Monday, December 30, 2013

ንጉስ ሚኒሊክ ቅኝ ገዢ ወይስ ከፊውዳሎች እንደ አንዱ--- ክፍል 1




በመጀመሪያ ጉዳዩን ማየት የምፈልግበትን መነሻ ላስቀምጥ። አላማዬ ታሪካዊ ትንታኔ መስጠት አደለም። አላማዬ ታሪክ የምናጣቅስበትን መነሻና እሚመራበትን አተያይ መፈተን ነው። ለእናንተም በዚህ ንባብ ቃል እምገባው በየትኛውም ወገን ሆነን የሰማነውን ታሪክ መነሻ አላማና ግቡን እንድትጠይቁት የሚጠቁሙ ቁምነገሮች እንደማካፍላችሁ ነው።

ሀገራችን ከየት ናት? የመቼ ናት?

ሀገራችን የብራና መጻፍ ወይም አመተምህረት መጥቀስ ሳያስፈልግ ከሰሜን እስከ ደቡብ ህዝቡ ተሳስሮ የሚገኝበት አሰፋፈር አንዴ አንዱ ሲያይል ወደ ሰሜን ሲዘምት፤ ኦሮሞ ጎንደር ላይ ሆኖ ሲያስተዳድር እስከዛው ድረስ ያለውን ህዝብ በጦርነት ረምርሞት ሄዶ እንደነበር ይናገራል። እስከ ዛሬ ጎንደር ላይ የምናያቸው ስያሜዎችና አብያተ ክርስትያናት እና የኦሮሞ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ማህበረሰቦች የሚያመላክቱት ያን ነው። በወሎ በኩልም የእያንዳንዱ ገጠርና ወንዝ አካባቢ ስም ሳይቀር በኦሮምኛ ተሰይሞ የምናገኘው በአጋጣሚ አደለም። አካባቢውን ይዞት ኖሮበት መርቶት እንደነበር የሚያሳይ ነባራዊ ሀቅ ነው። አሁንም ድረስ ኦሮምኛ የሚናገሩ የወሎ አካባቢዎች የዛ ዋቢዎች ናቸው። እስከ ትግራይ የኦሮሞ ባህል እና ደም አሻራዎች ዛሬም አሉ። እናም ሀገር አንዴ በሰሜኖቹ ተዋጊዎች ሌላ ግዜ ደግሞ በደቡቡ ጀግኖች ስትመራ ስትገብር የኖረችበት ሁኔታ ነበር። ሀገር አንዴም በደቡቦቹ ጭካኔ ሌላ ግዜ ደግሞ በሰሜኖቹ ጭካኔ ስትደማ ስትበለት ስትቆረጥ ነበር። 

የታሪክ ድርሳናት የቅርቡንም የሩቁንም ታሪክ ሲያወጉ የወንድ ብልትና የሴት ጡት ቆርጦ ወደ መጣበት አካባቢ በመውሰድ ጀግንነቱን የሚያስመሰክር ጦረኞች እንደነበሩ ይዘክራሉ። የገደልንም እኛው የተጋደልንም እኛው ማን ምንገደለ እንዴት ገደለም ብለን የምንነታረክ እኛው ነን። ታሪካዊ ሀቆቹን መቀየር አይቻልም። ሀቆቹን መካድም ፋይዳ የለውም።

ወሎ ካሳሁን ሁሴን የሚባል ሙስሊም ብቻ ሳይሆን መሀመድ ሀይለጊዮርጊስ አምባቸው ጉደታ የሚባልም ሰው ያለበት አካባቢ ነው። ስም እየጠራህ ስትሄድ ሀይማኖት ብቻም አደል የሚደባለቀው ዘሩም ድብልቅ ይሆንብሀል። ይሄን አገር በወጉ ካየነው ቋንቋዎቹ የሚያሳዩንን ልዩነት ሀይማኖቶቹ የሚያሳዩኑን መስመር እና ብሄራዊ ጥንቅሩ የሚያሳየንን ልዩነት ታሪካችንን የሁዋሊት እየተረተርነው ስንሄድ አናገኘውም።

ሰው ከማመን ይሄን መረጃ ማናችንም አንብበንና አጣርተን ልንደርስበት የምንችለው ነው። በደም በሀይማኖት እና በብሄር ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ መረጃዎች በቋንቋም ረገድ ይሄ የአፍሪካ አካባቢ አንድ ቋንቋ ይናገር እንደነበር ይናገራሉ። የሁዋሊቱን እውነት ወደፊት ስንጓዝ ግን ልንተረትረው እየጣርን መሆኑ ይታያል። እውን ችግሩ አብረን መቋጠራችን ነው? እውን አደጋው አንድነቱ ነው? መፍትሄውስ አንድነቱን ያላሳመሩትን ችግሮች መቅረፍ ነው ወይስ በጋራ የተቋጠርንበትን ውል መበጠስ?

እናም ሀገራችን እና አሁን በኛ ካርታ ውስጥም ያይደሉ አካባቢዎች የሁዋሊት ረጅም ግዜ ታሪክ ያላቸው የተሳሰሩ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን የሚቀዱበት ህዝባዊ ገመድ አንድ እንደሆነ ይመሰክራሉ። የመቶ አደለም የሶስት መቶ አደለም በአስር ሺዎች የሚቆጠር ታሪክ አለ። አለማቀፋዊ የታሪክ ድርሳናት ስለ ሀገራችን የሚያሳዩት እውነት ይሄ ነው። ባለመቶ አመት እድሜ ባለጸጋ ብቻ አደለንም። በሺ የሚቆጠር እድሜም ስላለን ብቻ አንድ ሆነን እንቀጥላለን ማለት አደለም። እሱን የዛሬው አያያዝ ይወሰነዋል። እምንጋራው ከአንድ ደም የሚቀዳ ቅርስ አለን ነው ድምዳሜው።

ከዚህ ተነስተን ንጉስ ሚኒሊክ ቅኝ ገዢ ወይስ ከፊዳሎች መሀከል አንዱ ነው? የሚለውን መመለስ እንሞክር።

ፊውዳሎች በጦርነት ወይም በውድ ማንንም ከማንበርከክ ወደሁዋላ አይሉም። ቁምነገሩ ክብር እንጂ ብሄር ምናምን የሚባል መስፈርት አደለም። ማረጋገጫው አንዱ በሌላው ላይ ይዘምትበት የነበረው የዘመነ መሳፍንት ግዜ ነው። ጦርነቱ በብሄር ልዩነት የሚነሳ ሳይሆን በአስገብራለሁ አልገብርም፤ በእኔ ነኝ የበላይ አይደለህም የሚነሱ ግጭቶች ናቸው። ከጎጃም እስከ ጎንደር ከጎንደር እስከ ትግራይ ከትግራይ እስከ ወሎ ከወሎ እስከ ሸዋ ከሸዋ እስከ ሀረር ከሸዋ እስከ ወላይታ ከሸዋ እስከ ጂማ እልክ አስጨራሽ ውጊያዎች ተድርገዋል። ጎልበተኞቹም ወታደሮቻቸውም ደሀውም ጪሰኛ አልቀዋል። የእገሌ ብሄር የለ የእገሌ ሀይማኖት የለ ተጨፋጭፈዋል።

ንጉስ ሚኒሊክም በዚህ ምእራፍ የነበረ በተለየ ሁኔታ ግን ለኛ ዘመን ስሜትና ተጨባጭ ሁኔታ ቅርብ የነበረ፤ አልገብርም ባሉ ወገኖች ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸመ፤ ከገበሩት ጋር ደግሞ ተስማምቶ የቀጠለ፤ ያ ዘመን የወለደው ነገር ግን በገዛ ምርጫው የዘመኑን ፍልስፍና ተከትሎ ጦረኛ የሆነ ንጉስ ነው። እሺ ብለው የተገዙት አልተገደሉም። እምቢኝ ያሉ የአካባቢ ፊውዳሎች ባሉበት ደግሞ ያለ ርህራሄ የጨፈጨፈ ነው። ጨለንቆ የዚያ ማሳያ ነው። ወላይታ ተመሳሳዩ ዱላ የደረሰበት ቦታ ነው።

አቅሙን ተጠቅሞ በጦረኛነት ከመሀል ሸዋ ወደሰሜንም ከመሀል ሸዋ ወደ ደቡብም ከመሀል ሸዋ ወደ ምስራቅና ምእራብ ዘምቶ የተስማሙትን ግብራቸውን ወስኖላቸው እምቢኝ ላሉት ሰይፉን አቅምሶ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ሀገር የመራ የዚያ ዘመን ፊውዳል እንጂ፤ የማያውቀውን የሚጋራው ቅርስ የሌለውን ባእድ ህዝብ በግዴታ የያዘ ንጉስ አልነበረም። ኦሮሞ ተወጊዎች አሸናፊ በሆኑበት ግዜ ወደላይ እና ወደታች ወደ ግራና ወደቀኝ በተንቀሳቀሱበት ልክ ሀይለኛ በነበረበት ግዜ በተመሳሳዩ ሰፈር ያሻውን ያደረገ ከወዲህም ከወዲያም ባለሙዋሎች የነበሩት ሀገሬ ፊውዳል ንጉስ ነው።

ቅኝ ገዢ መባል አለመባሉ ዛሬ ለሚኖረን አገራዊ አንድነት ወይም መገንጠል ጥያቄ ፋይዳ ስለሚኖረው እናዳፍነው በሚል መቀነት መታሰር አልፈልግም። የሆነ ሆኖ ሚኒሊክ ቅኝ ገዢ የሚሰኝበት ታሪካዊ ሀቅ ግን አይታየኝም። ካርታው ጎልቶ የወጣው በሱ ግዜ ስለሆነ ይሄ አገር ከዚያ በፊት አልነበርም ለማለትም ከሆነ። ስለ ካርታ ማሰብ ስለ ወሰን መወሰን የመጣው ከቅኝ አገዛዝ ጋር ተያይዞ በመሆኑ የሚኒሊክ አብይ ውጤት ተደርጎ መሳሉ ስህተት ነው። ድንበር በብሄር ማንነት የሚወሰን ቢሆን ከፊሉ ኦሮሞ  በኢትዮዽያ ከፊሉ ደግሞ በኬንያ ከፊሉ አፋር በጂቡቲ ከፊሉ አፋር በሀገራችን ከፊሉ ሶማሌ እዚህ ከፊሉ ሱማሌ ደግሞ እዚያ ከፊሉ ንዌር ከኛ ጋር ሌላው ደግሞ ከሱዳን ባልሆነ ነበር። ድንበሩ የቅኝ አገዛዝ ውጤት ነው በዋናነት። ተፈጥሮ ያሰመረችው እና ብሄራዊ ማንነቶች ተተንትነው በወጉ የተሰደረ ጉዳይ ይመስል በሌለ እና ባልተደረገ ጉዳይ ግዜ ማባከኑ ተገቢ አይመስለኝም።

በመሆኑም ቅኝ ገዢ አልነበረም። ቅኝ ገዢ የሚያስብለውም ምንም አይነት ታሪካዊ መሰረት ያለው አደለም። አለመሆኑንም እንዲያ ብለው የሚሰብኩትም ያውቃሉ። ግን ያን ስብከት ደጋግመው ይነግሩናል። ፕሮፖጋንዳ ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚለውን የህዝብ ግንኙነት ፍልስፍና ይዘው። ሚኒሊክ ከሌሎቹ ፊውዳሎች የሚለየው በቅርቡ ታሪካችን በርካታ ብሄሮችን በስሩ አድርጎ በተነጻጻሪ በዘመናዊት ኢትዮዽያ ታሪክ ግዙፍ አካባቢ እና በርካታ ብሄሮችን በስሩ ያደረገ በመሆኑ የገጠሙትም ተግዳሮቶች በዚያው ልክ የተለያዩና ሰፊ ነበሩ። ሰፊ ቦታና የተለያዩ ብሄሮች በስርህ ሲኖሩና ያ ግዜ በተነጻጻሪ በህሊና ረገድ ነቃ ያለ ሲሆን የሚገጥምህም ችግር ይወሳሰባል። የችግር አፈታትህም የቀድሞውን ጨካኝ ልምድ የሚከተል ሲሆን ደግሞ ያን መሰሉ ድርጊት የሚያስከትለው ውጥንቅጥ ሰፊና ውስብስብ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።

በቀላሉ ሚኒሊክ ከኦሮሞ ብሄር ቢሆን ጥላቻው ከሸዋው ኦሮሞም ከባሌው ኦሮሞም ከጂማውና ከኦሉአባቦራው ኦሮሞም ከሀረሩም ኦሮሞ ይገዳደል ነበር። የብሄር ጉዳይ ቢሆን ያን ያክል ኦሮሞ ወዳጆችና ጋሼ ጃግሬዎች ሊኖሩት ባልቻሉ ነበር። ሚኒሊክ እኮ አብልጠው የሚወዱት የሰሜን ሸዋ ኦሮሞዎችና አማራዎች ናቸው። የጨለንቆው ጦርነት በሚኒሊክም በኩል ኦሮሞ የጦር መሪዎች እና ባለሟሎቹ የተሰለፉበት ነበር። 

ከዚህ ከፍ ብለን ሀቁን ስንጋፈጠው የሚኒሊክ ወታደሮች ጦርነቱን የገጠሙት አልገብርም ባንተ አልገዛም ከሚል ኦሮሞ ፊውዳል ጋር እንጂ ተራው ጪሰኛም አልነበረም። ጦርነቱን የተዋጉት ወታደሮችም ብሄራዊ ማንነታቸው ተሰምሮ በዚህ ኦሮሞ በዚያ አማራ ወይም ሌላ ብሄር አይነትም አልነበረም። በሁለቱም በኩል ኦሮሞ አለ። የሚኒሊክ ጦር ቅይጥ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ። ይሄ ሁሉ ግን እውነታ የአገዳደላቸውን እና የቅጣቱን አሰቃቂነት የሚቀይረው አይደለም። የሆነ ሆኖ ቅጣቱ ብሄርን ለመቅጣት ሳይሆን እምቢኝ አልገዛም ማለትን በሀይል ለመስበር በሰሜን ይሁን በደቡብ በምስራቅ ይሁን በምእራብ ስራ ላይ የሚውል ተግባር ነው። በመሆኑም መነሻው የብሄር ልዩነት እንዳልሆነ መናገር ይቻላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ንጉስ ሚኒሊክ እማይጠረጠሩ ስኬቶችም ነበሩት። ዘመናዊነት ወደ ሀገራችን የገባው ዘመናዊ የመንግስት አሰራር የተዋወቀው ትምህርት እና ሌሎቸ በጎ ነገሮችም የሆኑት በዚሁ ግዜ ነበር። በመሆኑም ለነዚህ መልካም ስራዎቹ ይመሰገናል። ልክ በመጥፎዎቹ እንደወቀስነው ሁሉ ማለቴ ነው። በወቀሳችም በሙገሳችም ግን የምንማረው እኛ ነን። የነሱ ግዜ ጠፍታለች። ከዚያ ግዜ ታሪክ መማርም መባላትም የኛ ፈንታ እንጂ የዚያ ዘመን ሰዎች አደለም። ችግሩ ጥንካሬው ሰላልሆነ የበጎ ነገሮቹ ማብራሪያዬን እዚህ ላይ ልግታው እና ወደዋናው የጽሁፌ ክፍል ልግባ።

የሆነ ሆኖ ይሄ እውነታ በታሪክ መነገር ያለበት እንዴት ነው? የሚለው ነው። እኒህን የመሰሉ የጦር ሜዳ ውሎዎች ጀግና ተብለው የሚቀርቡ መዋእሎች ናቸው? ወይስ ደግሞ በብሄር ጥላቻ ተፈርጆ የእንገንጠል ከቀሪው ህዝብ ጋር የሚያስተሳስር እትብት የለንም የሚባልበት ነው ወይ? እኒህ አተያዮች እና ማዳራሻዎች እማያስኬዱ ከሆነ ምን አማራጭስ አለን? እውን የታሪክ ንባባችን የተለያየው እውነቱን ስለምንፈልግ ነው? ወይስ ከደማችንና ከሰፈራችን ትርክት ተነስተን ታሪክን በፈለግነው መንገድ ስለምናቀርብ? የታሪክ አነሳሳችን አላማና ስሜትስ ሀቅ ፈላጊና ተማሪ ወይስ ስሜት አቀጣጣይ እና የጥላቻ ስብከት ጃኖ ሆኗል? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት በተከታዩ ጽሁፌ ልመለስ። ከዚህ በላይ ቢረዝም እንዳይሰለቻችሁ ሰግቼ ነው። ቀሪውን በቀጣዩ ጽሁፍ ላወጋችሁ እመለሳለሁ።

No comments:

Post a Comment