Tuesday, November 20, 2012

ሊለውጥ ሲለወጥ

አውግቸው ጅምሩን ዲሞክራሲ ሩቅ ሊያደርሱት ለራሳቸው ቃል ከገቡ ቆራጦች አንዱ ነዉ፡፡ ተስፋ ሰጪውን የኢኮኖሚ እድገትም የምር የብዞዎችን ኑሮ መቀየር ከሚችልበት ደረጃ ለማድረስ እጅግ ተነሳስቱዋል፡፡ ማንም አጠገቡ ያለ ሰው አዘውትሮ ከሚወተውታቸው እና ከሚያነሳቸው ጨዋታዎቹ ይህን ይረዳዋል፡፡

መንገዱ ረጅም ነው ይላል ሁሌ፡፡ ዋጋም ያስከፍላል- ቢያንስ በራስ ጥረት ባገኙት ብቻ መኖርን ይጠይቃል፡፡ እነ እገሌ ሰርቀው ትተውን ሄዱ በሚል ቁጭትና በአጭር በመክበር ፍላጎት ተማሎ በስነ ምግባር አለመላሸቅ ትልቁ ነገር ነው ሁሌም በጨዋታው መሀል፡፡

ይነሳሳሉ አጋዥ አቅም ይሆኑኛል የሚላቸው ወዳጆቹ ፅናቱን ፍላጎቱን እና ተነሳሽነቱን ከማድነቅ ባለፈ ጣታቸውን ትግሉ በሚጠይቀው ተግባር ዙሪያ ማነካካት አይፈልጉም፡፡ ትግሉን ስለማያምኑበት አደለም፤ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ስለማያሳምኑዋቸው አደለም፡፡ ትግሉን የሞከሩ ሰዎች ቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰጉ ዋልጌ ልምዶች እና አሰራሮች እንዴት እንዳሰናከሉዋቸው ስላዩ ነው፡፡

ለውጡ ቢመጣ ይወዳሉ ግን የለውጡ ተቃራኒዎች የሚደቅኑትን ስጋት የሚሻገሩበት መላ አይታያቸውም፡፡ እንዲያውም በጅብ ሊያስበላን ነው እንዴ አርፌ ትምህርቴን ልማር፤ አርፌ ኑሮዬን ልኑር፤ አርፌ እድገትና መስል ጥቅማጥቅሞችን ላግኝ እንዳገር ለማገኘው ጥቅም ለምን ብዬ ነው የግል ጥቅሞቼን የማጣው በሚል መነሻ ግን በተሸነፈ አተያይ እና ልምድ ተይዘው ሊያግዙት አልቻሉም፡፡

ስለ ለውጥ በተነሳ ግዜ ሁሉ ግን ድፍረቱ ለለውጥ ያለው ቀናነት በተሳሳተ አሰራራቸው ለሚታገላቸው ሰዎች እንኩዋ ሳይቀር ያለው ክብር ያስገርማቸዋል፡፡ የዚያኑ ያክል ሊያገኝ ሲችል በተለያዩ ማሳበብያ ምክንያቶች ያጣቸው ጥቅሞች፤ እድገቶች እና መሰል ነገሮች ግን ያስቆጩዋቸዋል፡፡ ይህንን መክፈል ስለሚጠሉ ነው እነሱ የሚወዱትን ለውጥ ሳይሰብኩ የሚያዩትን ነውር ለማረም ሳይጠሩ የቀሩት፡፡ እንዳያግዙት ትግሉ የሚያስከፍለውን ዋጋ ይፈሩታል ያው ግን ከንፈር ይመጡለታል- ምሰኪን፡፡

አውግቸው በቀናነት በጠቃሚነታቸው እና በአዋጭነታቸው አስቦባቸው የሚያመጣቸው ሀሳቦቹ አይወደዱለትም፡፡ አጉል አውቃለሁ ባይ፤ ያለኔ ተቆርቁዋሪ የለም አለ፤ ደርሶ ጠበቃ፤ ግትር፤ ወሬኛ፤ ክርክርን እንደስራ የቆጠረ ሰነፍ በሚሉ ቅፅሎች እየታጀበ ይወረፋል፡፡ ለነዚህ ዘለፋዎች እቁብ ባይሰጥም ትንሽ ገፋ አድርገው የሚገባውን ጥቅማጥቅም በመንሳት እንደማይችል ሊያሳዩት ቆርጠዋል፡፡

ይህ የትግል ዋጋዉ ነው፤ ይህ የትግል ልኩ ነው ይላል አውግቸው ጉዋደኞቹ ለምን አውጌ ትንሽ እራስህን ወደሚጠቅም ነገር ለተወሰነ ግዜ ዞር አትልም ሲሉት፡፡ አንተ ብቻህን ስለታገልክ አይሆን፡፡ ሁሉም ሲሰራው ይምጣ አንተ የራስክን ኑር ይሉታል፡፡ እርሱ ለሰዎች እየኖርኩ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ለራሱ ኑሮ እየታገለ እንደሆነ ነው የሚያምነው፡፡ ጥቅል አገራዊ ባህሎቻችንና ልማዶቻችን በየግል እንደሚጎዱን ያያል፡፡ ለዚያ ነው አሰራሩን ተቁዋሞቹን እና አገራዊ ልማዶቻችንን የሚገመግመው፡፡

አንዳንዴ የብቻው ግዜ ወስዶ ሲያስብ የለወጠው ነገር ቢኖር ብዙ ሊያድግ ሲችል አለማደጉ፤ ባለመደጉ፤ የደሞዝ ጭማሪዎች የሚገባውን ያህል ባለማግኘቱ አቻዎቹ የነበሩ ሰዎች ተሻግረውት ሲሄዱ የሱ ምርጫዎች ውሱን እየሆኑ ሲሄዱ ያያል፡፡ የቀድሞውን ያክል እንኩዋ የሚፈልገውን ምግብ መርጦ የመመገብ እድሉ እየኮሰመነ፤ የሚሻውን ልብስ የመግዛት አቅሙ እየወደቀ፤ የቤት ኪራይ የመክፈል አቅሙ እየደከመ መሆኑ ነው የሚታየው ለውጥ፡፡ እናም ለውጡ ይብሱኑ መቸገሬ ካልሆነ እውን ምን ለውጥ አመጣሁ ብሎ በስጨት ይላል፡፡

ለምን እንደማንኛውም ሰው ዝም ብዬ ስራዬን እየሰራሁ ጥቅሞቼን አላስጠብቅም ይላል፡፡ ሰዉ ዝም ባለበት ብዙው ዋጋውን ፈርቶ በተወበት የኔ ወትዋችነት ምንድነው ኪሳራ ከመሆን ባለፈ- ራሱን ይሞግታል፡፡ ህሊናው ግን ሁሌም ትግል በአንድ ቆራጥ ሰው ልብ ተፀንሶ እየሰፋ እንደሚሄድ ይነግረዋል፤ ዝምታውም ዝምታ እንዳልሆነ ያውቃል፡፡ ፍርሀቱ ሲገፈፍለት ዝምታዉ የሚፈልገውን ወጤት እንደማያመጣ ሲታየው የሚቀላቀለው ብዙ የምር በለውጡ የሚያምን ብዙ ሰው እንዳለ ያያል፡፡

የቁዋሚው አጫፋሪዎችም ትግሉ ሲፋፋም ለውጡ አይቀሬ ሲሆን በፅናት የመቆም ባህሪያዊም የትግልም አጀንዳ እንደለላቸው ይረዳል፡፡ አጨብጭቤ መብላት እስካቻልኩ ምን አገባኝ ባዮች እንደሆኑና የሀይል ሚዛን ሲቀየር እንደሚቀልጡ እንዲያውም የአዲሱ ትግል ካድሬዎች ለመሆን እንደሚቃጣቸው ይረዳል፡፡ እናም የሆነው ትግሉ የሚጠይቀውን ስነምግባር ገና በጠዋቱ በተግባር የመማር ጉዳይ ነው፡፡ ጥቅም ቀርቶብኝ፤ ተነቅፌና ያን ወቀሳና ኪሳራ ዛሬ በጅምር በትንሽ ካላሸነፍኩ የነገውን ትላልቅ ትንቅንቅ ስለመወጣቴ ምን ማረጋገጫ ይኖራል ይላል፡፡

ትግል የውጣውረድ አለመኖር ሳይሆን በውጣውረድ ሳይዝሉ መነሻው የሆነውን ግብ ዳር ማድረስ እንደሆነ የምር ይገነዘባል፡፡ አሸናፊዎች ምንግዜም ውጣውረዱ ያልጣላቸው ያላንገዳገዳቸው አደሉም፡፡ እንዲያዉም እንዲያ ያለውን ድግግሞሽ ተስፈንጥሮ መነሳትን እየተማሩበት የጎደላቸውን እየሞሉበት ከቀደመው የመለጠ እየተጉበት የተበጠሰ የሚመስለውን ተስፋና ተግባር እየቀጠሉበት እንደተጉዋዙ ካነበባቸው የጀግኖች እና የመሪዎች ግለ ታሪክ እያጣቀሰ ቀቢፀ ተስፋ የሸተታትን ወኔውን የበለጠ አጠናክሮ ይነሳል፡፡

ሁሌም ለካ ለመቀየር መነሳት ቀድሞ ይቀይራል፡፡ የዘገየን የሚመስለን ትግሉ የሚጠይቀውን የቤት ስራ በራሳችን ላይ ስንጨርስ ነው- ይላል፡፡ ሁሌም ከንደዚህ አይነቱ ፍተሻ በሁዋላ የበለጠ ተነሳስቶ ብቅ ይላል፡፡ እንዲጠወልግ የሚሹት የሳቱ ወዳጆቹም የበለጠ ሊያዳክሙት ይቆርጣሉ፤ ወዳጆቹ እና ሌሎች የማይታጠፍ ግንባሩን ይበልጥ ያደንቃሉ፡፡ ትግሉ አጋር እንዳለው የበለጠ እርግጠኝነት ይሰማቸዋል፡፡
ነገም መዛል አለ ግን የበለጠ ጠንካራ ታጋይ ይወለዳል ያምጡት ተግዳሮቱን - የሁሌ ምኞቱ ነው፡፡ ይበልጥ እየጠነከረ ነው እንጂ እየደከመ እንደማይሄድ ይረዳዋል፡፡
ጀግና ሰው ነው ይፈራል፤ ይዝላል፤ ይሳሳታል፡ ይወድቃል ግን ጀግና ነውና ዝለቱን ድካሙን ውድቀቱን ጠንክሮበት የበለጠ ተስሎ ይነሳል ይቀጥላል፡፡ ለመቀየር መቀየር ለማስጀመር መጀመር የግድ ነው፡፡ ትግል ሲታገልህ ይለውጥሀል፡፡ ለለውጡ የተመቸህ ያደርግሀል፡፡
የቀረው ይቆየን!

No comments:

Post a Comment