Monday, December 30, 2013

የአማራው፣ የኦሮሞው እና የትግሬው ዘረኛ ትረካዎች--- ክፍል 2



=======================
በዚህ ትንታኔዬ የኔ የሚባሉትንም ከመተቸት ወደሁዋላ አላልኩም። እውነታውን በጋራ መጋፈጥና በሀቀኝነት ችግሩን ፈተን ሁላችንም በጥረታችን ልክ አሸንፈን እና እኩል ተጠቃሚ ሆነን የምንኖርበት አገር ካልፈጠርን መዘዙ አደገኛ ነው ብዬ ስለማምን የሚመስለኝን ሁሉ ድፍረትና ሚዛናዊነትን አጣጥሜ ላቀርበው ሞክሬያለሁ። መልካም ንባብ።

ስጀምር በኔ አተያይ እንደ ብሄራችን የታሪክ ትረካችን ይለያያል። ታሪኩን እምንዘክርበት ስሜትና ወግም በዚያው ልክ የተለያየ ነው። አንዱን ታሪካችንን ከደማችን እየቀዳን እያነበብን ብዙ አይነት አድርገን ግራ እንጋባለን፣ ግራ እናጋባለን።

ጥቅል ድምዳሜዬን የሚጎሉትን ጉዳዩች ሞልታችሁ እንደምታነቡ በማመን ለኔ እንደሚታየኝ ከሶስቱ ብሄሮች፦ ኦሮሞ፣ አማራና ትግሬ የሚወለዱ የታሪክ ነጋሪያን እና አመስጣሪዎች እንዴት ታሪካችንን እንደሚያነቡት ላስረዳ።
===================
1 የአማራው ታሪክ ተንታኝ፦

የአማራው ታሪክ ተንታኝ በአመዛኙ የኢትዮዽያን ታሪክ የኔ ብሎ የሚያስብ፥ በሀገሪቱ በተካሄዱ መሰረታዊና ወሳኝ ጉዳዩች ላይ የራሱ ብሄር የተለየ ግዙፍ ሚና አለው ብሎ የሚያስብ፥ በመሆኑም በተነጻጻሪ አማራ ስልጡን ብሄር ነው ብሎ የሚያምን እና ለዚህ ተወልጄበታለሁ ለሚለው ብሄሩ አገር ግንባታ ታሪካዊ ሪከርድ ተጋድሎ ለመፈጸም የቆረጠ፥ ማን እንደኛ እያለ ማስረዳት እሚቃጣው፥ በዚህም የተነሳ ራሱን የተሻለና የዚሁ የተሻለው ታሪክ አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ የሚያስብ ሆኖ የቆየ ነው።

አማራው እኮ ማለት የሚቀናው በቀጥታም አዙሮም የብሄሩን ታላቅነት ለመስበክ ወደሁዋላ የማይል ነው። የዚህን አገር ታሪክ የማንነቱ መገለጫና የአማራነቱ ክፋይ አድርጎ ስለሚያይ ብሄራዊ ማንነቱን ከታሪኩ ለይቶ ማየት የተሳነው ሊባል ይችላል። ይሄን ታሪክ ሊጠይቅ የሞከረውን ሁሉ ሀገራዊ ፍቅር የሌለው፣ ገንጣይ አስገንጣይ እያለ የሚፈርጅ ነው። የታሪክ አሳሳሉ ደግሞ አድናቂ እና አወዳሽ ከመሆን አይዘልም።

የዚህ የአማራ ታሪክ ተራኪ መሰረታዊ ስህተቶች ሁለት እንደሆኑ እረዳለሁ። አንደኛው የሀገሪቱን ታሪክ የአማራ ታሪክ ብሎ መውሰዱና ሁለተኛ ደግሞ የአማራን ማንነት እና ትልቅነት ከዚህ ታሪክ መወድስ ጋር አሰናስሎ የሰፋው መሆኑ ነው።

አማራው ከዚህም ታሪክ ጋር ይሁን አይሁን ክቡርነቱ እንዲያው ከተፈጥሮ እንደማንኛውም ህዝብ የሚቀዳ መሆኑን አይረዳም። በመሆኑም ለዚህ የታሪክ መምህር ታሪኩን መንካት አማራን መንካት፤ ይህን የሱን የታሪክ ትርክት አለመቀበል የአማራን የበላይነት እና የተሻሌነት አለመቀበል አድርጎ ይወሰደዋል። በቀጥታ ማንነቴ ተነካ ግን አይለንም። ሀገሬን ኢትዮዽያን የነካ እምዬ ኢትዮዽያን የደፈረ በሚል መፈክር ይህን የታሪክ ትርክት የተቹትን ያሳድዳል። ያኔም አሁንም።

በመሆኑም በኔ እምነት ሀገራዊ ታሪክ ሀገራዊ አንድነት እና ብሄራዊ ማንነቱ የተምታቱበት በመሆኑ የሌላውን የታሪክ ትርክት ለመስማት እንኳ እድል የማይሰጥ ይመስላል።


===========================
2 የኦሮሞው ታሪክ ተንታኝ

የተለመደው እና ጎልቶ የወጣው የኦሮሞ ታሪክ ተንታኝ ደግሞ ኢትዮዽያ እሚባለው ሀገር እኛን እሚመለከት አደለም፤ ተገደን ነው በዚህ አገር ጥላ ውስጥ እንድንኖር የተደረግነው ብሎ የሚያምን ነው። የዚህን አገር ታሪክ ከሚኒሊክ ጀምሮ መተረክ የሚወድ፤ ኦሮሞ ለደረሰበት እንግልት ሚኒሊክን ዋነኛ ተጠያቂ የሚያደርግ የታሪክ አመስጣሪ ነው። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ለዚህ የታሪክ መምህር የኦሮሞ ችግር ምንጭ አንድነቱ ነው።

የዚህን አገር ታሪክ ሲያነሳ ኦሮሞ ጦረኞች አሸናፊ የነበሩበትን፤ በተመሳሳይ መንገድ ሌሎችን ድል ነስተው በጦር ሜዳ ረተው የኖሩበትን እና ተመሳሳዩን ግዳያ በሌሎች ላይ የፈጸሙበትን ታሪክ ማንሳት ነውሩ ነው። እሱ አይነካም። የትረካው መነሻም መድረሻም ምሬት፣ የኦሮሞ ህዝብ እንግልት እና የደረሰበት ሰቆቃ ነው።

እንዲህ አድርገን የሚል ዜማ የለም ይሄ ተደርጎብን፣ ያ ተደርጎብን፣ እንደ ህዝብ ሳንቆጠር፣ ተንቀን፣ ተዋርደን በሚል የሚሰፈር የተበዳይነት እና የሰቆቃ ቀማሽነት ትርክት ብቻ። ከአማራው የታሪክ መምህር ጋር እጅጉን የሚቃረን አቀራረብ ነው። የኦሮሞው የታሪክ መምህር እቺ አገር የኔ አደለችም፤ ታሪኳ ማንነቴን ክዷል፤ አዋርዳኛለች በመሆኑም ማንነቴ የሚከበረው ከዚህች አዋራጅ አገር ጋር ያለኝን ግንኙነት ስበጥስ ነው ይላል። የአማራው መምህር ደግሞ እቺን አገር መገንጠል ማለት የኔን ማንነት እና ተጋድሎ ከንቱ ማድረግ፤ ማንነቴን የምቀዳበትን ታሪካዊ መፈክር መቅደድ ነው አይሆንም ይላል።

አንዱ ከጀግና ነኝ ባይነቱ እና ከዚያ ታሪካዊ ውሎው ማንነቱን አስተሳስሮ የዚያ መተቸት የማንነቱ መክሰር ሲያደርገው ሌላኛው ቡድን ደግሞ በማንኛውም መልኩ ከዚህ ታሪክ ጋር መቆራኘት ውርደቱን ንቀቱን በማስቀጠል ማንነቱን ማርከስ አድርጎ ይቆጥረዋል።
==============================
3 የትግራዩ የታሪክ ተንታኝ

የትግራዩ ታሪክ ተንታኝ ደግሞ ታላቅነቱን በጦር ሜዳ እየተቀናቀነ ሲፎካከረው የነበረውን የአማራውን ታሪክ መምህር ደካማ ጎን የሚፈልግ፤ ልክ ፊውዳሎቹ በግዜያቸው አንዱ ሌላኛው ላይ እንደሚዶልቱት የአማራውን ታሪክ መምህር የተዛነፉ የሚላቸውን ትረካ እያነሳ ኦሮሞውን እና ሌሎች ብሄሮችን ያስደስትልኝ እና ድጋፍ ያስገኝልኛል በሚል መንገድ እየቀረጸ አማራው ታሪክ አመስጣሪ የሚሳሳላቸውን ድሎቹን ያለርህራሄ እየዳጠ ተበድያለሁ ለሚለውና እና ተዋርደናል ለሚሉ ሌሎች ብሄሮች ጥያቄ ምን ያህል ክብር እንዳለው ለማሳየት የሚተጋ ነው።

ይሄ ትረካው ታሪኩን በትክክል ያቅርብ አያቅርብ ግድ የለውም። ከሌሎቹ ብሄሮች ድጋፍ ያስገኝልኛል ብሎ ካመነ ታሪኩን ባሰኘው መልኩ ሸንሽኖ ከማቅረብ ወደሁዋላ የሚል አደለም። በመሆኑም የፊውዳሎቹን ታሪክ ሸንሽኖ እያቀረበ የአማራውን ታሪክ አመስጣሪና ታሪካዊ እውነታዎቹን በሚክድ መልኩ ለዛሬ እና ለነገ አላማው በሚል መለኝነት እና ሚዛናዊነት ያልታከለበት ትረካው የሚዘምት፤ በሂደቱም ማንነቱን ከዚያ ታሪክ ጋር ሰፍቶ የሚያየውን በተለይ አማራ የታሪክ መምህር ልብ በሚያደማ መስመር የሚጓዝ ነው።

ይሄ የታሪክ ተንታኝ አላማው የኦሮሞ ወይም የሌሎች ብሄሮች መበደል አይመስልም። አላማው አማራውን የታሪክ መምህር በማዳከም እና ተበድለናል የሚሉ የታሪክ መምህራኖችን ስሜት በመጠገን ለራሱ የጫወታውን ሜዳ ማመቻቸት ነው። ይሄም ታሪክ አመስጣሪ ለሀገር አሳቢ እሚባል አደለም። በመሆኑም ይሄ ቡድን ዋነኛ ተቀናቃኜ ነው ብሎ የሚያስበውን የአማራውን የታሪክ እና የፖለቲካ ቡድን ማዳከም እና ሁኔታውን ለራሱ ማመቻቸት እንጂ በተሟላ መንገድ ችግሮችን መፍታት አደለም።
===========================
ሶስቱም ግን አንድ ነገር ያመሳስላቸዋል - የስልጣን ጥማታቸው። ይሄ ትርክታቸው ያን ከግምት አስገብቶ እንጂ የሌሎችን ሁኔታ በመረዳት የሚቀርብ አደለም። አማራውም የታሪክ ሰው በእምዬ ኢትዮዽያ ስም ለራሱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት፥ ኦሮሞውም በአባት ኦሮሞ ምድር ስም እና በተበድያለሁ መንፈስ ተነጥሎ በአንድነት ስር አላገኘውም የሚለውን ስልጣን ለመፈናጠጥ የሚጥርበት፤ ትግሬው የታሪክ አመስጣሪም አዬ በደላችሁ በሚል ከራሱ በራቀ መፈክር የሌሎችን ድጋፍ በመሻት ተቀናቃኜ የሚለውን የአማራውን ታሪክ መምህር ዘርሮ ስልጣኑን መፈናጠጥ ነው አጀንዳው።

ታሪካችን እንደ ነበረ እና በተፈጸመበት ገጽታው ሳይነበብ የቀረውም እኒህ የታሪክ መምህራን እና ፖለቲከኞች ስልጣን ለመፈናጠጥ የሚያመቻቸውን አግባብ በማማተር ታሪኩን በየፊናቸው እንዳሻቸው ለስሜት እና ለድጋፍ ቅርብ በሆነ አግባብ ስለሚያነቡት ነው። እያነበቡትም ስለሆነ ነው።

የሰሞኑ የታሪክ ንበታችን እሰጥ አገባ የሚመነጨውም ከዚያ ተረክ የተቀዳ በመሆኑ ነው። የተወሰነ አማራ የለም ታሪካችን ጥሩ ነበር ስህተትም ካለው ለአሁን ፋይዳ የለውም በሚል ሲያልፍ እና ከዚህ በተቃራኒ የቆሙት የኦሮሞና የትግሬ አስገንጣዮች ናቸው ሲል፤ የተወሰነ ኦሮሞ የለም አሁንም አማራው ለደረሰብን እንግልት እና ውርደት ቦታ አይሰጥም ጭራሽም ይክደዋል በመሆኑም በዚህ አገር አንድነት ለምን መቀጠል እንደሌለብን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው በሚል የሚመቸውን አጀንዳ ሲደበድብ፤ የተወሰነው ትግሬ ደግሞ ሚኒሊክ አድርሶብኛል የሚለውን የዚያ ዘመን መከፋፈልና ደባ በውስጡ ደብቆ አዎን ለዚህ አገር ችግር ሁሉ ተጠያቂው ኦሮሞዎች እና ሌሎች ህዝቦች እንደምትሉት ሚኒሊክ ነው፤ አሰብና ወደብ በሉት፣ የብሄር ጭቆና በሉት፣ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ የሚኒሊክ ስሪቶች ናቸው ይላል። እውነት አይጠፋውም ግን አላማው እና እሚተረክበት መንገድ አደገኛ ገጽታዎች አሉት። የሆነ ሆኖ የምር ችግሩም መፍትሄውም እኛ ጋር ነው በሚል ይሰብኩታል።

ሁሉም ተነቃቅተዋል። ግን በአደባባይ ተማምነው ሁሉም ብሄር በሀገር ጉዳይ ላይ ባለቤት ሆኖ ራሱን በራሱ በአካባቢው በመረጠው መንገድ መርቶ፤ ያም የእኩልነቱ ማሳያ ሆኖ፤ በፌደራል መንግስት ደረጃ በኮታና በአቅም ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ በመርህ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመፍጠር ግን ሶስቱም ፍቃደኛ አደሉም።

ሁሉም እኔ መሆን አለብኝ ባይ ሆኗል። የተነቃበትን አጀንዳቸውን ያለማባራት ቀንና ማታ ከመለፈፍ የትኛውም ቡድን አልተመለሰም። መፍትሄው የምር ሁሉም በእኩልነት የሚሳተፍበት፣ ሁሉም በመንግስታዊ መዋቅሮቹ ተመጣጣኝ ውክልና እና ተሳትፎ የሚያደርግበት ሁኔታ መፍጠር ነው አይሉም።
==============================
ለዚህ ነው በአሁኑ መንግስታዊ ስርአት የትግሬ የበላይነት አለ በሚል በተለይ የጸጥታ መዋቅሮቹን በማሳያነት በመውሰድ እገሌ ብሄሩ ትግሬ ነው እገሌ ብሄሩ አማራ ነው እነ እገሌ ደግሞ ኦሮሞ ናቸው። እንዴ ምን እኩልነት አለ እዚህ አገር፤ ይህ ሁሉ ቦታ በነእከሌ በተያዘበት እያለ የሚዘምረው እኩልነት ዛሬም የለም የሚለውን ትረካውን ለማስረገጥ ነው።

በመሆኑም አሁን ያለውን ህገመንግስት እና ፌደራል ሲስተም ጠብቀን ሆኖም ግን በፌደራል ደረጃ የሚታየውን የቦታ ሽሚያ በእቅድ እና በሂድት መልክ አሲዘን፤ ጉዳዩን በቀናነት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ መፍታት የሚገባ ይመስለኛል። በኔ እምነት ታሪኩን የምናብራራበት አላማና በየጓዳችን ያለን ምክንያት የተለያየና ዘረኛ ብቻ ሳይሆን ስግብግብና መተማመን የሌለው ጭምር በመሆኑ ዛሬ ጀምረን በቅርብ ግዜ በየደረጃው የሰው ሀይል መመጣጠን በመፍጠር ህዝቡ በስርአቱ ላይ የማይናወጥ እምነት እንዲኖረው ማድረግ ወሳኝ ነው።

እማይናወጥ ስርአት የማበጀት ጉዳይ ብቁ ፓርቲዎች እና ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መዋቅሮችም በመፍጠር ረገድ የማይታካ ሚና ስላለው ለነገ የማይባል ስራ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሲሆን የዛሬው ከደም የሚንቆረቆር የታሪክ ትርክት በቅርቡ ጡረታ ይወጣና እውነተኛና ምክንያታዊ ታሪካዊ ተረክ ቦታውን ይረከባል። የቀረው ይቆየን።

No comments:

Post a Comment