Saturday, January 26, 2013

ሽንፈቱን ጸጋ ማድረግ የኛ ፈንታ ነው

በ 11 ተጫዋች ያጠቃነው ቡድን በ 10 ተጫዋች ረመረመን። አራት ጎል ሲገባ መመልከት ያስቆጫል። አሁን አስር ሆነዋል እናሸንፋለን ብለን ስንጠብቅ መሸነፋችን ደግሞ ሌላው የሚያስቆጭ ነገረ ነው።


ያም ሆኖ ግን መቼም የምንመኘው የማይሸነፍ ቡድን ከነበረ ችግሩ ወዲህ ነው። ልጆቻችንም ይሁኑ አሰልጣኙ በማሸነፍ የሚገኘውን ክብርና ብሄራዊ ስሜት አያጡትም። አንዳንዴ  ግን የቀን ጎደሎ ሲያጋጥም የሚሞላበትን መላ መሻት ነው መፍትሄው።


የቀን ጎደሎውን መርገም የሚያመጣው ጭቅጭቅ ካልሆነ በቀር የሚፈይደው አንዳች ፋይዳ ያለ አይመስለኝም።


እገሌ ገብቶ ቢሆን ኖሮ እገሌ ተቀይሮ ቢሆን ኖሮ አስራት ግትር ባይሆን ኖሮ የሚለው የአሁን ላይ ትርክት ብዙም ፋይዳ ይኖረው አይመስለኝም።


የባይሆን ኖሮ መለኝነት ምንም አስገኝቶ አያውቅም። ቁም ነገሩ ከዚያው ሽንፈት የሚወሰደውን ትምህርት ወስዶ ለቀጣይ ጨዋታ መዘጋጀት ነው።


የምር በምናደንቀውና በምንወደው ቡድናችን ላይ ያሉበትን እጥረቶች መለየት ሲቀጥል ለተለዩት እጥረቶች የሚመጥን የረጅምም የአጭርም ግዜ እቅድ ይዞ መስራት ነው።


ያሸነፉ ለት ሆ የተሸነፉ ለት አይናችሁን ለአፈር የሚባል ፍልስፍና የወደቀ ፍልስፍና ነው። አሸናፊዎች የማይሸነፉ ሳይሆኑ ሽንፈት የአሸናፊነት ወኔያቸውን የማይሰልባቸው ናቸው። ሽንፈትን እዚያው ሜዳው ላይ አራግፈው ቀጣዩን ጉዞ እንዳዲሰነቱ የሚቀበሉ ጎበዞች። ዛሬ ና ነገን በትላንት አይመትሩም ትላንትናዎቻቸው ዛሬዎቻቸውን አይወስኑም ነገዎቻቸውንም አይተልሙም።


ቀኖቹን ለየራሳቸው መኖሩ ነው ጥበቡ። ቡድናችን ተሸንፉዋል ሰነፍ እማይረባ ቡድን ግን አደለም። ቡድናችን ተረቱዋል መረታት ግን ገጠመኙ እንጂ የማንነቱ ልኬት አደለም። ገጠመኝን ደግሞ በደምና በስጋ አይዙቱም በተከሰተበት ይተውታል እንጂ።


አዬ ባይሸነፉ ኖሮ አደለም የዛሬው አጀንዳ የዛሬው አጀንዳ  ይልቁንም ሽንፈትንም ከነክብሩ አንገቱን ቀና አድርጎ የሚቀበል ቡድን የመመስረትን አስፈላጊነት የምናወሳበት ነው። ድልንማ ማንም ያጣጥማል ቁምነገሩ ሽንፈትን በጸጋ መቀበል ከሽንፈት ባሻገር ያሉ ነገዎችን በትላንቱ ሽንፈት አስተማሪነት ለማስዋብ መሞከር ነው።


እንዳይሸነፍ የተገነባ ሳይሆን ሽንፈትን እንዲቋቋም የተሰራ ቡድን እንዳለን መታወስ ይኖርበታል። አሰልጣኝ ሰውነትም ይሁን ተጫዋቾቻችን ሲረቱም ይሁን ሲሸነፉ ከጎናቸው መሆናችንን ማወቅ አለባቸው።

አይናቸውን ለክብር እንጂ አይናቸውን ለአፈር  አንልም። ያልንም ካለን መማር ይኖርብናል። ሲያሸንፉም ሲሸነፉም የኛ ናቸው። ሁሌም ድጋፋችን እንደማይለያቸው ማረጋገጥ የኛ የደጋፊዎች ፈንታ ነው።


ቀና ልጆቻችን ቀና በሉ። ዛሬም ጀግናዎቻችን ናችሁ። የይቻላል ማሳያዎች። አንገታችሁን አቅንታችሁ ከነሙሉ ክብርና ወኔያችሁ ቀጣዩን ጨዋታ የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉበት።

ካሸነፋችሁም ደግ ብትሸነፉም ደግ ነው። ጀግና ጀግንነቱ የሚጎላው ሽንፈትን ሲቋቋም ነው። ነገ ሌላ ቀን ነው………

No comments:

Post a Comment