Wednesday, March 20, 2013

ዘረኞች ታሪክን ለቀቅ ! ጠባቦች ከታሪክ ፈቀቅ!


ታሪክን የሚማሩበት ተመሳሳይ ስህተት አይሰሩም ታሪክን የሚማሩበት ሰዎች ከደም አይቆራኙም ቁምነገራቸው ከተከሰተው ታሪካዊ ጥሬ ሀቅ ነው$

ታሪክን ከደምና ስጋቸው ተነስተው የሚመዝኑ ሰዎች ታሪክ ተሳስተዋል ብሎ ከሚከሳቸው ሰዎች የተለዩ አደሉም$ እንዲህ አይነት ግለሰቦች ሀቃቸው ከደም የሚቀዳ በመሆኑ ሁለት ፊውዳሎችን በታሪክ አይን መዝኑ ቢባሉ ለደማቸው የቀረበውን ጻድቅ ከደማቸው የራቀውን ጭራቅ የማድረግ ልምድ አላቸው$

የዚ መነሻው መገምገሚያው ጥሬ ሀቅ አላማው ደግሞ ትምህርት አለመሆኑ ነው$ የታሪክን ግዙፍ ገጾች የሚገልጡት ባላንጣቸውን ለማጣጣል በማለም እኛ የሚሉትን ደማቸውን ደግሞ ለማዳነቅ በመሆኑ ነው$ ለነዚህ አይነት የታሪክ ሰዎች ታሪክ ጥይታቸው እንጂ ዛሬን የሚያንጹበት ነገን የሚተልሙበት መነሻቸው አደልም ግብአታቸው አደለም$

ታሪክን የነሱ አዲስ ደማዊ ትርክት ይለውጠው ይመስል ታሪኩን እያዛቡ ሲነግሩን የትላንቱን ባለጌ ሊያሳዩን ተፍተፍ ሲሉ የዛሬዎቹን የታሪክ እድፎች እየታዘብን እንደሆነ እንኳ አይረዱም$ ከትላንቶቹ ስህተቶችና ብልሹ ግለሰቦች የበለጠ የነሱ የዛሬዎቹ አሜኬላዎች ቁመና እንደሚያሳሰበን አይገባቸውም$

የታሪክን እድፍ ሊያሳዩን ሲጥሩ ማደፋቸውን የሚያሳብቁን የዛሬ ታሪክ የደም ቀላሚዎች ታሪክን ለትምህርት ታሪክን ዛሬን ለማነጽ እንዲያወሱት እናስታውሳቸዋለን$ ባዳፋ መነጽር ታሪክን እያዩ ሀቁን አቀርባለሁ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው$ የሚቀድመው በደም የቀለመ የታሪክ መነጽራቸውን ማጥራት ወይም የጠራ አዲስ መነጽር ማጥለቅ ነው$

የትላንትና አንበሶችም ሆኑ ውሾች ዛሬን አያንጹትም አያበላሹትምም$ የዛሬዎቹ የተበከሉ የታሪክ ውሻዎች ግን ዛሬን እንዳይበክሉት ነገን እንዳያጨፈግጉት ሀይ መባል አለባቸው$ እውን የታሪክ ተማሪ መሆን ከብዶ ነው እንዲህ የታሪክ ሙርከኛ ሆነን ትላንትን ከፊሎቻችን ለፖለቲካችን ማራገብያ ደሞ ከፊሎቻችን ዘረኛ አቋሞቻችንን ለማንጸባረቅ ይህን ያህል የምንባትለው?

ሀቁ ይህ ነው$ ታሪክ ታሪክ ነው$ ያማረም የከፋም አስተያየታችን አይቀይረውም አስተያየቶቻችን ግን የባለአስተያየቱን ቁመና እና ሀሳብ ያሳብቃሉ$ ቢያንስ እረ ሰው ይታዘበናል ብለን ከመቀባጠር እንቆጠብ$ ታሪክ ለዘረኝነት ታሪክ ለርካሽ ፖለቲካ ማራመጃነት ታሪክ ለመቀባጠር ባይሆን$

የምር ከታሪክ ብንማር ታሪክ ብንሰራ ታሪክ በዚህም ቢያስታውሰን ይሻላል$

No comments:

Post a Comment