Tuesday, January 28, 2014

ኢህአዴግ ችግር ሆኖ ይሆን? እስቲ ይፈተሽ

ተቃዋሚዎች እና የተወሰኑ የግል ፕሬሶች የዚህ አገር ችግር ተጠቃሎ ሲታይ ኢህአዴግ ስለመሆኑ ያብራራሉ። ይሄን ውትወታቸውን ቸል ከማለት ቆም ብሎ መመርመር ተገቢ መሰለኝ። ችግሩ ምንድነው? ኢህአዴግ ወይስ ሌላ?

በመሰረቱ ኢህአዴግ በዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረከ ካገኘናቸው አማራጭ መሪ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይሄን አገር ከሌሎቹ አማራጭ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተሻለ የምመራበት የፖሊሲ ፕሮግራምና የመምራት ብቃት ስላለኝ ምረጡኝ የሚል ፓርቲ። በካርድ በየአምስት አመቱ የመሪነት ስራው የሚታደሰለት ወይም የማይታደስለት ፓርቲ።

በመሆኑም ፓርቲው ይሄ አገር ለገጠመው ችግር መፍትሄ የሚሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መፍትሄዎች አበጃለሁ በሚል ቃሉ የተመረጠ ነው ማለት ነው። መፍትሄ እንፈልጋለን፣ ችግሮቹን ከነመነሻቸው ለይተን አውቀናል፣ አዋጭ መፍትሄዎችም ተልመናል በሚል የመወዳደሪያ ሀሳብ በየአምስት አመቱ ሀላፊነቱ ይራዘምለታል ማለት ነው።

ኢህአዴግ ችግር ነው ማለት የሚገባኝ መፍትሄ ማፈላለግ አልቻለም በሚል የሚቀርብ ከሆነ ነው። አለበለዚያ እዚህ አገር ያሉ ችግሮችን ኢህአዴግ ጠፍጥፎ እንዳልሰራቸው ይታወቃል። በመሆኑም ኢህአዴግ ችግር ነው ማለት ድህነትን፣ ድንቁርናን፣ የተበላሹ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ ግንኝነቶችን ወዘተ ማረቅ እና ማረም አልቻለም ማለት ነው። ከሆነ ሌላ አማራጭ ያስፈልገናል ማለት ነው።

አማራጭ መፍትሄ ቀረበ ወይ?

ኢህአዴግ ችግር ነው ወይም ኢህአዴግ ችግር መፍታት አልቻለም የሚል ቡድን ችግሮቹን የሚፈታ አማራጭ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ወዴት ናቸው ታዲያ አማራጮቹ? ድህነት እንዴት እንደሚቀረፍ? ትምህርት እንዴት እንደሚስፋፋ? ማህበራዊ የብሄረሰቦች ግንኙነት እንዴት መልክ
እንደሚይዝ የሚያረጋግጡት አማራጮች የት አሉ?

አቤቱታዎቹን ተቀብለን ኢህአዴግ መፍትሄ መሆን ተስኖታል ብንል እንኳ ይሄ ሀቅ የትኛውንም ተቀናቃኝ ጠንካራ አማራጭ ያደርገዋል ማለት አደለም። ስለሆነም ቁምነገሩ ኢህአዴግ መፍትሄ መሆን አለመቻሉን ማወቅ አደለም። ዋነኛው ጉዳይ መፍትሄዎቹን አበጅቶ መገኘት ነው። እውን የምር የቱ ፓርቲ ነው መፍትሄ አበጅቶ፤ መፍትሄውን መፈጸም የሚችል የፖለቲካ አመራር ቡድን አደራጅቶ የሚታየው?

እንደ ቡድን የማይተማመኑ፣ ከአንድ ስብሰባ የተለያየ መግለጫ የሚሰጡ፣ በስብሰባ ወቅት የሚደባደቡ፣ የፖሊሲ ትስስር እና መጣጣም በሌለበት ጥምረት የሚፈጽሙ ፓርቲዎች ናቸው መፍትሄ የሚሆኑን? ትንሿን ፓርቲያቸውን በጠንካራ ዲሲፕሊን ሳይመሩ ነው ይሄን ትልቅ አገር እና የተለያዩ ፍላጎቶች ያሉበት አገር አቻችለው የሚመሩት?

ኢህአዴግ ችግር ቢሆን እንኳ መፍትሄ ያላቀረበና መፍትሄዎቹን መተግበር የሚያስችለው ጠንካራ ፖለቲካዊ አመራር ያልገነባ ቡድን በምንም ሚዛን የመሪነቱን ቦታ ሊያገኝ አይችልም። ከነችግሮቹ ኢህአዴግ ይምራን መባሉ አይቀሬ ነው።

በትናንሽ ማሳ በማረስ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አይቻልም ይላሉ ተቃዋሚዎች፤ እዚያው ሳሉም ለትላልቅ ባለሀብቶች መሬት በሊዝ ሲሰጥም ሀገር ተሸጠ ይላሉ፤ እነሱ ቢሆኑ ኖሮ ምን አማራጭ ነበራቸው? ወይስ እነሱ ይሄን አማራጭ ሲሰሩት ደርሶ ትክክል ይሆናል?

መንገድ ሲጠብም መንገድ ለመገንባት ሲቆፈርም ያማርራሉ፤ እነሱ ስልጣን ቢይዙ መንገድ እና ባቡር ሳይቆፈር እንዲሰራ ያደርጋሉ?

የሀይል እጥረት ያማርራሉ፤ ቆይማ ስልጣን ቢይዙ የሀይል እጥረት ለመፍታት የሀይል ማመንጫ ከመገንባት ሌላ አማራጭ ነበራቸው? ወይስ የተቃወሙትን የአባይ ግድብ ይተውት ነበር ችግሩን ለመፍታት?

እሚያከራክረኝ ያለው ኢህአዴግ መፍትሄ መሆን አልቻለም የሚለው ሳይሆን መፍትሄ መሆን ሳይችሉ ወይም የመፍትሄ አማራጭ በአግባቡ ሳይቀምሩ መፍትሄዎችን አነሰም በዛም እያበጀ ያለውን ፓርቲ መውቀስን እንደ ሁነኛ የፓርቲ ስራ ማየታቸው ነው።

ፓርቲዎች ተመራጭ የሚሆኑት በአማራጮቻቸው እንጂ መሪ ፓርቲን በማጣጣል ብቃታቸው አደለም። ዞሮ ዞሮ ስልጣን ሲያዝ ሀገር ይገነባል እንጂ ወቀሳ አይጠፈጠፍም።

ልደምድመው አማራጭ መሆን እንጂ ኢህአዴግ ደካማ ቢሆን እንኳ ደካማውን አማራጭ መተቸት ምርጥ አማራጭ ሊያደርገን አይችልም።

Tuesday, January 14, 2014

ከህወሃት ምን እንማር?



ከህወሃት ሌሎች እህት ፓርቲዎችም ይሁኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊማሩት የሚገባው ጥንካሬ ይሄ ነው - በአንድ የፖለቲካ አቋም ዙርያ ጠንካራ እምነት ያለው ሰፊ እና በቅጡ የተደራጀ ህዝባዊ መሰረት መገንባት። የትግራይን ህዝብ ቀስበቀስ ግን አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ በማደራጀት ልጆቹን ለጦርነት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ያስተማመነ ጠንካራ ድርጅት ነው። ለአላማው ሲል ሞትን እሺ በጄ ብሎ የሚቀበል ህዝባዊ መሰረት መፍጠር ግዙፍ ስኬት ነው። 

ለዚያ ነው ከሶስት ሚሊየን የማይበልጠውን የትግራይን ህዝብ አደራጅቶ ሀገር የሚመራውን ደርግን ያንበረከከ ሰራዊት እና አደረጃጀት በ17 አመታት ሂደት የፈጠረው ። ያ አደረጃጀት እና ሰራዊት ደግሞ ራሱን ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ድጋፍ በሚሰጠው ሰፊ የትግራይ ህዝብ ድጋፍ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አሸናፊ መሆን ችሏል።

ዛሬም ድረስ አጋር ድርጅቶቹን በማጣጣል ህወሃት ነው ይሄን አገር የሚያሽከረክረው የሚባለው አቤቱታ የሚሰማው ይሄን መሰሉ ህዝባዊ ድጋፉ የፈጠረለትን ጠንካራ አደረጃጀት ከመረዳት መሆኑ አይጠረጠርም።

አሁን መፍትሄው ለማንኛችንም ህወሃትን መጥላት አደለም። መፍትሄው እንደ ህወሃት ባላፊ አግዳሚው ተቃውሞና ማዕበል እማይፍረከረክ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ፓርቲዎች ቀስበቀስ ግን አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ማነጽ ነው። እንዲህ ያለው ጥንካሬ ደግሞ በሰሞነኛ ጫጫታ እንደማይፈጠር አውቆ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ህዝብ የሚያስተማምን ፕሮግራም መቅረፅ ያን ደግሞ ሳይሰለቹ ለህዝብ ማስተዋወቅ እና በዚያ ዙርያ የተሰባሰበ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ማነጽ ይጠይቃል።

ይህን አይነት አደረጃጀት ሲኖርህ ከ33 ሚሊየን ከሚበልጠው ኦሮሞ እና ከ25 ሚሊየን ከሚበልጠው አማራም ቢሆን የሚሻል ጥንካሬ ልትገነባ ትችላለህ። ቁምነገሩ በአስተማማኝ አላማ ዙርያ የተማመነ ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ ማቋቋም አለማቋቋም እንጂ ብዛት እንዳይደለ ማን በነገረልኝ።

ለዚህ የሚተቸው ደግሞ ጠንካራ ሆኖ የተገኘው ህወሃት አደለም። ጥንካሬ ከሌላቸው ሊተቹ የሚገባቸው በህወሃት ደረጃ እና ጥልቀት ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት መገንባት ያልቻሉት ሌሎች አጋር ፓርቲዎች እና የሚመለከታቸው ደካሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው።

የካቲት 11 ይህን አይነቱን ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ያለው ፓርቲ ለመመሰረት ጠንሳሽ ቀን በመሆኑ እናደንቃለን።
ነፍሱን ይማርና መለስ ዜናዊ አስር የተደራጀና የታጠቀ ሰራዊት አንድ መቶ የታጠቁ ግን ያልተደራጁ ሀይሎችን ሊያጠፋ ይችላል ይል ነበር። ሳይደራጁ እንቡር እንቡር ማለቱን ትተን እስኪ ለሁነኛ ለውጥ ጠንካራ እና ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያለው አደረጃጀት እንፍጠር።

ይህን ለመሰለ ህዝባዊ አደረጃጀት የተሰው ጀግኖችን ማሰብና ክብር እንደሚገባቸው መናገር ከተግባራቸው ለመማር እና ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው ፓርቲ ከማቋቋም ሌላ መሰረታዊ እና ሁነኛ ሚና የሚጫወት ፓርቲ መመስረት የሚቻልበት መንገድ ዝግ ነው።

ለዚህ ጥንካሬው ህወሃትን ከመተቸት የተሻለው አማራጭ ማድነቅና ያን ትምህርት ወስዶ የሚመለከተው ሁሉ ጠንካራ ፓርቲ መገንባት እንዳለበት አምናለሁ። መራራ ድክመትን ተቀብሎ ማረም እንጂ ጠንካራውን ስለብርታቱ መጥላት የከፋው አደጋ ነው - የመማር እድላችንን ዝግ ያደርገዋልና።

ህወሃትን መገዳደር ስታስብ ያንን ህዝባዊ መሰረቱን የሚፎካከር መሰረት ያለህ መሆኑን ደጋግመህ እንድታስብ ትገደዳለህ። ህወሃት ብቻውን ግን በቂ አደለም። እነ ብአዴንም ኦህዴድም ደህዴንም በእንዲህ አይነት ህዝባዊ መሰረት ላይ ራሳቸውን አጠንክረው መትከል ይጠበቅባቸዋል። የ97 ምርጫ የናጠው ያን አይነት አደረጃጀት ያልፈጠሩ ፓርቲዎችን መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ተቃዋሚዎች በሌሎቹ ክልሎች የሚያገኙትን አይነት ድጋፍም ማግኘት የተሳናቸው አስተማማኝ መሰረት በተጣለበት ትግራይ መሆኑ አይሳትም።

ጨዋታው የቁጥር እና የብዛት አደለም። ጨዋታው የተሳካለት አደረጃጀት የመፍጠር አለመፍጠር መሆኑ አይሳት። ያን አይነት መሰረት ደግሞ ለፖለቲካው መረጋጋት እና ለፍትህ መንገስ ትልቅ ሚና አለውና ለሁላችን የሚተው የቤት ስራ ነው። ከመደንፋት ባሻገር ያለው ያልተወጣነው ስክነት እና ጠንካራ እንዲሁም ተከታታይ ስራ የሚጠይቀው ተግባር ይሄ መሆኑ አይሳት።

በመጨረሻ ቁምነገሩ ህወሃት እንዲዳከም ከመስራት እንደ ህወሃት ጠንክሮ መገኘት የሚሆነውም ለዚህ ነው። ይህን ሀቅ ስንረዳ ደግሞ ህወሃትን ለዚህ ያበቁትን የመለስ ዜናዊን የመሳሰሉ ጭንቅላቶች አንዘነጋም። በርግጥም ክብር ይህን መሰል አደረጃጀት እና ታጋይ ድርጅት መፍጠር ለቻሉ ሰማዕታት። አድንቅ ከምታደንቃቸው ጠንካሮች ተምረህ ደግሞ ተመሳሳዩን ቁመና ፍጠር። ሲተቹ ከመኖር ግዜ ወስዶ ጠንካራ ሆኖ መታነጽ ይሻላል ባይ ነኝ።

Friday, January 10, 2014

ብአዴን/ኢህአዴግ Vs መኢአድ፣ ኢዴፓ እና አንድነት


===========================================
እነዚህ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የጎላ ድርሻ ያላቸው ናቸው ማለት ይችላል። ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፓርቲዎቹ አንድ ነገር በወሳኝነት ያመሳስላቸዋል - በወሳኝነት በአማራ የፖለቲካ ኢሊቶች የሚመሩ መሆናቸው። ያ ሆኖ ሲያበቃ ግን ፓርቲዎቹ ከብአዴን ጋር መሰረታዊ የሚባል ልዩነትም ያላቸው መሆኑ አይሳትም።

በርግጥ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ ይሄ ነው የሚባል የጎላ የፖሊሲ እና የፕሮግራም ልዩነት ያላቸው አደሉም። ይልቅ በተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚታየው ልዩነት የግለሰቦችን ቅሬታ እና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው። ፌደራላዊ ስርአቱን፣ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት እና ሀገራዊ አንድነትን በተመለከተ የሚያቀነቅኑት አቋም አንድና ያው ነው። መንግስታዊ ባህሪው ምን መሆን አለበት በሚሉና መሬትን እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በተመለከተ የሚያቀነቅኑት አቋምም ተመሳሳይ ነው።

ብዙ ግዜ እነዚህ አማራዎች የሚበዙባቸው ቀኝ ፖለቲከኞች የቀድሞውን ስርአት እና የአማራን የበላይነት ለመመለስ ይሰራሉ በሚል የሚወነጀሉበት በሌላ ገጹ ደግሞ ብአዴን/ኢህአዴግ ደግሞ የህወሃት ጥገኛ ተደርጎ የሚሳልበት ክስ ይሄ ጽሁፍ ከግምት የሚያስገባቸው ጉዳዩች ናቸው። ስለሆነም በጹሁፌ ማየት የምፈልገው ቁምነገር እነዚህ አማራ ኤሊቶች የሚመሯቸው ፓርቲዎች በፌደራላዊ ስርአቱ እና በአንድነት/መገንጠል ጉዳይ ላይ ያላቸውን ልዩነት እና እነዚህ ፓርቲዎች ያላቸው አቋም በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አባሎቻቸው ላይ ያለውን ተጽእኖ ነው።
ፌደራላዊ ስርአቱ
==================================================
ፌደራላዊ ስርዓቱን በተመለከተ መኢአድ ኢዴፓና አንድነት ያላቸው አቋም ህዝቦች እንደ አስፈላጊነቱ ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን የሚጠቀሙ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአስተዳደር እንዲመች ተደርጎ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን ከግምት ባስገባ መልኩ መከናወን አለበት የሚል ነው። በብሄረሰብ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ይላሉ እነዚህ ቡድኖች ሀገራዊ አንድነቱ እና የህዝቡ ትስስር ይላላል። እንዲያውም ያ አይነቱ ፌደራሊዝም አንድነቱን እየሸረሸረው ይሄዳል የሚል ስጋት ያነሳሉ። እነዚህን ቡድኖች ብሄረሰባዊ ፌደራሊዝሙን የሚደግፉ እና ተገቢ ነው የሚሉ ሀይሎች የቀድሞውን ስርዓት ለማምጣት የሚተጉ፥ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ፌደራሊዝም ሰበብ ህዝቡን ከፋፍለው ድምጹን ከፍ አድርጎ ማሰማት እንዳይችል ለማድረግ የሚሰሩ ናቸው የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ኦነግን የመሳሰሉ ቡድኖች ደግሞ እነኚህ ሰዎች "የአያቶቻቸውን ስርዓት" ለማስቀጠል እና የህዝቦችን ትግል ለማዳከም እንጂ የህዝቦች መብት አሳስቧቸው አደለም በሚል ይወነጅላሉ።

ብአዴን/ኢህአዴግ የሚያቀርቡት አማራጭ ደግሞ አዎን ህዝቦች ብሄራዊ አንድነታቸውን ተከትለው ፌደራላዊ መንግስት ማቋቋም ይችላሉ። በሀገራችን ታሪክ ቀድመው የነበሩ ስርአቶች ሆን ብለውም ይሁን ባለማወቅ ያደረሷቸው ጭቆናዎች ፍትህ የማጣት የመበዝበዝ ብቻ ሳይሆን ብሄረሰባዊ ጭቆናም የነበረባቸው ናቸው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ብሄሮች ማንነታቸው ለጥቅምም ለበደለም ታርጋ የማይሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር መስራት አለብን ይላሉ። ለአንድነት ምክንያት የሚሆነን እና አንድነቱን የሚያቋቁሙት መሰረታዊ ጉዳዩች ግን የፌደራል ስርአቱ አከላለል ሳይሆን ለአንድነት መነሻ የሚሆኑን ጉዳዩች ናቸው በማለትም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ። አንደኛ ህዝቦቿ በታሪክ ሂደት ያፈሩት የጋራ ቅርስ እና መቻቻል ሁለተኛ ደግሞ ከጦርነት እና ከጸጥታ ስጋት ጸድቶ በማያውቀው ቀጠና ጥቅሞቻችንን በተሻለ ለማስጠበቅ እና ደህንነታችንን ለመጠበቅ ከጠንካራ አንድነት የተሻለ አማራጭ የሌለን መሆኑ ነው። ስለሆነም ይላል ብአዴን/ኢህአዴግ ህዝቦች አንድነቱን የሚመርጡት ባለንበት ቀጠና እና ባለን ታሪክ አንድነቱ የተሻለው እና የማያወላዳው አማራጭ በመሆኑ እንጂ እንዳንገነጣጠል በሚል ስጋት ብሄሮች ወዲያና ወዲያ በክለላ ስለተሰፉ አደለም ይላል። ይሄን በወሳኝነት የሚቃወሙት ደግሞ መኢአድ አንድነት እና ኢዴፓን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ናቸው። ሰማያዊ ፓርቲም ከሰሞኑ ይሄንኑ ጎራ የተደባለቀ መሆኑ አይዘነጋም።