Sunday, March 24, 2013

የታክሲና የወር ቀለብ መሸፈን የቸገረን ባለ ድግሪዎች!


Hiwot Emishaw በፌስቡክ በምታስኮመኩመን ጽህፏ እንዲህ ብላ ነበር "አንዲት የተቻኮለች ሴት ልጅ አጠገቤ ስትቁነጠነጥ ግራ በመጋባት ጠየኳት የመለሰችልኝ መልስ ግን መልሼ እንድተክዝ አደረገኝ ያን ያህል ታክሲው ቶሎ እንዲሄድ የተጣደፈችው ብታረፍድ ከዚያው ለወር ቀለብ እና ለቤት ክራይ ከማይበቃት ደሞዟ እንዳይቆረጥባት በመስጋቷ መሆኑን ነገረችኝ" ይላል ጥቅል መንፈሱ።

ይሄ ትዝብቷ ሁላችንም ጓዳችንን መለስ ብለን እንድናይ ኪሳችንን እንድንፈትሽ የሚያስገድድ አይነት ነው። በርግጥም የአብዛኞቻችን ኑሮ ይሄው ነው። ይሄን መልሼ ማንሳት የመረጥኩት መተከዝ በቂ ባለመሆኑና ይህን መራራ ሀቅ ለመቀየር ማድረግ ስላለብን ቁምነገር ሀሳቤን ማጋራት በመፈለጌ ነው።

እውቁ ባለሀብት የሶፍትዌሩ ኢንጂኒየር ቢል ጌትስ እንዳለው ደሀ ሆኖ መወለድ አይነወርም። መወለድን መምረጥ አይቻልምና። መወለድን በምንም መልኩ መወሰን የተወላጁ ፈንታ አደለምና። ደሀ ሆኖ ማርጀትና መሞት ግን የያንዳንዳችን ምርጫ ውጤት ነው። ያ መሆኑም የሚያሰጠይቀው እኛኑ ይሆናል በዋናነት። ማለቴ ለመቀየርም ላለመቀየርም ኳሱ በኛ ሜዳ ነው።

ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት እድሉን ካገኙት ሚሊዮኖች መካከል በድግሪ ለመመረቅ የበቁት ጥቂቶች በቅጡ ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉ ከሆነ በርግጥም አገራችን የሚያሳፍር ኢኮኖሚ ባለቤት ናት። እኛም ዜጎቿ በአለማቀፉ ገበያ ተወዳዳሪና አሸናፊ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ የተሳነን በመሆኑ የምናሳፍር ነን። የሚያስቆጭ ውርደት የሚያንገበግብ ሀቅ ነው።

ኤኮሶም ሞቢል የአሜሪካው የነዳጅ ድርጅት የተጣራ የ2012 የሶስት ወር ገቢ አሁን ባለው ምንዛሪ መንዝሬው 288 ቢሊየን ዶላር ይሆናል። ይሄ እንግዲህ ከኛ ሀገራዊ የዘንድሮ በጀት ከመቶ ቢሊዮኖች በላይ የሚልቅ ነው። አመታዊ በጀታችን ከሶስት ወር የአንድ ትልቅ የንግድ ተቋም የተጣራ ገቢም እጅግ የሚያንስ ነው።

ተመሳሳይ ምሳሌ ብንወስድ የሳምሰንግ የተመሳሳይ ግዜ የሶስት ወር የተጣራ ገቢ 133 ቢሊየን ብር ገዳማ ነው። ይሄ እንግዲህ በአመታዊ ትርፉ ሳምሰንግ አራት ኢትዮዽያን የሚያክሉ አገሮች በየአመቱ ማስተዳደር ይችላል ማለት ነው።

የቢቢሲ አመታዊ የ2012 በጀት ለዚያውም በገጣማቸው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ ቅናሽ ተደርጎበት ወደ 96 ቢሊየን ብር ገደማ ነው። ይሄ ማለት ኢቲቪን ለሚመስለው የህዝብ ሚዲያ 60 ሚሊየን ገዳማ ህዝብ ያላት ብሪታኒያ የምትመድበው በጀት በሀገራችን የዘንደሮ በጀት ሲለካ በየሁለት አመቱ የሀገራችንን የአመት በጀት ይሸፍናል እንደማለት ይሆናል።

ሌላ ማነጻጸርያ እንውሰድ የብሪታኒያ ማእከላዊ መንግስት አመታዊ የትምህርት በጀት ባሁኑ ምንዛሪ ወስደነው ከ700 ቢሊየን ብር በላይ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ አመት በጀት ስሌት የአራት አመት የኢትዮዽያን በጀት መሸፈን የሚችል ገንዘብ ለትምህርት ዘርፉ ብቻ ይመድባሉ ማለት ነው። ይሄ ቁልጭ አደርጎ የድህነታችንን ልክ የሚያሳብቅ መረጃ ነው።

የጠቀስናቸው ካምፓኒዎችና ብሪታኒያ ሀገራችን የምትገኝበትን የድህነት ጥልቀት የሚያመላክቱ ናቸው። እናም ማፈር መተከዝ የሚገባ ነው። ወደ እልክ እና ቁጭት ካለተቀየረ ግን አይረባንም። አስተዋጿችን እስካላቀ አቅማችን እስካልጎለበተ እና የተሻለ ምርትና አገልግሎት መስጠት እስካልቻልን ድረስ ከዚህ መራራ ህይወት የሚያስለቅቀን ስለማይኖር።

ከአንድ ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚከፈላቸውን የቢቢሲ ምርጥ ጋዜጠኞች የሚመጥን ደሞዝ ለማግኘት እነሱ የሚያቀርቡትን ያክል ጥራት ያለው የሚዲያ አገልግሎት ማቅረብ እና ግዙፍ ገቢ መሰብሰብ ይጠይቃል። እናም የማይበቃን ደሞዛችን የማያረካ አገልግሎታችን እና ምርቶቻችን ግልባጭ መልክ ነው። ገቢው የመረረውና ኑሮው ያማረረው የኔ ቢጤ አቅሙን ሲልም ስራውን በላቀ ጥራት የመፈጸምና ራሱን ተፈላጊ የማድረግ በዚሁ ሂደት ጥቅል ሀገራዊ አቅማችንን የማሳደግ ሀላፊነት አለበት።

እናም ከመራራው ኑሯችን ጀርባ ከደቃቁ ደሞዛችን ጀርባ ያላደገው ብቃታችን የማያምረው አገልግሎትና ምርታችን ፊታችን ይደቀናል። ስለሆነም የምንመኘውን ኑሮ የሚመጥን ጠንካራ የስራ ባህል እና አርኪ ውጤት መፍጠር አለብን። ያን ለማድረግ ደግሞ አቅማችን በተከታታይ መገንባት የሚሰቀል ሰርተፊኬት ለመያዝ ሳይሆን ለደንበኛ የሚመጥን ውጤት ማቅረብ የሚያስችል ትምህርት መቅሰም ያሻል።

ስር የሰደደውን ድህነታችንን ወይም የማያረካውን ኑሯችንን ለመቀየር ያለው መፍትሄ ከመተከዝ ከፍ ይላል። የላቀና ተከታታይ ስራም ይጠይቃል። ደቃቃ አገራዊ ኢኮኖሚ ለተመሳሳይ ሰራ የሚከፍለው ክፍያ ከለማ ድልብ ኢኮኖሚ እጅጉኑ አናሳ መሆኑ ሁሌም ኗሪ ሀቅ ነው። ማማረር አይፈታውም ወቀሳ አይፈታውም ቁጭትም አይፈታውም። ከቁጭት የሚመነጭ የታለመ ተከታታይ ጠንካራ ተግባር ግን በሂደት አሳምሮ ይለውጠዋል።

አብሮን የኖረው አሮጌው ድህነት በአሮጌው ተግባራችን እንደማይፈታ በመራራው ኑሯችን አሳይቶናል። አዲስ ትጋት አዲስ አተያይ አዲስ ተግባር አዲስ እልክ ያሻናል። የምሬት መድሀኒቱ የተመረጠ የታቀደና ተከታታይ ተግባር ብቻ ነው። አዎ በውድቀትም መሀል ነጥሮ እንደኳስ የሚነሳ የማያባራ ተግባር። ትካዜ የምን ይሻለናል መጀመርያ ነው ትካዜ የመፍትሄው ጫፍ አደለም የሚል እምነት አለኝ።

ከትካዜ የሚመነጭ እቅድ ከትካዜ የሚመነጭ እልክ ከዚሁ የሚንደረደር የማያሰልስ ተግባር መሰረታዊ ይሆናሉ። አለበለዚያ እስከዛሬ የኖርነውን ድህነት ገና ነገም በከፋ መልኩ እያጣጣምነው እንቀጥላለን። ድህነት የሚበቅለው በያንዳንዳችን የተበላሸ ምርጫ በዚያው ከሚመራው ተግባር እና በዚያው ተግባር በሚታነጸው ድግግሞሽ ወለድ ተልካሻ ልምድ ነው። ድህነት የሚከስመውም ያ ደሀ ልምድ ባለጸጋ በሆኑ ልምዶች የተተካ እንደሆነ ነው።

ሄዊ ትካዜውን እዚህ አድርሼዋለሁ አንቺ ወይም ሌላ ሰው ደግሞ ትንሽ ፈቅ አድርጉት። ድህነትን እንግፋው ጎበዝ ይናዳል!
ይቆየን!

Thursday, March 21, 2013

ለምን ይዋሻል!


አንዳንድ ሰዎች እውነት ይነገር ይሉናል ብዙም ሳይርቁ ግን በሚሹት ጉዳይ ብቻ ካልሆነ በተቀረው ይክዱናል$
እውነት ነው መለስ ንጹሃ ባህሪ አደለም ያንም የሚል እብድ የለም  የላቀ የአመራር ብቃቱ ግን በምንም መልኩ አጠያያቂ አይሆንም$

ለምሳሌ የአባይ ግድብ ጉዳይ ሲነሳ አንዳንድ ወዳጆቻችን የለም ይሄ ፕሮፖጋንዳ ነው ታስቦበት የሆነ አደለም ይሉና የዚህን ጀግና አስተዋጾ ሊያሳንሱት ይሞክራሉ$ በርግጥ በቁምነገሩ ከዚህ ገለጻቸው ዋሾነታቸውን ካልሆነ በቀር የሚያሳብቅላቸው ሌላ ነገር ያለ አይመስለኝም$

ለመሆኑ መለስ ዜናዊ ምን አስልቶ ነበር ከአስርት አመታት በላይ የፈጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በናይል ኢኒሼቲቭ ዙርያ ሲያካሂድ የነበረው የአካባቢውን ሀገሮች አስተባብሮ ሲሰራ የነበረውና በፍትሀዊ የውሀ ክፍፍል ዙርያ የቀጠናውን አገሮች የሚያስማማ ውል ለማሰር ውጤታማ ስራ የሰራውን ምርጥ የዲፕሎማሲ ስኬቶቹን የትኛው ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ጥለን ነው አባይ ፕሮፖጋንዳ ነው ብለን ልንናገር የሚቃጣን$

በርግጥ ይህን የሚከራከሩ ግለሰቦች የዚህ ምጡቅ ስብእና ቁመና በሞትም በኋላ እንደሚያስፈራቸው በቅጡ ያልታነጸች ፖለቲካዊ አተያያቸውን እንደሚንጣት እረዳለሁ$ ያም ሆኖ ግን እውነን እውነት ማለት እኮ ለራስ ነው$ ጎበዝ በትግል ሂደት ትልቁ ነገር ሊታመን የሚችል ስብእና እኮ ነው ማለቴ መለስ ጻድቅ ነው ማለት ውሸት የሚሆነውን ያክል የመለስን የተራራ ያህል የገዘፉ ሀገራዊና አለማቀፋዊ ስኬቶችም መካድ ያው ወሸት ነው ማለቴ ነው$

በምን ሂሳብ ነው ግብጾቹ ስለተራበሹና አመጹ ወደኛም እንዳይጋባ በመስጋት ነው ተብሎ የሚወራው በርግጥም ይሄ ታታሪ መሪ ለህዝቡ ከምርጫው ማግስት የገባውን የላቁ ልማቶች የማሳካት አጀንዳ እና በወንዙ ላይ ለአመታት የተደረጉ ድርድሮቹን ተከትሎ የሰራው ታሪክ በደማቅ የሚመዘግብለት ግዙፍ ስኬቱ ነው$

ሌላው የሚሰማው ደግሞ ኢህአዴግ መለሰን በማሞካሸት ባዶ መቅረቱን እያወጀ ነው የሚለው ነው$ ይሄም ያው የዚህን ታላቅ መሪ ስብእና መደነቅ በመጥላት የሚናፈስ ጠማማ ወሬ ነው የሰራው ከሆነ የተወራለት ምን ችግር አለው ሁለተኛ ደግሞ በአመዛኙ በሁሉም ስራዎች ላይ አሻራው አለ ማለት ሌሎቹ ብቃት የሌላቸው እቃዎች ናቸው ማለት ነው ያለው ማነው$
እንደው ደርሰን ቋሚዎቹን ለማድነቅ የፈለግን በማስመሰል የዚህን ትጉህ መሪ ስኬቶች ላለመስማት የምናደርገው ሌላው ጥረት ነው$
በየትኛውም ሚዛን በለስን እና ተከዜን በራሱ ወጪ አቅዶ በራስ አቅም ግድብ መስራት እንደሚቻል ያሳየና ያን ልምድ ይዞ ወደላቀው ስራ የተሸጋገረን ልሂቅ ማጣጣል ለዚያውም አንጸባራቂ ስኬቱን እያጣጣሉ የምር ይደብራል ማለቴ ዋሽቶ ከመቃወም በትክክልም ደካማ ጎኑን በመጥቀስ መርታት አይሻልም$

ለነገሩ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎቹ በአግባቡ የተቀመሩ በመሆኑ ለመርታት አይመቹም እሱ የተለየ ፍጡር ስለሆነ ሳይሆን መርታት ያልተቻለው በርግጥም ፖለቲካዊ አስተምሮዎቹና ፖሊሲዎቹ በትክክል የዚህችን አገር ችግሮች በአስተማማኝ ሁኔታ መፍታት የሚያሰችሉ በመሆኑ ነው$

ለነገሩ ለሀገሩ አስቦ የሚቃወም ሰው ሲገባው የሚቃወመውን እና የሚያቀርበውን የተለየ አማራጭ እያጠራ ይሄዳል ያን እረዳለሁ$ የማይገባኝ በቃ እንዲያው ለመቃወም እንዲያው ለማጠልሸት በመፈለግ የሚዋትቱት ወዳጆቼ ጥረትና ግዜ መባከኑ ነው ይሄ ጥረታቸው በርግጥም አገር በምትጠቀምበት ጉዳይ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ምንኛ አገር በጠቀመ ነበር$
ከተከዜ እስከ 200 ከበለስ እስከ 460 ከስካሁኖቹ ጊቤዎች ከሁለት ሺ በላይ እና ከአባይ እስከ 6000 ሜጋ ዋት ሀይል ለማመንጨት የሰራ ሰው በስኬቱ ማጣጣል የጤና ነው ይሄ እኮ ሲደመር የንፋስ ሀይሎችን ጨምረን ወደ ዘጠኝ ሺ ሜጋ ዋት እኮ ነው ጎበዝ$

በየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ይቅርና በየትኛም አለማቀፍ መስፈርት ቢታይ ይህ መሪ በርግጥም የውጤት ሰው ህዝቡን መውደዱን በቃሉ ሳይሆን በተግባር ያሳየ የስራ ጀግና ነው$ ቆራጥ መሪነቱን በጥይት እብሪት ሳይሆን በሚቆጠሩ የልማት ስኬቶቹ የከተበ የህዝብ ልጅ የህዝብ ልጅነቱን ችግር አለ እያለ በመዘመር ሳይሆን ለባሰው ችግር ለወሳኞቹ ችግሮቻችን መፍትሄ እየቀመረ እየተገበረ ከተግባር እየተማረ ስህተቱን በአደባባይ እየገመገመ ለሀገር እየነገረ ሀገርን ወደማይቀለበስ የእድገት አዙሪት ያስገባ ጀግና ነው$

ስኬቶቹን የምንቆጥረው ዛሬ ላይ ችግር እንዳይኖር አድርጓል በሚል መንፈስ አደለም ሊሆንም አይችልም ስኬቶቹን የምንተርከው መፍትሄ ካበጀላቸው መሰረታዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎቻችን አንጻር ነው እንዲህ ያለ ጀግና ስኬቶቹ ዛሬ ላይ የሚመዘኑ ብቻ አደለም የላቁ ዘመን ተሻጋሪ ስኬቶቹ ገና በመጪው ግዜ እየተተነተኑ የሚገላለጡ ናቸው$

ይሄን የምንለው አፈር እንዲቀለው ወይም አንዳንድ ወዳጆቻችን እንደሚሉት ይሄን ስላልን ሆዳችንን ልንሞላ ብለን አደለም ይሄን የምንለው የጀግኖቻችንን ስኬቶች በመካድ የሚገኝ ሀገራዊም ግለሰባዊም ፋይዳ ስለለ እንዲያውም ይህን ከመሰሉ ትጉሀን የምንማራቸውን ውብ ልምዶች እንዳናጣ በማሰብ ነው$

እሱማ ጊዜውን በመረጠው አላማ ኖሮት ተሰናበተን ቁምነገሩ ለቋሚዎቹ ነው$ የምር ቁምነገሩን ለማወቅ ከሆነ እየተወያየን ያለነው አዎን መለስ አባይን የደፈረ አዎን መለስ አይቻልምን የደፈረ አዎን መለስ በውጭ ብድር ካልሆነ በቀር አይሞከርም የተባለውን የዘመናት ካቦ የበጠሰ ጀግና ነው አዎን መለስ በምርጥ ተደራዳሪነቱና ንግግር አዋቂነቱ የአካባቢውን ሀገራት ለፍታዊ ውሀ ክፍፍል ያበቃ ጀግና ነው ያን ተከትሎም የተጋለትን ሀገራዊ ኢላማውን አባይን ለጥቅም የማዋል አጀንዳ 6000 ሜጋ ዋት ከሚያመጨው የህዳሴ ግድባችን ያስጀመረው$

አዎን ባለ2000 ሜጋ ዋቶቹን ሌሎች የአባይ ግድቦች ደግሞ ይሄን ስንጨርስ እኛ እንሰራቸዋለን ምሳሌህ ተማሪዎች አሉት አብዝተው አስፍተው ይተግብሩታል የምር የስካሁኑን ስኬት ያጣጣመ አገር የቀሩ የድህነት ምሬቶቹን ለመቀልበስ ይተጋል አስተምሮህ ከኛ ጋር ይኖራል ላንተ ብለን ሳይሆን ነገን የተሻለ ለማድረግ አዎን ያንተም አላማ መለስ ዜናዊ ደረትህ እንዲቀላና ሆድህ እንዲሞላ አልነበረም እና ይሄ የተጋህለት ህዝብ የተመኘውን እስኪያሳካ የሚተጉ ጎበዞች እንዳሉ እናምናለን$

Wednesday, March 20, 2013

ዘረኞች ታሪክን ለቀቅ ! ጠባቦች ከታሪክ ፈቀቅ!


ታሪክን የሚማሩበት ተመሳሳይ ስህተት አይሰሩም ታሪክን የሚማሩበት ሰዎች ከደም አይቆራኙም ቁምነገራቸው ከተከሰተው ታሪካዊ ጥሬ ሀቅ ነው$

ታሪክን ከደምና ስጋቸው ተነስተው የሚመዝኑ ሰዎች ታሪክ ተሳስተዋል ብሎ ከሚከሳቸው ሰዎች የተለዩ አደሉም$ እንዲህ አይነት ግለሰቦች ሀቃቸው ከደም የሚቀዳ በመሆኑ ሁለት ፊውዳሎችን በታሪክ አይን መዝኑ ቢባሉ ለደማቸው የቀረበውን ጻድቅ ከደማቸው የራቀውን ጭራቅ የማድረግ ልምድ አላቸው$

የዚ መነሻው መገምገሚያው ጥሬ ሀቅ አላማው ደግሞ ትምህርት አለመሆኑ ነው$ የታሪክን ግዙፍ ገጾች የሚገልጡት ባላንጣቸውን ለማጣጣል በማለም እኛ የሚሉትን ደማቸውን ደግሞ ለማዳነቅ በመሆኑ ነው$ ለነዚህ አይነት የታሪክ ሰዎች ታሪክ ጥይታቸው እንጂ ዛሬን የሚያንጹበት ነገን የሚተልሙበት መነሻቸው አደልም ግብአታቸው አደለም$

ታሪክን የነሱ አዲስ ደማዊ ትርክት ይለውጠው ይመስል ታሪኩን እያዛቡ ሲነግሩን የትላንቱን ባለጌ ሊያሳዩን ተፍተፍ ሲሉ የዛሬዎቹን የታሪክ እድፎች እየታዘብን እንደሆነ እንኳ አይረዱም$ ከትላንቶቹ ስህተቶችና ብልሹ ግለሰቦች የበለጠ የነሱ የዛሬዎቹ አሜኬላዎች ቁመና እንደሚያሳሰበን አይገባቸውም$

የታሪክን እድፍ ሊያሳዩን ሲጥሩ ማደፋቸውን የሚያሳብቁን የዛሬ ታሪክ የደም ቀላሚዎች ታሪክን ለትምህርት ታሪክን ዛሬን ለማነጽ እንዲያወሱት እናስታውሳቸዋለን$ ባዳፋ መነጽር ታሪክን እያዩ ሀቁን አቀርባለሁ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው$ የሚቀድመው በደም የቀለመ የታሪክ መነጽራቸውን ማጥራት ወይም የጠራ አዲስ መነጽር ማጥለቅ ነው$

የትላንትና አንበሶችም ሆኑ ውሾች ዛሬን አያንጹትም አያበላሹትምም$ የዛሬዎቹ የተበከሉ የታሪክ ውሻዎች ግን ዛሬን እንዳይበክሉት ነገን እንዳያጨፈግጉት ሀይ መባል አለባቸው$ እውን የታሪክ ተማሪ መሆን ከብዶ ነው እንዲህ የታሪክ ሙርከኛ ሆነን ትላንትን ከፊሎቻችን ለፖለቲካችን ማራገብያ ደሞ ከፊሎቻችን ዘረኛ አቋሞቻችንን ለማንጸባረቅ ይህን ያህል የምንባትለው?

ሀቁ ይህ ነው$ ታሪክ ታሪክ ነው$ ያማረም የከፋም አስተያየታችን አይቀይረውም አስተያየቶቻችን ግን የባለአስተያየቱን ቁመና እና ሀሳብ ያሳብቃሉ$ ቢያንስ እረ ሰው ይታዘበናል ብለን ከመቀባጠር እንቆጠብ$ ታሪክ ለዘረኝነት ታሪክ ለርካሽ ፖለቲካ ማራመጃነት ታሪክ ለመቀባጠር ባይሆን$

የምር ከታሪክ ብንማር ታሪክ ብንሰራ ታሪክ በዚህም ቢያስታውሰን ይሻላል$

Tuesday, March 12, 2013

Religion not a criteria for Employment


Zeryihun Kassa
Some Ethiopian businesses seem recruiting employees with same religious affiliation. Businesses set up by a Muslim, Orthodox or Protestant Christian appears to take in employees who practice same religion.

I don't get it. Had they been serving their religion it very much works, but they are serving customers with whatsoever faith. How on earth they feel and believe customers would be happy with this kind of virtual bias in the name of religion which in fact expects them to love everyone with equal heart.

I hope the public will punish such businesses by boycotting buying their services and products. Such practice is a disgrace in a country known for its religious tolerance and neighborliness among people with differing religions.

An employee should only be recruited for excellence and skills not for religious affiliation. It is time to correct this malice from the very beginning.

Any job doesn't call for a particular individual. It rather needs someone who is able to properly perform it. It is about getting a job done and getting customers satisfied. In a way it is not about having employees who come to terms with your religious belief.

At least Ethiopia is not the place for such bad tendencies and practices. I am an orthodox and I don't like a fellow orthodox with a business firm to employ an individual for just being orthodox. Individuals are enough to apply for a job just for being Ethiopians and for having the skills that the work demands.

Those who want to have organizations with their own religious followers should establish their business inside the fences of their worship places if at all business works that way.

It is such tendencies that grow into solid segregation agendas in time. Every time such rogue practices come into play it is good to kill them at the very onset than trying to eliminate it after it gets stronger.

Now is then the time to advocate for elimination of it and it is also time to boycott businesses which do so for no good reason other than discrimination.

Saturday, March 2, 2013

የአድዋን የድል መንፈስ እንቀስቅስ



አድዋ የቆራጥ ኢትዮዽያውያን አቅም በአግባቡ ከተመራ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ያመላከተ ገድል ነው$ በርግጥም ሰይፍ ከዘመናዊ መሳርያ ጋር ፊትለፊት ተጋፍጦ በአሸናፊነት የደመቀበት ነውና$ ያ ድል ፍትሀዊ የትግል መነሻና ቆራጥነት በተባ አመራር እስከተያዘ ድረስ አሸናፊነት የማይቀር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው$

ከአደዋ ምን እንማር
መንግስታዊ በሆነም ባልሆነም ተቋም አቅማቸው በፈቀደ የሚሰሩት የዛሬዎቹ ጀግኖች መመስገን ያለባቸው ሆኖ በአመዛኙ የዛሬዎቹ ኢትዮዽያዊያን ችግሩ ያለበትን ትክክለኛ ቦታ የማከክ እና የማረም ችግር አለብን$ አንደኛ ብዙዎቻችን የተሰጠንን ሀላፊነት ቦታው ምንም ይሁን በተለያዩ ኩርፊያዎችና ሱሶች ተጠምደን በአግባቡ የማንወጣ ነን$ ሌሎቻችን ደግሞ ሃላፊነታችንን በአግባቡ የምንወጣ ከቅጥራችን ውጭ ሰው እንኳ ቢገደል እንዴት እንዲህ ይሰራል ብሎ የመጠየቅ ወኔም የይመለከተኛል መንፈስ ያልፈጠረብን ግድየለሾች$

ደሞ ሌሎቻችን ኪሳችን የሚገባ ፍርፋሪ የሚገኝ ከሆነ ባልደረቦቻችንን ለማጥፋት እና ደንበኛን ከመዝረፍ የማንመለስ ጅቦች ነን$ እንዲያው የሚፈጸመው በደል የሚቆረቁረን ብዙዎች ደግሞ በየጥጋጥጉ ከማማት ባለፈ ፊትለፊት ስህተቱን የፈጸመውን ሀላፊ ተጠያቂ የማድረግ የመወያየት ወኔ ያልፈጠረብን ፈሪዎች$ ያው ግን ዝም ብለዋል እንዳይባል ምን አይነት ባለጌ ነው ባክህ እንዴት እንዲህ ይደረጋል የሚል ቅኝት በየሻይ ቤቱ የምንዘምር$ ደፈር ያልነውም የሚመለከተው ሀላፊ ተጠያቂ የሚሆንበትን ህጋዊ መንገድ ተከትለን በመድረክ ከመርታት ይልቅ በአንድ በሁለት ድንፋታ አድሏዊነት ሙስናና ዘረኝነት እንዲፈታ የምንመኝ የዋሆች ነን$

ለውጥ እንደ አድዋው ውጊያ ያንተ የሆነውን ለማስጠበቅ የህዝብ የሆነው ለህዝብ ይድረስ በሚል መንፈስ መስራትን ይጠይቃል$ እናም እንዲህ ያለ ህዝባዊ አላማ አንግተን ስናበቃ ደሞ አላማችንን የሚመጥን ትጥቅ አቅም ጉዳዩ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ በቁርጠኝነት የመቀጠል ድፍረት እና ዝግጁነት ይፈልጋል$

በየተቋማቱ የሚታዩትን ችግሮች በየመስሪያ ቤቱ ያሉ ሰራተኞች ካልፈሩ በቀር ከማንም በላይ ያቋቸዋል$ ከሆነ ደግሞ ስርአት እና ህግን ተከትሎ የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍሎ መታገልና መፍታት ነው$ የገንዘብ ሚንስትርን ችግር ለመፍታት የውሀ ሚኒስትር ሰራኞች አይሰለፉ የሸቀጣሸቀጡን ችግር በግንባታ ዘርፍ የተሰማራው ባለሀብት እንዲፈታው አይጠበቅ መሆን ያለበት በያለንበት ለደንበኛ የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ ሂደቱ የሚጠይቀውን ዋጋ መክፈል ነው$

ይሄ አገር የኖረው መሞት የሚጠይቀውን አድዋን በተጋፈጡ ጀግኖች ነው$ በርግጥ ለማን ብዬ ነው የምሞተው የሚሉ ብልጣብልጥ ነን ባይ ፈሪዎች በዝቷል$ ዛሬ ለመሆኑ ትግል የሚጠይቀውን ዋጋ የሚከፍሉት እነማን ናቸው ሁሉም ጥግ ይይዛል$ ሁሉም ለመኖር አይመችም በሚለው አገር አርፌ ልጆቼን ለሳድግ ይላል$ የማይመች ከሆነ ልጆቹስ ቢያድጉ ምን ዋጋ አለው ትግሉ መካሄድ ያለበት እንዲያውም ለልጆቻችን ሲባል ነው ለምቾታቸው የምትመጥን ሀገር ለመፍጠር$

መንግሰታዊ መዋቅሩና ህጉ የሚፈቅድልንን የመጠየቅ ፍትሀዊ አገልግሎት የማግኘት መብታችንን እንኳ ለመጠየቅ እዚግቡ የማይባሉ በተጨባጭ ስርአቱን መጠምዘዝ የማይችሉ ቢሮክራቶችን ፈርተን ጥግ ይዘናል እኮ$ ጎበዝ በዚሁ ባህሪ እኛ አሁን የአድዋ ልጆች የአድዋ አክባሪዎች ነን አድዋ እኮ ጥይት ለመጠጣት የማይፈሩ ጀግኖች ሀውልት ነው$ አድዋ እኮ የጥቁር አሸናፊነት ምልክት ነው$

በመሀላችን ያሉ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ተከታትለን ህጉ በሚፈቅድልን አግባብ ለመፍታት የማንነሳሳ ከሆነ የምር ለፍርሀታችን ምን ወሰን አለው$ በርግጥ ዛሬም ለጥይት ደረቱን ይሰጣል ኢትዮፕያዊው$ ግን ሁሌም ለድንበሩ ሲል መሆኑ ነው ችግሩ$ ድንበር ለመጠበቅ ጥይት የሚጠጣው ድፍረት የተመቸ የመኖሪያ የመስሪያ አካባቢ እና ለህዝቦቿ የምትመች አገር ለመፍጠር በሚደረገው ጉዞ ላይ ለምን በንቃት አይሳተፍም$

ይሄ ሀገርን ከውጭ ጠላት የመጠበቅ ጥንካሬ ለምን ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመፍታት ረገድ አይደገምም$ ምንም የሚጠይቅ ሰው የለም በየተቋሙ የሚታገል የለም እያልኩ አደለም$ ሆኖም አብዛኛው በፍርሀት የተሸበበ በመሆኑ በድምጽ ብልጫ በሚወሰን ጉዳይ ላይ እንኳ እንዲህ አይነቶቹን ታጋዮች ለመደገፍ እስከማይችልበት ሽባ መሆኑ ነው$ ህጋዊ በሆነ መንገድ መብትን ለማስጠበቅ ካለመንቀሳቀስ በላይ ምን ሌላ ፈሪነት ይኖራል ጃል$

የሚገርመኝ ደግሞ ፊትለፊት የምንሰራበትን ተቋም የስራ ሀላፊዎች እንኳ መጋፈጥ ለመቻል የየራሳችንን ፍርሀት ሳንረታ ሁሌም የሚቀናን በቸገረን ቁጥር የትችት ካብ መከመር ነው$ እውን ትችት ሌቦችን ያጠፋል? ወይስ እውን ዘረኛ በትችት ህብረብሄራዊ አስተሳሰብ ይኖረዋል? ወይስ እውን ክፉ ቢሮክራቶች በሻይ ቤት ጥጋጥግ ወሬ ይናዳሉ?

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በየተቋሙ የሚገኙ ክፉ ቢሮክራቶች የልብ ልብ የተሰማቸው በየጥጋጥጉ ከማውራት ባለፈ የተደራጀ የተጠና እና ተከታታይነት ያለው ትግል እንደማናደርግ ማወቃቸው ነው$ ተወው ያውራ ከስብሰባ አዳራሽ ሲወጣ ይረሳውል እኮ ነው የሚሉን$ እናም ህጉ የሰጠንን መብት ተከትለን የማንንም ክብርና መብት ሳንጥስ መብታችንን ማስከበር የማን ስራ ነው የኛ ወይስ ሌቦች ሙሰኞች የምንላቸው ሰዎች

ሌላው ገጽታ ለምን መንግስት አይፈታውም የሚለው ነው$ መንግስት ችግሮችን የመፍታት እድሉ ከፍ የሚለው እንዲህ በተደራጀ መንገድ የሚታገሉ በሳል ሰራተኞች ኗሪዎች እና ባለሀብቶች ባሉበት እንጂ እኛ እንደ ዜጋ ባንቀላፋንበት ሊሆን የሚችል አደለም$ መንግስት እንዲያገለግሉን ያስቀመጣቸው ሰዎች አይደሉም እንዴ እያጠፉ ያሉት ስለሆነም ተከታትለን ቅደም ተከተሉን ጠብቀን የሚበሉንን አፎች እና የሚቧጭሩንን ጥፍሮች ማስቆረጥ ያለብን እኛው ነን$

የአድዋው መንፈስ  ይሄ ነው$ ችግርን በትችት ናዳ የመፍታት ሳይሆን ችግርን በሚፈለገው የትግል አይነት የሚፈልገውን መስዋእትነት ከፍሎ የመፍታት አቀራረብ$ ከያኔዎቹ ጀግኖች አገር የሚማረው ይህን ነው$ በቁርጠኝነት ችግሮችን መጋፈጥ በጽናት ትግሉን በድል ማጠናቀቅ$