Wednesday, January 2, 2013

አድርባዮች

አድር-ባይ አድር ብሎ ያልሆነውን ነው የሚል የሆነውን ደግሞ የለም አልተደረግም ብሎ የሚክድ ነው ይህን እንደ አስተዋጾ ቆጥሮም ለሞላጫ አድራጎቱ ዳረጎት ከአለቃው የሚጠብቅ መሰሪ ግን በራሱ መተማመን የማይችል ምስኪን ነው

አድርባይነት በየትኛውም ትግል እና ግንኙነት ውስጥ ብዙ ግዜ ችላ የሚባል ግን ውስጥ ውስጡን ሰፊ ጉዳት የሚያደርስ ምግባረ ብልሹነት ነው የገዚ ፓርቲም ይሁኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አድርባዮች መሰረታዊ ባህሪያቸው ያው እና አንድ በመሆኑ የሚደቅኑት ስጋት ይመሳሰላል

አድርባዮች ሁሉንም ስራና ግንኙነት የሚወስኑት "ለኔ በዚህ ውሳኔ ወይም ተግባር የማገኘው አለያም የማስጠብቀው ጥቅም ምን አለ" በሚል ነው እንጂ ሌላ አገራዊ አካባቢያዊና ማህበራዊ ጥያቄ መጠየቅ ምርጫቸው አደለም

ለዚህ ሁሉ የሚዳርጋቸው ግን በጥረቴ አድጋለሁ እሚል በራስ መተማመን የሌላቸው መሆኑ ነው በራስ ጥረት መስራት ቀርፋፋነትና ሙደኛ አለመሆን ይሆንባቸዋል አቁዋራጩ መንገድ ሁሌም ቅንጥብጣቢ የሚያገኙ ከመሰላቸው አጀንዳ እና አለቃ ጋር መንፈስ ነው 

ማቸው ሁሌም እድገቶችንን እና ሹመቶችን የሚያጸድቀውን ሰው በገባቸውም ባልገባቸውም በሚመለከታቸውም በማይመለከታቸውም ጉዳይ ላይ መደገፍ ነው እነሱ በመቶ ብሮች የሚቆጠር ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ከመሰላቸው ሌላ ሰው ያለ ጥፋቱ ወይም ትንሹዋን ጥፋቱን አጋነው ከስራ ለማባስባረርና ሺዎችን ሊያሳጡት ከመስራት ወደላ አይሉም ብቻ ያ ድርጊት ያሳድገናል ብለው ይመኑ ተስፋ የሚያደርጉትን ሰው ያስደስታል ብለው ይገምቱ እንጂ ወደሁዋላ ማለት አይነካካቸውም

እኚህ ሰዎች እጣ ፈንታችንን ይወስናል ብለው የሚያምኑትን ሰው ሆድ ያራራል ብለው ካሰቡ የዚያን ሰው ጉዋደኞች እና ዘመድ አዝማድ ከመቅጠር፣ በጨረታ ከማሳለፍ ወይም ያለአግባብ ከመጥቀም ወደሁዋላ የሚሉ አይደሉም ጅቦች ናቸው

እንደዚህ አይነት የስነምግባር ልሽቀት ያለባቸው ሰዎች ሁሌም ያ "የጣ ፈንታቸውን ወሳኝ" የሚሉትን ሀላፊ ማሞካሸትሲሳሳትም ሳይሳሳትም ትክክል ነህ ማለት፣ እርስዎ እንዳሉት ብሎ የተገፋውን መጣል፣ የተነሳውን መስቀልና የተደነቀውን ምንተስኖት ማድረግ ሁነኛ መለያቸው ነው

ሌላው ለማዳው ባህሪያቸው ያንን አለቃቸውንና አጋሮቹን እሺ እሺ፣ አዎ አዎ፣ ልክ ነህ ልክ ነህ ማለት በተቃራኒው ያ ሀላፊ ፊት ነስቸዋል ብለው የሚያስቸውን የለም ልክ አደለም አይሆንም ተሳስተሀል አምህ ጸረ ዳሽ ነው ማለት ሱሳቸው ነው

እንዚህ አይነት ሰዎች ተስፋ በሚያደርጉት አለቃቸው በመተማመን ላታቸውን ደጅ የሚያሳድሩ ቢሆንም የለየላቸው ፈሪዎች ናቸው  በተለይ የዛ ተስፋ የሚያደርጉበት አለቃቸው ፊት የጠቆረ ቀን ፊታቸው ሲጨልም ቀኑ ሲመሽባቸው ያ ሙሉ በኩለሄ አለቃቸው ፊቱ የፈገገ ቀን ቀናቸው ሲበራ የሚኖሩ የበራስ መተማመናቸው ማብሪያና ማጥፊያ በአለቃቸው ግንባር ላይ የተገጠመላቸው በምርጫቸው የላሸቁ የምርጫቸው ምርኮኞች ናቸው

የአለቃቸውን ክብርና የማዘዝ ስልጣን አክብረው ሲያበቁ ይጠቅማል የሚሉትን ነጻ ሀሳብ ማራመድ የትንታግ ያክል የሚፈጃቸው ደፈር ያሉ በጥረታቸው እንጂ ተሞዳሙደው በማደግ የማያምኑ የተሳሳቱ ቀን ታርመው ለመሄድ ትክክልም የሆኑ ቀን ባበረከቱት አስተዋጾ ሊረኩ የሚሹ ጎበዞች ሲናገሩ የሚያንገፈግፋቸው

ትግልን የሚማጸኑትን ሀላፊ አቁዋም መደገፍ ብቻ አድርገው የሚያዩ ሃሳቡ ልክም ይሁን አይሁን ሌላ አማራጭ አለ ብሎ የሚያምን ባልደረባቸውን የሚያሳጡ እንዲህ ያለ የትግል መንፈስ ያለውን ሰው ሲመቻቸው የሚያሳድዱ ሊያሸንፉት እንደማይችሉ የገመቱ ሰሞን አጋድመው እስኪያቆስሉት በደማቅ ሰላምታ ሊያዘናጉት የሚሞክሩ የትግል እንቅፋቶች ናቸው በጥረት የማደግ ሳንካዎች

በራስ ጥረት ማደግ በራስ እቅድ እና አቁዋም መመራት ያማቸዋል። ለነሱ ነገን በራሳቸው ጥረት እንዴት እንደሚያሳምሩት ማሰብ እማይቻል ነው ለአድርባዮች የራስን እቅድ ሳያሰልሱ ተግብሮ ማደግ እችላለሁ ማለት የዋህነት ነው

የስም ማጥፋት ዘመቻቸው ደግሞ ሌላው ሁነኛ መሳሪያቸው ነው አድርባዮች ልክ ሎላ ካሬይሮ የቤላ ካላሚዳዴስ ተከታታይ ፊልም ዋና ገጸባህሪ (የስፓኒሽ ሳጋ ፊልም ነው) ላይ እንደሆነው ይህን እና ያን እድገት ያገኛል የሚሉትን ጎበዝ ያለርህራሄ በማያቀው ጉዳይ ሲያጠለሹት የሚውሉ ጥቁር ቀለሞች ናቸው

ይህንንም አስጸያፊ ተግባራቸውን ታዲያ ለመንግስት ስራ መሳካት ለገዚው ፓርቲ እቅዶች ስኬት ካላቸው ተቆርቁዋሪነት አንጻር ያደረጉት ለማስመሰል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም በቅጡ ለማያውቁት እና ለማያብራሩት ፖሊሲ ጠበቃም መሆን ያምራቸዋል ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አሉ- መነሻቸው የመሾም ርሀብ ሆኖ ሳለ

እኒህ ሰዎች በጥረትና በብቃታቸው ብዙ ሊያደርጉ የሚችሉትን ሰዎች ቶሎ እድሎችን አግኝተው የሚቻላቸውን አስተዋጾ እንዳያበረክቱ ከባድ መሰናክል ይፈጥራሉ በርግጥ ጀግኖች መንገዳቸው ቢረዝምም ትግላቸውን ዳር ከማድረስ ወደላ የማይሉ ቢሆንም

በርግጥ ስራ አስኪያጅ ሲያዝ ያንን ትእዛዝ ተቀበሎ መፈጸም ይገባል አድርባይ አለመሆን አሰሪ በተሰጠው ሃላፊነት ሰራዎችን ሊያሰራ ሲጥር እቅፋት መሆን እና መጨቃጨቅ ማለት አደለም  ጠንካራ ሰራተኞች የተሰጣቸውን ሀላፊነት በትጋት ፈጽመው ሲያበቁ ለውይይት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ግን የመሰላቸውን እና ያዋጣል ብለው የሚያምኑትን አቁዋም የማራመድ መብትም ሃላፊነትም እንዳለባቸው የሚያውቁ ናቸው

በመሆኑም እንዲህ አይነቶቹ ጎበዞች በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን የማመንጨት ብቃት ያላቸው በአማራጭ ሀሳቦች መቅረብ የሚያምኑ ሀሳብን በተመለከተ ደግሞ ከስራ አስኪያጃቸውም የተለየ ሀሳብ ማራመድን እንደ አንድ ማንኛውም የሀሳብ ልዩነት የሚወስዱ ለሃላፊ ክብር መስጠት እንደሚገባ ያ ክብር ግን የተባለውን ሁሉ አሜን ማለትን እንደማይጨምር የሚያውቁ ናቸው

ጨቅጫቃና ሰነፎች ግን አደሉም ስራን በስራ ቦታቸው የሚረቱ የሀሳብ ትግል በሚደረግበት መድረክ ደግሞ የበሰለና መረጃ-ጠገብ ውይይቶች መጫር የሚችሉ ናቸው

አድርባዮች በእገሌ እንዳለው ጀምረው እገሌ እንዳለው እያሉ የሚጨርሱ የእነ እገሌን ሀሳብ መልሶ ከማብራራት እና ድጋፋቸውን ከማሳየት በዘለለ የሚጨምሩት ቁምነገር የሌላቸው መሆኑን ይረዱዋል አድርባዮች በአንድ ወቅት እንደማቃቸው የዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንት እገሌ እንዳለው ብሎ የሚጀምርን ሰው አንተ ሌላ ሀሳብ ከሌለህ በቀር የሱን ስለሰማን እድትደግምልን እና ሰአት እንድታባክን አይፈቀድልህም ሊባሉ የሚገባቸው ውስጠ-ኦና ቃጭሎች ናቸው

አድርባይ ቃሉ ራሱ ገላጭ ነው ማደሪያውን ሊያመቻች ጥጋጥጉን የሚያስስ ጥገኛ እንደማለት ሲብራራ አድርባይ የሌሎችን ችግሮች እንዲያዳምጥ እና እንዲያይ የተሰጡትን ሁለት ጆሮዎችና አይኖች የከደነ ውስጥ ውስጡን የሚበላውን የግል ስግብግብ መሻቱን ካልሆነ የጋራ በሆኑ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ የማይሰለፍ እንዲያ ያለው ስራ የሚጠይቀውን ብቃት ተግቶ የማይገነባና ሊገነባም የሚሻ ህሊናዊ ምርጫ የሌለው ቀድሞ በአመለካከቱ ስብራት የከሰረ ሲለጥቅ በዚህ ሰንካላ ምርጫው የተነሳ በተግባሩና በስራዎቹ ብዙዎቹን ያለእዳቸው የሚያቆሽሽ ነው

የወገነለት ላስመሰለው አለቃውም ቢሆን በተባ እውቀት እና በተሳካ ተግባር ድጋፍ መሆን የማይችል ከመሆን አልፎ በምላሳቸው ውዛት ሳይሆን በህሊናዊ ብቃታቸውና በማያሰልስ ተግባራቸው የማገልገል አቅሙና ዝግጁነቱ ያላቸውን ሰዎች በተልካሻ የወሬ ፈጠራ እና አራጋቢነቱ የሚረብሽ ነው

ታዲያ ምን ይጠበስ? ለመሆኑ አድርባዩን እንዴት ከጨዋታ ውጭ ማድረግና ማረም ይቻላል?

መፍትሄው አድርባዮቹ ወሬ በማመላለስ የሚወስዱትን ብልጫ በመደበኛ መድረኮች እየተገኙ እግር በግር ማክሸፍ እና መደበቂያ ዋሻ ማሳጣት ነው ያን ማደረግ ሲቻል በወሬ ስልቻቸው መጠን ጥቅሞች የሚያገኙበት እድል እየጠበበ ሰራተኛ በጥረቱ ልክ ብቻ የሚለካበት አግባብ እየተፈጠረ ይሄዳል

ለአድርባዮች መፋፋት ለሙ መሬት በጥረትና በስራ የሚያምኑቱ ሰዎች ኩሩነት ነው ቁምነገሩ ኩሩ መሆኑ ሳይሆን በብልሀት አሸናፊ መሆን መቻሉ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል አለመልከስከስ አንድ ነገር ነው ልክስክሶች ካሸነፉህ ግን ኩራትህ የተሙዋላ አይሆንም ስለሆነም አድርባዮች ሊፈነጩ የሚችሉበትን ሜዳ በየትኛውም ህጋዊ አመራጭና ውይይት ማሳጣት የጎበዞቹና የባለምግባረ ሰናዪቹ ፈንታ ነው

እንዲህ ባለ የተጋጋለ የትጉሀን ትግልና አሰራር ባለበት መድረክ አድርባዮችም አድርባዮችን ዙርያዉን ከቦ መፋፋት የሚፈልግ አለቃም ቢኖሩ እንኩዋ ያሻቸውን የማድረግ እድላቸው ጠባብ መሆኑ አይቀሬ ነው በእንዲህ አይነቱ አውድ በሂደት ትጉሀኑና ባለምግባሮቹ በአሸናፊነትና በመሪነት የሚወጡበት መሆኑ አይጠረጠርም

ዳር ቆሞ አዬ አገራችን አድርባይ ይፈንጭብሽ ማለት በቂ አይደለም መጀመሪያም ቢሆን ችግሩ ለአድርባዮች ሜዳውን መልቀቁ ነበርና እናም በኔ እምነት ለአድረባዩቹ ሁነኛ አጋጣሚ የፈጠረላቸው አድርባይነትን አጸየፋለሁ የሚለው አካል ከትግሉ ሜዳ ዘወር ማለቱ ነው

አድርባዮች የስራውን እና የለውጡን ትግል ሜዳ እንዳይዙት ዋነኛው መላ ሜዳውን መቆጣጠር ነው ሜዳውን ወዲያው መቆጣጠር ካልተቻለም የተጋጋለ ትግል እያደገረጉ በመቆየት የአድርባዩችን የተመኙትን የማድረግ አቅም ማኮሰስ ያስፈልጋል ፈረንጆቹ  ክፋት የሚንሰራፋው ደጎች ሜዳውን ለክፉዎች ሲተውትና የሚችሉትን ደግነት መፈጸም ሳይችሉ ሲቀሩ ነው ያሉት ይህንኑ ተገንዝበው ይመስለኛል

ለአድርባዩች የምትተው አንዲት ጋት መሬት መኖር የለባትም እያንዳንዱ ክፍተት አድርባዩቹ የበለጠ እጃችንን እንዲጠመዝዙ የሚያስችላቸው ይሆናልና። አድርባይ ሳይሆን አገልጋይ መንፈስና ልምድ ይኑረን። የቀረው ይቆየን!!!

No comments:

Post a Comment