Tuesday, September 3, 2013

መፍትሄ ፈብራኪ ወይስ ወቀሳ ጠማቂ


ነጻ የወጣ ህሊናና ህዝብ አብይ ተግባር ኢኮኖሚያቸውን መቀየር ነው፡፡ ዲትሮይቶቹን እና ሲሊካን ቫሊዎቻቸውን ማነጽ፡፡ ነጻነታቸው ከሚያስጀምሯቸው ሁነኛ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ኢኮኖሚያዊ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ነጻነትም አብይ ፋይዳ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት መቻሉ ነው፡፡ የህዝብ አብይ ጥያቄዎች ዞሮ ዞሮ ኢኮኖሚያዊ ናቸውና በተለይ እንደኛ ባለ ደሀ ሀገር፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎችም አብይ ፋይዳ ኢኮኖሚያዊ ነጻነቶችን ማረጋገጥ መቻል መሆኑ ይታወቃል፡፡


ኢኮኖሚውን ማንደርደር ወይስ ፓለቲካውን ማንተክተክ
በብዙ መልኩ ሲመዘን የኛ ሀገር ፖለቲካ ያለበት ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩችን ወደፊት በመግፋት ላይ የሚያተኩር ሳይሆን በመብት ላይ የተንጠለጠለ ከመብትም ደግሞ በተሟላ መንገድ ያሉ ጭብጦች ላይ ሳይሆን በየወቅቱ ከሚወጡ ደንቦችና ህጎች ውስጥ በተወሰኑ ለወቀሳ ያመቻሉ በሚባሉ በወጉ ባልተላመጡ ጉዳዩች ላይ ተንተርሶ ገዢውን ፓርቲ ለማጣጣል ከመሞከር ባለፈ በሀራችን የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውን በወጉ በተጠኑ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙርያ የማያደራጁ በየወቅቱ በሚኖሩ ክርክሮች ላይ ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ በድክመትም ቢሆን እያነሱ ሲያስተዋውቁ የሚውሉት ኢህአዴግን  የሆነብት ሁኔታ ነው ያለው፡፡


በዚህ ሂደት የፖለቲካውን ሙቀት ከመጨመር በዘለለ ምናልባትም በተወሰኑ ጉዳዩች ላይ ገዢውን ፓርቲ ከማብጠልጠል ባለፈ በሀገሪቱ ወሳኝ ስለሆነው የኢኮኖሚ እድገት ወዴትነት እንዴትነት በምን አማራጭ ሊያድግ እንደሚችል በማመላከት ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ግብአት እስከማይኖራቸው ደርሰዋል፡፡


በዚህ የተነሳ በኢኮኖሚው ላይ ፓርቲዎቹ የሚሰጡት ትንታኔ ግለሰቦች ከሚሰጡት የአሉባልታ ትንታኔ የተሻለ ብስለት የማይታይበት እና ወትሮም ገዢው ፓርቲ እያሳደገው ያለውን ኢኮኖሚ እንዴት በላቀ የእድገት ምጣኔ እንደሚያሳድጉት ሊያመላክቱን ቀርቶ አሁን ባለውም ቁመናው እንዴት እንደተደራጀ ምን ለውጥ እያስገኘና ምን እጥረቶች እየፈተኑት እንዳሉ እንኳ በወጉ የማይገነዘቡ ፓርቲዎች የተጠራቀሙበት ምህዳር በመሆን ቀጥሏል፡፡


ይሄ የሆነው እና እየሆነ የቀጠለው ተቃዋሚዎቹ ወደ ፖለቲካው ጎራ ከተፍ የሚሉት አንድም በፖለቲካ ፓርቲ መሰባሰብ ያስገኛል የሚሉትን ጥቅም ለመቀራመት በሌላም ይህ ካልሆነ ደግሞ ኢህአዴግን በሚረባም በማይረባም ጉዳይ ስለሚጠሉት ብቻ ይሆንና ተቃውሞ የጥላቻ መልእክት ከመቀመር እና አቤቱታ ከመዘመር የተሻለ ቁምነገር የሌለው ሆኖ ያርፋል፡፡ ለዚህ ነው የሀገራችን የተቃዉሞ ፖለቲካ ከአቤቱታ ከፍ የሚል ሚና መጫወት የተሳነው፡፡

ፖለቲካን ህዝባዊ ጥቅም አስቀድመን ወይም ደግሞ ልንጠላቸው የምንችላቸው ፓርቲዎች ቢኖሩ እንኳ (መጥላት ሁነኛ አጀንዳ ሊሆን አይችልም) ህዝብ ሊጎናጸፍ ሲችል ያጣቸውን ጸጋዎች ለማላበስ አልመን እና በዚያው አላማ ዙርያ የተማመኑ እና ያን ማስመጸም የሚችል የአላማ ዝግጅት ያላቸውን ግለሰቦች አሰባስበን የምንገባበት ትልቅ አላማ እንጂ ለገዢ ፓርቲ ጥላቻ ያለው ሁሉ የውር ድንብር ጥላቻውን ለመግለጽ የሚሰባሰብበት የጥላቻ ማወራረጃ ጽዋ አደለም፡፡


ፖለቲካ ፓርቲን ያክል ነገርና ሀገርን ያክል አብይ አጀንዳ ለሻይ ቤት ወሬ የማይበቃ አላማ አንግቦ ለመምራት ማሰብ እንኩዋንስና ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዩችን ለመምራት ከሚንጠራራ ቡድን ይቅርና የፖለቲካ ከሜዲ ለሚተውኑ ቡድኖች አይመጥንም፡፡ እቺን ታክል ግብ እንኳ በወጉ ሳይሰናዳ ፖለቲካዊ ምሬት መፍጠር ብቻ በአጀንዳነት ተይዞ ፖለቲካውን በቀውስ ለመናጥ የፈጠራ ወሬ ታጥቆ እዚያም እዚህም ብቅ ጥልቅ ማለት ከጅምሩ የከሸፈ ቡድን መፈክር እና መዋቅር ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡


አደባባይ በቀውስ በመናጥ አንዲት ብጣሽ ዳቦ ማቅረብ አይቻልም፡፡ በወጉ በመረጃ ላይ ያልተደራጀ የፖለቲካ ክርክር ማካሄድ አቦ አነጋገሩ አሪፍ ነው ከማሰኘት በዘለለ በቁምነገሩ እዚህ ግባ የሚባል ጭብጥ አልባ ሆይሆይታ ነው የሚሆነው፡፡ ልክ ያልተጠና ሰላሙን ያጣ የጎዳና ላይ ነውጥ የሚኖረውን ያክል መተራመስ ብቻ፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ፖለቲከኞች የሚታወቅ ወጥ የሆነ እና ተገማች አጀንዳዎች ቀርጸው ተስፋ ሊጣልበት በሚችል ፍልስፍናና አደረጃጀት ብቅ ማለት ካልቻሉ ፓለቲካውን የምህዳሩ ጠበበን ስንክሳሩን ከማስተጋባትና የፖለቲካውን የጥላቻ ግለት ከመጨመር በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል እምነት የማይጣልባቸው ተራ ቡድኖች ነው የሚሆኑት፡፡


በዚህ ባህሪያቸው የተነሳ ነው ህዝብ እምነት የሚጣልበት ተቃዋሚ የለም የሚለው፡፡ በመሆኑም የተቃዋሚው ሁነኛ እና ዋነኛ ድክመት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ያለበት ግብ እና ዲስፕሊን አልባነት ነው፡፡ ርስበርሳቸው የማይከባበሩ ርስበርሳቸው የማይደማመጡ እና በውስጥም በውጭም ጥላችን የሚያርምዱ እንጂ ከዚያ ከፍ የሚል የረባ ግብ የሌላቸው ናቸው፡፡


እንደሚወዷት የሚናገሩትን እቺን ሀገራችንን የት ሊያደርሱዋት እንደሚፈልጉ እንዴት እዚያ እንደሚያደርሷት እና ምን አይነት የፖለቲካ አመራር ተጠቅመው ያንን እንደሚፈጽሙ ትንሽ ግዜ ወስደው እንኳ የማብራራት ግድ የሌላቸው ከስም በቀር አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያደርጋቸው መገለጫ የሌላቸው ቡድኖች ናቸው፡፡ ቡድንም የምንላቸው የተሰባሰቡ ግለሰቦች ስላሉ እንጂ በበርካታ መሰረታዊ ጉዳዩች ላይ ስምምነት የሌላቸው ግለሰቦች ስብስብ መሆኑን በየወቅቱ ከሚፈነዱ ልዩነቶቻቸው የምንታዘበው ነው፡፡ በርካታ ውህደቶቻቸውም የአቻዎች ጋብቻ ሳይሆን ጠርቀም ብንል ምናልባት ኢህአዴግ ይደነግጣል በሚል ስሌት የሚሾፈር በመሆኑ በመሰረቱ አንድ ተራ ጉዳይ አንኳ ማስፈጸም የሚችል አደለም፡፡


ስንኳስና ተቃራኒ ቡድን የሚፈጥርባቸውን ተጽእኖ ይቅርና በየስብሰባው በየመሀላቸው የሚፈጠርን የአስተሳሰብ ልዩነት አርቀው ማሰቀጠል የተሳናቸው በመሆኑ ፖለቲካን በጥላቻ ከማንተክተክ በዘለለ የህዝብን ሁነኛ የፖለቲካና መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዩች መምራት የሚችሉ አደሉም፡፡ ይሄ ደግሞ የህዝብን የመኖር ጥያቄ የመብላት ጥያቄ የመሰረተ ልማት ጥያቄ መፍታት የሚችል አደረጃጀት ባለመሆኑ በዚሁ ቁመናው ለመቼውም የይስሙላ ውድድር ከማድረግ ዘሎ ምርጫዎችን ማሸነፍ በሚያስችል ቁመና ላይ ሊያደርስ የሚችል አደለም፡፡


በመሆኑም ፓርቲዎች ተቃራኒያቸው ያላበሰለውን እና ያሳረረውን ከመናገር በፊት የሚያበስሉትን ሕዝባዊ ጥቅም የሚጋግሩትን ሊበስል የሚችል ዳቦና እንጀራ ሊያሳዩ ይገባቸዋል፡፡ ተቃራኒን ማጣጣል ከዚህ የሚለጥቅ ዳር ላይ ያለ የትግል አግባብ እንጂ መቼም ሁነኛ ትጥቅ መሆን አይችልም፡፡


እናስ ጥላችን ከማንተክተክ በመለስ ያለውን ኢኮኖሚውን የመጋገር ኢኮኖሚውን የማንደርደር የንግግር ሳይሆን የተግባር መፈተኛ የሆነውን ይህን ጉዳይ ተቃዋሚዎች ቢታጠቁት ምን ይላቸዋል፡፡ በኔ እምነት የተአማኒነት የተገማችነት እና ድጋፍ የማሰባሰብ አቅም ያለው አማራጭ ይሄ እንጂ የትችት ጋጋታ ማዝነብ አይመስለኝም፡፡ አደለምም፡፡

No comments:

Post a Comment