Friday, October 11, 2013

ፖለቲካችን አጓጓን ወይስ አስቄመን



ፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የሚያቀርቡ ሲሆኑ ህዝብ በአዲስ ጉጉት ይወጠራል፡፡ በአዲስ ተስፋ ይሳባል፡፡ አዲሱ ምርጫ ስቦት ነባሩን ገዢ ፓርቲ በአዲስ ስለመተካት ያሰላስላል፡፡ ቃል የተገባለት የተሻለ ነገር አሁን ያለውን ጥሩ አማራጭ ለመተካት ያነሳሳዋል፡፡ ይሄኔ ነው ማጓጓት የሚቻለው፡፡ ይሄኔ ነው አማራጭ መኖሩ የሚታወቀው፡፡ ጉጉት የተሻለ ነገር ከመናፈቅ የሚፈጠር ስህበት ነው፡፡

እንዲህ ያለ የሚያጓጓ አማራጭ ባለበት መከፋትን በመጠንሰስ ቂም በቀል በማስረጽ የሆን ተብሎ ተበደልክ ተገለልክ ስብከት በማስለፈፍ ድጋፍ መፈለግ ይከስማል፡፡ ቁምነገሩ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ ያን የሚያሳካው መንገድ ደግሞ የተዋጣላት እና በወጉ የተቀመረ ፕሮግራም ይሆናል፡፡

እሚያጓጓ ፕሮግራም ያበጀ ፓርቲ በተበዳይነት ስሜት (ቪክቲም ሜንታሊቲ) ወይም በቂም በቀል ፖለቲካ የሚጣድበት ምንም ምክንያት ስለማይኖረው አብይ አጀንዳው ሳቢና አስተማማኝ ፕሮግራሙን በስፋት በማስተዋወቅ ድጋፍና የምርጫ ካርድ መግዛት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡

ይህን መሰሉን በራስ መተማመን እና ልምድ የተላበሰ ፓርቲ ማቋቋም ደግሞ የበሰሉ ፕሮግራሞችን መንደፍ ሀገራዊ ውርደቶቻችንን የመቀየር እና ሀገራዊ ድሎቻችንን የማስቀጠል በመሆኑ በዋናነት ከተቃውሞ ጋር ሳይሆን ሀገራዊ መፍትሄዎች እና ሀብት ፈጠር አቅሞች ከማዳበር ጋር ይሰናሰላል፡፡

በመሆኑም ሆድ የማስባስና ተፎካካሪ ፓርቲን የማስጠላት ድውይ ፖለቲካ ዋናኛ መነሾ አማራጭ አልባ ሆኖ በጥላቻ ፖለቲካ ተመርዞ ፖለቲካውን መቀላቀል ነው፡፡ ይህን መሰሉ ፖለቲካ ለሀገራቸው ሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ ሳይሆን በፖለቲካ መድረኩ ላይ ለሚያዩዋቸው ግለሰቦች ያላቸውን ጥላቻ ለመግለጽ በሚገቡ ግለሰቦች የሚፈጸም ነው፡፡

ፕሮግራም የሌለው ቡድን ደግሞ የሚቃወመውን ቡድን ፕሮግራም እያነሳ ከማላዘን የተሻለ አማራጭ ሊኖረው አይችልም፡፡ ቂም በቀልና ጥላቻ የመዝራት ተልእኮ ይዘው በፖለቲካው መድረክ የሚርመሰመሱ ቡድኖች አብይ መገለጫም ይሄው ነው፡፡ ማጣጣል ማሳበብ መውቀስ ይህን መሰሉን ወሬ ነጋ ጠባ መደጋገም እና ይሄው የፖለቲካ ፕሮግራም ሆኖ ኢህአዴግ ባያጭበረብር ኖሮ በዝረራ ይሸነፍ ነበር እያሉ መጎረር ነው አጀንዳቸው፡፡

በመሆኑም የበሳል ፖለቲካ አንዱ መገለጫ ለሀገራዊ ችግሮች ያበጃቸውን መፍትሄዎችና ለሀገራዊ ሀብቶች መፍጠርያ ያበጃቸውን አማራጮች በማስተዋወቅ ህዝብ በፕሮግራሞቻቸው በመተማመን በሚልቀው አማራጫቸው ጉጉት አነሳሽነት እንዲመርጣቸው ማስቻል ነው፡፡

ይህን መሰሉን ባህሪ በማዳበር እንዲህ አይነቱን ባህሪ የሚያላብስ ፕሮገራም በመቅረጽ ኅዝብን በጉጉት የሚስቡ ፓርቲዎች ለማግኘት መብቃት ይገባል፡፡ ይቻላልም፡፡ ቁምነገሩ በሀገራዊ ችግሮቻቸን መፍትሄ እና ሀብት ፈጠራ ዙርያ ለመስራት መሰባሰብ መቻል ነው፡፡

Tuesday, October 8, 2013

#‎አማራጭ‬ ፓርቲ #አማራጭ ፕሮግራም ነው



የፖለቲካ ፓርቲ ብዝሀነት አብይ አላማ ለአንድ ሀገር ህዝቦች የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮችን ማቅረብ ነው፡፡ የተቃውሞ ፖለቲካ ከገዢ ፓርቲ አንጻርም ከተመዘነ ሌላ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም:: ገዢ ፓርቲው እያስገኘ ካለው ስኬት የተሻሉ ስኬቶች ማስመዝገብ የሚችሉ የፖሊሲ አማራጮች የፖሊሲ አማራጩ እምብዛም ልዩነት ከሌለው ደግሞ የተሻለ የመፈጸም አቅም እና ስነምግባር ያለው ፓርቲና አባላት በማደራጀት ህዝቡ ይህን በመሰለው ፓርቲ አማራጭ የማስፈጸም አቅም ዙርያ መተማመን እንዲፈጥር ማድረግ ነው፡፡

ይህን በመሰለ አማራጭም ሰከን ብሎ ገዢ ፓርቲን መርታት በሂደትም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርአት መመስረት ይቻላል፡፡ ይህን መሰሉን ጠንካራ ፖለቲካዊ ስርአት ለማቋቋም ደግሞ ቀስ በቀስ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

ያን የመሰሉ እሴቶች የሚኖሩን ሰከን ያሉ አማራጮች በማቅረብ የተጠመዱ ፓርቲዎችና መልእክቶቻቸው እኒህን አማራጮች በማስተዋወቅ ዙርያ ያጠነጠኑ ፓርቲዎችን መገንባት የቻልን እንደሆነ ነው፡፡ በወሳኝነት ይህን የመሰለ ቁመና የሚኖራቸው ፓርቲዎች አብይ ስራ ውስጣዊ ቁመናቸውን ማነጽ የጠሩ ፕሮግራሞችን መንደፍ በነደፏቸው ፕሮግራሞች ዙርያ መልእክቶች ማበጀት እነዚሁኑ መልእክቶች በትጋት በማሻሻጥ ላይ ያተኮሩ ይሆናሉ፡፡

ያኔ ነው በሂደት በህዝቡ እምነት እየተቸራቸው አማራጮቻቸው መወያያ እየሆኑ የአባሎቻቸው ቁመና ከሌሎች አባሎቸ ቁመና አኳያ እየተመዘነ በእንድ በኩል የዳበሩ ብቁ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት የተለያዩ አቋሞች የሚራመዱበት ዴሞክራሲያዊ እሴቶቹ የጎለበቱበት የፖለቲካ ብዝሀነት በሌላ ጎኑ ደግሞ ይህን በመሰለው ሂደት አቀጣጣይነት የዳበረ የማገልገል መንፈስ አፈጻጸም እና ልማት የሚስተዋልበት መንግስታዊ እና ድርጅታዊ መዋቅሮች እየተገነቡ የሚሄዱበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

አሁን ያለውን ሁኔታ ስናጤን ግን ከስልሳ እስከ 90 የሚደርሱ ፓርቲዎች እናስተውላለን፡፡ ይሄ ግን ተመሳሳይ ቁጥር ባለው አማራጭ የተተረጎመ አደለም፡፡ ከአማራጮች ይልቅ የፓርቲዎቹ ቁጥር የሚያመላክተው በተለያዩ ቡድኖች የተሰባሰቡ ግለሰቦችን በፖለቲካ ስም የመነገድ ጥቅሞች የማጋበስ ፍላጎት ነው፡፡ ስንኩዋንስና ዘጠና በኛ የፖለቲካ መድረክ የለየላቸው ጥርት ባሉ ፖለቲካዊ አይዲዮሎጂና ፍልስፍና የሚመሩ 2 ወይም 3 አማራጮች አናይም፡፡

እየተዘጋጀ ካለ መጽሀፍ የተቀነጨበ

አዋጭ ፖለቲካዊ ባህርያት



  • ጎደለ ወይስ ሞላ
ፖለቲካ በአማራጮች ሲዋጅ እስከ ግማሽ ጎዶሎ ነውን በእስከ ግማሽ ሙሉ ነው ይተካል፡፡ ይሄ የአባባል ለውጥ አደለም፡፡ የአጀንዳ ለውጥ ነው፡፡ ሊሞላ ሊጨምር እና ሊያሳካ የሚመኘው ያንንም ለማሳካት የቀረጸው ፕሮግራም ያለው በመሆኑ ስለጎደለው ሳይሆን እንደሚሞላ ስለሚተማመንበት እና ዝግጅት ስላደረገበት ጉዳይ በማንሳት ይጠመዳል፡፡
በራስ መተማመኑ የሚመነጨው በባላንጣው ጉድለቶች ላይ ሳይሆን በራሱ ጥንካሬዎች ላይ በመሆኑ ስለጎደለው ሳይሆን የቀረው ስለሚሞላበት አግባብ እና ያን ለመሙላት ስላደረገው ዝግጅት በማስረዳት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡

ስለሚሞላው ነገር ምንነት ስለጉድለቱ መነሻዎች እና ሊሞሉት ስለሚችሉ ቁሳቁሶች ምንነት ያን እንዴት እንደሚያፈላልግ እና እንደሚያሟላ ስትራቴጂክ ትልሞቹን እየነገረ ስለሚሞላው ነገር በአባላቱ በደጋፊዎቹና በጥቅል ማህበረሱ ላይ እምነት እየፈጠረ ይሄዳል፡፡

ለእንደዚህ አይነት ፓርቲዎች ጉድለት መንጠላጠያ የትችት ማዝነቢያ ሰንሰለት ሳይሆን በአማራጭ ፓርቲነት የቀረበው ቡድን መፍትሄ የሚፈልግለት ተጨባጭ መመዘኛው መሆኑን አይስትም፡፡ ለዚህ ተጨባጭ ክፍተትም መፍትሄ በመፈለግ ድርጅታዊ ብቃቱን ለጉድለቶች መሙያ የሚሆኑ መፍትሄዎችን እና መላዎችን ማቅረብ እንደሚችል ያረጋግጣል፡፡
ይሄ ድርጅታዊ የመሙላት አቅም እና ዝግጁነት ነው አንድን ፓርቲ አማራጭም ተመራጭም ሊያደርገው የሚችለው፡፡ 

በመሆኑም ኢህአዴግ መሙላት ስላልቻለ እና ጎዶሎ ስላለበት ምረጡኝ ከማለት ወደ የመፍትሄው ባለቤት ነኝ ላልተሞሉት ችግሮች መፍትሄ ያበጀሁላቸው በዚህ አግባብ ነው ጉድለቶቹም የተፈጠሩት በነዚህ መነሻዎች መሆኑን ለይቻለሁ ሊሞሉ የሚችሉትም በዚህ አግባብ ስለመሆኑ ይህን የመሳሰሉ መረጃዎች አሉ በሚል ይቀርባል፡፡

ያኔ ስለጎደለ ልምረጥ ማለት ይቀርና የመሙያውን ቁልፍ የያዝኩት እኔ ስለሆንኩኝ ምረጡኝ ወደሚል በሁለት እግሩ የቆመ አማራጭ ይወስደናል፡፡ በመሆኑም አማራጭ ፓርቲዎች ጉድለቶችን መፍትሄ የማፈላለጊያ አማራጭ የመጠቆሚያ ተጨባጭ መነሻዎች እንጂ የወቀሳ መንጠላጠያ አያደርጓቸውም፡፡

እግረ መንገድ ግን እንዴት ሙሌቱን እንደሚፈጥሩ ሲያመላክቱ ገዢው ፓርቲ ቀዳዳዎቹን እንዴት እንደፈጠረ ወይም ሊለያቸው እንዳልቻለ ከየትኛዎቹ ፕሮግራሞቹ ወይም ፖለቲካ ፍልስፍናዎቹ እንደሚመነጩ ከፓርቲው ፍልስፍና እንኳ የማይመነጩ ከሆኑ ደግሞ እንዴትና ለምን ጉድለቶቹን ሊሞሏቸው እንዳልቻለ በመጠቆም ከገዢውም ከሌሎቹም ፓርቲዎች ለምን የተሻለ አማራጭ እንደሆኑ ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡

ዋናው ነገር ግን መፍትሄ ማበጀት መቻላቸው እና ሙላት የሚሆኑ ሀሳቦች አሰራሮች እና ፕሮግራሞች ያሉዋቸው መሆናቸውን ማስተዋወቅ በመሆኑ በራሳቸው ጥንካሬና ፕሮግራም ዙርያ አተኩረው የጎደለውን የሚሞሉ እንጂ በጎደለው ሰበብ የስልጣን ርካቡን የሚንጠላጠሉ አለመሆናቸውን ማስረገጣቸው ነው፡፡

ስለጉድለት አውስተው የሚወዳደሩ ሳይሆኑ በሚሞላው መፍትሄ መሆን በሚችለው ተወዳዳሪ ፖሊሲዎች ፕሮገራሞች እና አደረጃጀታቸው ተጫርተው በተሟላ የህዝብ እምነት ለመፍትሄው ወደስልጣን የሚመጡ መሆናቸው ነው፡፡
ይህን ለመሰሉ ፓርቲዎች ጥማታቸው ወንበር አደለም፡፡ ጥማቸው ሀገራዊ መፍትሄ መበጀቱ ነው፡፡ በዚህ ሂደት መፍትሄውን ማበጀት የሚችል ቡድን በህዝብ ሀላፊነት እስከተሰጠው ድረስ የስልጣን ጥማቸው ሆዳቸውን በልቷቸው ለነሱ መሰልጠን ሲባል ሰላማዊው ሂደት እንዳይደፈርስ በጽናት የሚቆሙ ናቸው፡፡ ውድድሩን ፖለቲካዊ ምህዳሩን የሚመዝኑት በውድድሩ አሸናፊ በመሆናቸው ሳይሆን ውድድሩ ዴሞክራሲያዊ  እሴቶችን ሊያንጽ በሚችል አግባብ እየተመራ ነው ወይስ አደለም በሚል ሚዛን ይሆናል፡፡

መሞላቱ ነው ቁምነገሩ፡፡ መፍትሄው ነው ዋናው ነገር፡፡ መፍትሄው እየተቀመረ እስከሄድ ድረስ ፖለቲካዊ ስልጣን መያዝ አለመያዝ የፖለቲካ ተሳትፏቸው መመዘኛ አደለም፡፡ ተሳትፏቸውን ማስገኘት በቻለው ጥቅል ፖለቲካዊ ጥቅምና እሴት ግንባታ እንጂ በታገሉለት ወይም በሚታገሉበት ፓርቲ ስልጣን ቆይታ ወይም መያዝ አደለም ማለት ነው፡፡