያ ህጎችን እንኳ በማውጣት ተቃዋሚዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብሎ በሚያስባቸው ክፍተትና ቀዳዳዎች ላይ ሲጥፍ ሲደርት ማየት የተለመደ ነው$ ያንተ ሃሳብ እንደሃሳብ አንዱን ጎን ብቻ መውሰዱና መተቸቱ ኢፍትሃዊ ትችት የሚያደርገው ከዚያም ሲያልፍ ያለውን ሁኔታ የማስቀጠል መከላከል የሚሆነው ለዚህ ነው$
በተጨማሪም ዺሞክራሲ በተፈጥሮ ባህሪው የሚያድገው እንዲሁ እድሜ ጠገብ ስለሆነ ወይም ብዙ አመታት በማስቆጠሩ አይደለም$ በሂደቱ ውስጥ የሚቀርብለት ግብዓትም ወሳኝ ሥፍራ አለው$ በተለይ ለዲሞክራሲ እድገት ብሎ በቅን ልቦናና ያለራስ ወዳድነት የሚስራ መንግስትን ትጋትና ሁሉንም ያገባኛል የሚል ህብረተሰብን አስተዋጽኦ የሚቀበል ሰፊ ምህዳር በግብዓትነት በቅድሚያና በወሳኝነት ይፈልጋል$ ይህ በኢትዮጵያ የለም ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግና መንግስት በዚህ ረገድ ዲሞክራሲ በሁለት እግሩ ይቆም ዘንድ የገንዘብ የዕውቀትና የተግባር አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚታትሩትን ግለሰቦችና ድርጅቶች በማደን ተግባር ላይ መሰመራታቸው ዛሬ ዛሬ መላው አለም የሚያውቀው ባህሪይ ሆኗል$ አሁን ባለው የፖለቲካ ምህዳር የሚመጣው ለውጥ በራሱ ተፈጥሮአዊና ነጻ አይደለም$ የህወሀት ኢህአዴግ ጣልቃ ገብነት የሚያሳርፈው ተጽዕኖ እንደ ጄኔቲክ ምህንድስና ዓይነት መጠንና ቅወጣው ከፍ ያለ ቁጥጥር አብይ መገለጫው ነው$ በመሆኑም ሆን ተብሎ ዲሞክራሲን በማጫጨት ለፍሬ የሚበቃበትን ጊዜና ዕድገቱን አዝጋሚ ተደርጓል$ እየተደረገም ነው$ ስለዚህ በዚህ በኩል ያለህ ትችት ትክክለኛ አተያይ አይመስለኝም$ አልስማማበትምም$
ከዚያ በመለስ ግን በሁለት ጉዳዮች የምንስማማ ይመስለኛል$ አንደኛ ተቃዋሚዎች ከወያኔ ኢህዴግ የሚያሳትፍ ፖለቲካ አይከተሉም$ በማናቸውም ሁኔታ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ወድቆ ያሉትን ባለስልጣናት አባሮ በአዲስ መተካት በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረት ምኞት አለ$ ይህ ትክክለኛ ምኞት አይመስለኝም$ የሚሳካም አይደለም$ ምክኒያቱም በዚህ ሥርዓት ጥቅማቸው የተከበረላቸው ወይም የመሰላቸው ከዚህ አይነት ትግል ተቃራኒ መቆማቸው አይቀርም$ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታና በትምህርትና ዕውቀት ሥርጭትም ምክኒያት እነዚህ የ/ሰብ ክፍሎች ብዙ ናቸው$ ከዚሁ ጋር የዚህ የድጋፍ መሰረቱ ትግራይና ብሔር ብቻ ነው ብሎ መታሰቡም ትክክል አይደለም$ ስለዚህም ወያኔ ኢህአዴግን አጥፍቶ በምትኩ ሌላ የአሸናፊ ፖለቲካ ለማምጣት መታገላቸው በሂደት ዋጋ የሚያስከፍል ነው$ እያስከፈላቸውም ነው ብዬ አምናለሁ$
ሁለተኛው ከጥቂት የድጋፍ መሰረታቸው በጣም ውሱን ከሆኑት የፖለቲካ ተቀናቃኝ ድርጅቶች በቀር በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ያሉ ተቃዋሚዎች ወያኔ ኢህአዴግ ስለመውደቁ የመተለማቸውን ያህል ከውድቀቱ ማዶ ሀገሪቱ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደምትመራ እንደዚሁም ከመሃከላቸው ምንና ማን አስማሚ ሃይል ሆኖ ሽግግርን እንደሚመራ በግልጽ ያስቀመጡት ወይም ይህን የሚገዛ አጠቃላይ ስምምነት የለም$ ይህ ያሳስበኛል$ ያሰጋኛልም$ ይህም እንደማስበውም ለሚያገኙት ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ አይነተኛ ቦታ አለው$ እኔም በወያኔ ኢህአዴግ ካልጠፋ መጣጥፍህ ላይ ያነሳኋቸውን አንኳር ነጥቦች እዚህ ላይ ቋጨሁ$ በቸር ያቆየን$
No comments:
Post a Comment