Friday, January 10, 2014

ብአዴን/ኢህአዴግ Vs መኢአድ፣ ኢዴፓ እና አንድነት


===========================================
እነዚህ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የጎላ ድርሻ ያላቸው ናቸው ማለት ይችላል። ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ፓርቲዎቹ አንድ ነገር በወሳኝነት ያመሳስላቸዋል - በወሳኝነት በአማራ የፖለቲካ ኢሊቶች የሚመሩ መሆናቸው። ያ ሆኖ ሲያበቃ ግን ፓርቲዎቹ ከብአዴን ጋር መሰረታዊ የሚባል ልዩነትም ያላቸው መሆኑ አይሳትም።

በርግጥ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ ይሄ ነው የሚባል የጎላ የፖሊሲ እና የፕሮግራም ልዩነት ያላቸው አደሉም። ይልቅ በተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚታየው ልዩነት የግለሰቦችን ቅሬታ እና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው። ፌደራላዊ ስርአቱን፣ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት እና ሀገራዊ አንድነትን በተመለከተ የሚያቀነቅኑት አቋም አንድና ያው ነው። መንግስታዊ ባህሪው ምን መሆን አለበት በሚሉና መሬትን እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በተመለከተ የሚያቀነቅኑት አቋምም ተመሳሳይ ነው።

ብዙ ግዜ እነዚህ አማራዎች የሚበዙባቸው ቀኝ ፖለቲከኞች የቀድሞውን ስርአት እና የአማራን የበላይነት ለመመለስ ይሰራሉ በሚል የሚወነጀሉበት በሌላ ገጹ ደግሞ ብአዴን/ኢህአዴግ ደግሞ የህወሃት ጥገኛ ተደርጎ የሚሳልበት ክስ ይሄ ጽሁፍ ከግምት የሚያስገባቸው ጉዳዩች ናቸው። ስለሆነም በጹሁፌ ማየት የምፈልገው ቁምነገር እነዚህ አማራ ኤሊቶች የሚመሯቸው ፓርቲዎች በፌደራላዊ ስርአቱ እና በአንድነት/መገንጠል ጉዳይ ላይ ያላቸውን ልዩነት እና እነዚህ ፓርቲዎች ያላቸው አቋም በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አባሎቻቸው ላይ ያለውን ተጽእኖ ነው።
ፌደራላዊ ስርአቱ
==================================================
ፌደራላዊ ስርዓቱን በተመለከተ መኢአድ ኢዴፓና አንድነት ያላቸው አቋም ህዝቦች እንደ አስፈላጊነቱ ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን የሚጠቀሙ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአስተዳደር እንዲመች ተደርጎ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን ከግምት ባስገባ መልኩ መከናወን አለበት የሚል ነው። በብሄረሰብ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ይላሉ እነዚህ ቡድኖች ሀገራዊ አንድነቱ እና የህዝቡ ትስስር ይላላል። እንዲያውም ያ አይነቱ ፌደራሊዝም አንድነቱን እየሸረሸረው ይሄዳል የሚል ስጋት ያነሳሉ። እነዚህን ቡድኖች ብሄረሰባዊ ፌደራሊዝሙን የሚደግፉ እና ተገቢ ነው የሚሉ ሀይሎች የቀድሞውን ስርዓት ለማምጣት የሚተጉ፥ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ፌደራሊዝም ሰበብ ህዝቡን ከፋፍለው ድምጹን ከፍ አድርጎ ማሰማት እንዳይችል ለማድረግ የሚሰሩ ናቸው የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ኦነግን የመሳሰሉ ቡድኖች ደግሞ እነኚህ ሰዎች "የአያቶቻቸውን ስርዓት" ለማስቀጠል እና የህዝቦችን ትግል ለማዳከም እንጂ የህዝቦች መብት አሳስቧቸው አደለም በሚል ይወነጅላሉ።

ብአዴን/ኢህአዴግ የሚያቀርቡት አማራጭ ደግሞ አዎን ህዝቦች ብሄራዊ አንድነታቸውን ተከትለው ፌደራላዊ መንግስት ማቋቋም ይችላሉ። በሀገራችን ታሪክ ቀድመው የነበሩ ስርአቶች ሆን ብለውም ይሁን ባለማወቅ ያደረሷቸው ጭቆናዎች ፍትህ የማጣት የመበዝበዝ ብቻ ሳይሆን ብሄረሰባዊ ጭቆናም የነበረባቸው ናቸው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም ብሄሮች ማንነታቸው ለጥቅምም ለበደለም ታርጋ የማይሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር መስራት አለብን ይላሉ። ለአንድነት ምክንያት የሚሆነን እና አንድነቱን የሚያቋቁሙት መሰረታዊ ጉዳዩች ግን የፌደራል ስርአቱ አከላለል ሳይሆን ለአንድነት መነሻ የሚሆኑን ጉዳዩች ናቸው በማለትም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ። አንደኛ ህዝቦቿ በታሪክ ሂደት ያፈሩት የጋራ ቅርስ እና መቻቻል ሁለተኛ ደግሞ ከጦርነት እና ከጸጥታ ስጋት ጸድቶ በማያውቀው ቀጠና ጥቅሞቻችንን በተሻለ ለማስጠበቅ እና ደህንነታችንን ለመጠበቅ ከጠንካራ አንድነት የተሻለ አማራጭ የሌለን መሆኑ ነው። ስለሆነም ይላል ብአዴን/ኢህአዴግ ህዝቦች አንድነቱን የሚመርጡት ባለንበት ቀጠና እና ባለን ታሪክ አንድነቱ የተሻለው እና የማያወላዳው አማራጭ በመሆኑ እንጂ እንዳንገነጣጠል በሚል ስጋት ብሄሮች ወዲያና ወዲያ በክለላ ስለተሰፉ አደለም ይላል። ይሄን በወሳኝነት የሚቃወሙት ደግሞ መኢአድ አንድነት እና ኢዴፓን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ናቸው። ሰማያዊ ፓርቲም ከሰሞኑ ይሄንኑ ጎራ የተደባለቀ መሆኑ አይዘነጋም።
የመገንጠል/ አንድነት ጥያቄ
============================================
መገንጠል እና አንድነት በብሄራዊ ማንነት እና በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ አደሉም። ለመገንጠልም ለአንድነትም አስቻይ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው። ለምሳሌ ሀገራችን አንድ ሆና ለመቆየት አንድ ሆና ለዘመናት መቆየቷ አንድ አስቻይ ሁኔታ ነው። በዚህ ሂደት ህዝቦች ተመሳሳይ እና ተቀራራቢ ፍላጎት እና ትውውቅ የፈጠሩ መሆኑ ሌላው አስቻይ ሁኔታ ነው። በዚህም ሂደት ለጋራ ጥቅሞቻቸው የሚታገሉ ቡድኖች የተፈጠሩ መሆኑና በጋራ እየሰሩ መሆኑ ሌላው አቋቋሚ ሁኔታ ነው።

ለመገንጠል ትልቁ አስቻይ ሁኔታ መበደል መበዝበዝ እና ከሌላው በተለየ ሁኔታ ከልማቱ ተጠቃሚ መሆን አለመቻል ነው። ስለሆነም መገንጠል እንዳይከሰት እና እንዲመነምን ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር አንዱ ጉዳይ ነው። አገር ባይለማ እንኳ ድህነትን እኩል በፍትሀዊነት ማካፈል የሚችል መንግስታዊ ስርአት መፍጠር ተገቢ ነው። ድህነት ግን በባህሪው ህዝብን ለአመጽ ሊያነሳሳ ስለሚችል እና መገንጠልን የመሳሰሉ አደኛ አማራጮችን ለመቀበል የሚጋብዝ በመሆኑ ፈጣን ልማት ማስመዝገብ መቻል ሁነኛ የቤት ስራ ነው ማለት ነው። በመሆኑም የመገንጠል አንድነት ጉዳይ የፍላጎት ሳይሆን ከተጫባጭ ጥቅሞች እና የስርዓት ባሕሪ የሚመነጩ በመሆኑ አንድነትን ማጠናከር የሚፈልግ ማህበረሰብ አንድነቱን የሚያቋቁሙ ሆኔታዎችን መመገብ ነው የሚኖርበት። ይሄ የጋራ የቤት ስራ ነው። ለማንም ለብቻ የሚተው ማንኛውም ቡድን በተለየ መልኩ ተቆርቋሪ ሊሆንለት የሚገባ ጉዳይ አደለም።

በመሆኑም አንድነት እና መገንጠል ሲነሳ አንድነቱ በተለየ የሚጠቅመው ቡድን ባለመኖሩ ለአንድነት በተለየ የሚሰራ ቡድን ወይም ህዝብ አይኖርም። በሌላም በኩል ደግሞ መገንጠሉ በተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርገው ቡድን ባለመኖሩ እባክህ አትገንጠል ተብሎ መማጸኛ የሚቀርብለት ቡድን እና ሕዝብም የለም ማለት ነው። ሁሉም በአንድነቱ የሚያገኘው በመገንጠሉ ደግሞ የሚያጣው ጥቅም በመኖሩ ነው አንድነቱን አብልጦ መርጦት የሚኖረው።

ጉዳዩ ይሄ ከሆነ በሀገራችን ሁለት ቡድኖች መኖር የለባቸውም። አንደኛው ዋ እገነጠላለሁ አርፋችሁ ቁጭ በሉ የሚለን ቡድን ሊኖር አይችልም። አይገባምም። አንድነት ለጋራ ጥቅም የሚፈጠር በመሆኑ። ሁለተኛው ደግም ሊኖር የማይገባው ቡድን ደግሞ ያለኔ የዚህ አገር አንድነት የትም አይደርስም ነበር የሚል ነው። ምክንያቱም አንድነት በሁሉም ህዝብ ፍላጎት እንጂ በጥቂቶች ምልጃ የሚቆም ባለመሆኑ። በመሆኑም የአንድነት መገንጠል ጉዳይ ከነዚህ አስተሳሰቦች መፋታት አለበት።
ከዚህ ተነስተን ከተመሳሳይ ብሄር የሚነሱ የፖለቲካ ሀይሎች ይኖሩ ከሆነ ሊኖራቸው የሚገባው የፖለቲካ ልዩነት ምን ላይ መመስረት አለበት የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል። ለምሳሌ የጠቀስናቸው በወሳኝነት በአማራ ኤሊቶች የሚመሩ ፓርቲዎች ልዩነት ምንድነው መሆን ያለበት ብለን እንጠይቅ።
የፓርቲዎች አማራጭ ምን ይሁን?
================================================
ለምሳሌ በወሳኝነት በአማራው ተሳትፎ የሚደራጅ ፓርቲ ልዩነት ሀገራዊ የፌደራል መዋቅሩን ብሄር ተኮር አይሁን፣ የአንድነት/መገንጠል ጥያቄ እንዲህና እንዲያ ይሁን ከሚል አልፎ በወሳኝነት የፓርቲዎቹ ልዩነት መመስረት ያለበት በመንግስት ባህሪ ላይ መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ አለኝ። ህዝቦች በገዛ ቋንቋቸው መጠቀማቸው እና የራሳቸው አስተዳደር በመፍጠራቸው መቼም ቅር ይሰኛሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ራስን ማስተዳደር ተፈጥሯዊ ባህሪ በመሆኑ ማንም ራሱን በማስተዳደሩ ቅር ሊለው አይችልም። እንዲያውም ያን ሲነፈግ ለትግል ይነሳሳል። አሁን ፌደራላዊት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የብሄረሰብ ራስ ገዝ አስተዳደር አማራጭ ይቀለበሳል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል።

ሀቁ ይሄ ከሆነ የፓርቲዎች አማራጭ መሆን ያለበት መንግስታዊ ባህሪው ላይ የተንጠለጠለ ነው። መንግስት የፍትህ እና የደህንነት ስራ ከመስራት የዘለለ ሚና የሌለው ቢሆን ይሻላል ወይስ እንደ አስፈላጊነቱ ህግና ስርዓትን ከማስጠበቅም አልፎ በልማቱ ስራ ላይ የራሱ ሚና ያለው መሆን አለበት በሚለው ፍልስፋና ዙርያ የኛን አገር ሁኔታ ከግምት አስገብቶ መከራከር ይገባል። ያን ከግምት ባስገባ ፖለቲካዊ መዋቅር ዙርያ ህብረብሄራዊ መልክ ያለው የፖለቲካ ቅንብር መፍጠርም ሌላው ጉዳይ ነው። ህብረብሄራዊ ቅንብሩ የሀሳብ ክርክሩን ተከትሎ በባህሪው የሚፈጠርም ይሆናል።

እስካሁን ያለው ሁኔታ ግን የሚያሳብቀው ፖለቲከኞቹ እስካሁን ሊያምኑት ያልፈለጉትን ግን የሆነውን ሀቅ ነው። በአንድ በኩል ብሄረሰባዊ ማንነት እና አስተዳደር ላይ (እስከ መገንጠል ይለጠጣል) የተመሰረቱ ግራ ዘመም ፓርቲዎች ያሉበት ሁኔታ አለ። ይሄ እነ አረናን የነመራራን እና የበየነ ፔጥሮስን ፓርቲ ያስታውሰናል። በሌላ ገጹ ደግሞ ከአንድ ብሄር የሚቀዱ ኢሊቶች ያቋቋሟቸው ፓርቲዎች (ቀኝ አክራሪ ብለን ልንወስዳቸው እንችላለን) የተሰለፉባቸው ናቸው።  ይሄ የሀይሉ ሻወልን የልደቱን እና የነ ግርማ ሰይፉን አንድነትን ያጠቃልላል። እነዚህ ሁለት ቡድኖች የሚጋሩት አጀንዳም ሳይኖር ነው ለመዋሀድ እና በጋራ ለመስራት ጥረት የሚያደርጉት። አንደኛው ገንጣይ ነህ መባሉን ፈርቶ ሌላኛው ደግሞ ከአንድ ብሄር የተሰባሰባችሁ የቀድሞውን ስርዓት ለመመለስ የምትሰሩ ቡድኖች ናችሁ የሚለውን ትችት ለመሸሽ ከመገናኘታቸው በቀር የሚጋባ ፕሮግራም የላቸውም።

መሀል ላይ የሚገኘው ብአዴን/ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ ህዝቡ በዚህ ሰላም በሌለው ቀጣና ይቅርና ሰላማዊ በሆነም ከባቢ ቢሆን ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና ፖለቲካዊ ተሰሚነት ያለውን አብሮ የመኖር እና አንድነት ይዞ መቀጠል አለበት። ይሄ ሆኖ ሲያበቃ ግን ከባቢያዊ አስተዳደሩ የህዝቦችን ባህል ወግና ቋንቋ መሰረት ሊያደርግ ይገባል የሚል መነሻ አለው። ይሄ በህዝቦች እኩልነት እና በፍትሀዊ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ሊመሰረትም ይገባል ይላል። የምንመሰርተው ስርአትም በተከታታይ ይህንን እያረጋገጠ መሄድ ይኖርበታል ከሚል መደምደሚያ ይነሳል።
እንደ መደምደሚያ
==============================================
የሆነ ሆኖ የሀገራችን የፖለቲካ ሀይሎች አሁንም ድረስ ፌደራላዊ ስርአቱ እና የአንድነት/መገንጠልን ጉዳይ በወጉ ደምድመው ከዚያ ከፍ ባሉ ሌሎች ጉዳዩች ላይ መስራት አልቻሉም። ቀኝ ፖለቲከኞች በዋናነት በአማራ ኤሊቶች የሚመሩበት እና በቀድሞው ስርአት ናፋቂነት የሚወነጀሉበት፤ አክራሪ ግራ ዘመም ፖለቲከኞች ደግሞ መገንጠልን በማስፈራሪያነት በማቅረብ ራሳቸውን ለአንድነት ስትሉ ተለማመጡን በሚል አሳንሰው የሚያቀርቡበት ሁኔታ እንዳለ እንታዘባለን።

አንደኛው ብሄረሰባዊ ማንነቱን ፈጽሞ የዘነጋ በሚመስል ቅርጽ የሚቀርብና ለአገር አንድነት ያለኔ ማን አለ በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል፤ ገባ ብለው ሲያዩት ግን እኛ አማሮች ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈልነው መስዋእትነት እንዴት ይረሳል እያለ ማቅራራት የሚወድ ሆኖ ይገኛል። ትንሽ ገፋ ከተደረገም ስለብሄር ማሰብ አልወድም እያለ የሚምል የሚገዘትም ቢሆን በየመስሪያ ቤቱ ያለውን ትግሬ እየቆጠረ የበላይነት ተወሰደብኝ በሚል የሚብሰከሰክ ሀይል ነው። እንደሚሰብኩን ኢትዮጵያዊውን መልኩና ብሄሩ ሳያሳስባቸው የሚቀበሉ አደሉም። መፍትሄው አማራ ነኝ ኢትዮጵያዊም ነኝ። እንደ ህዝብ አማራውም ፍትሀዊ ጥቅሞቹ እንዲከበሩለት እንደ አገር ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር እና ለኢኮኖሚያችን በተከታታይ ማደግ እሰራለሁ ማለት ነው።
ግራ አክራሪው የህዝቦችን የመገንጠል መብት ደጋግሞ በመደለቅ ይህንን አገር እንዳንተረትረው በሚል ዝማሬ እያስፈራሩ ቦታ ስጡን የሚሉ ሀይሎችም ሆኑ አክራሪ የአንድነት አቀንቃኞች ከዚህ ነጠላ ዜማ ወጥተው ህዝቦች ማንነታቸው ተከብሮ በሚኖሩባት አገር የሚኖሩ ፓርቲዎች ሊኖራቸው የሚችለውን ገንቢ ሚና ለመጫወት ከብሄራዊ ማንነት ከፍ ያሉ የፌደራል መንግስትን ሚናዎች እያነሱ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ በሚችሉበት አግባብ መጓዝ ይኖርባቸዋል። ሀገራዊ አጀንዳም በመቅረጽ ለአንድነቱ መጠናከር የበኩላቸውን ሚና መወጣት ቢችሉ የሚል ሀሳብ አለኝ።

የሆነ ሆኖ በስተመጨረሻ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት እና ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያላቸው አማራ ኤሊቶች የሚመሯቸው ፓርቲዎች አንድነት እና ኢትዮጵያ የሚል ቅኝት ብቻ ሳይሆን የብሄሮች ራስ ገዝ አስተዳደርም ጉዳይ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተረድተው፤ በሌላም በኩል እነሱን እየጠቀሰ ዛሬም ቢሆን ማንነትህ አልተከበረም እድሉን ካገኙ ወደ ቀድሞው ሁኔታ የሚመልሱን ነፍጠኞች አሉ እያሉ የሚሰብኩ ኦነግን የመሳሰሉ ቡድኖች አፍ ለማዘጋት የሚችል አማራጭ መያዝ ይኖርባቸዋል። ብሄረሰባዊ ፌደራላዊ መዋቅሩን መቀበል ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ እመርታ ይሆናል። አለበለዚያ እንዲህ አይነት ፓርቲዎች ወይ ለተወለዱበት ማህበረሰብ የማይጠቅሙ አለያም ደግሞ ለአገራዊ አንድነታችን መጠናከር የማይሆኑ እርባና ቢስ መዋቅሮች መሆናቸው አይቀሬ ይሆናል።

No comments:

Post a Comment