Tuesday, September 3, 2013

የፖለቲካ ሀላፊነት እንደ ችግር መፍቻ ቃልኪዳን




አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ለህዝብና ለደጋፊዎቹ የሚገባው ቃልኪዳን ለውጥ ነው፡፡ በተገማች እና በሳይንሳዊ ዘዴዎች መመላከት ማሳመን ማነሳሳት የሚችሉ የለውጥ ቃልኪዳኖች፡፡ እንዲህ ያለ ቃልኪዳን መግባት ደግሞ አላማ ይጠይቃል፡፡ ሀገር የመለወጥ አላማ፡፡ ሀገር ለመለወጥ የተነሳሳ በዚያው አላማ ዙርያ መሸ ጠባ ሊተጋ ይገባል፡፡ ይህን በመሰለ አላማ ዙርያ የማይሰራ ያን ማሳካት የሚችሉ ጥቅል ፍልስፍናዎች ከዚያ የሚቀዱ የረጅም ግዜ የመካከለኛና የአጭር ግዜ እቅዶች ነድፎ በነዚያ ዙርያ ህዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው የማይተጋ ፓርቲ የሚቀረው መንጠልጠያ ትችት ብቻ ነው፡፡ ትችት ጌጡ ሆኖ የሚያርፈው እንዲህ አይነት ትልም የሌለው ፓርቲ ነው፡፡


ይሄን መሰሉ የፓርቲ ቁመና የጠራ አላማ እና ከአላማ ለአፍታም ቢሆን አይንን አለመንቀል ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ባለ ትኩረት የሚሰራ ቡድን በርካታ የሚያቅዳቸው የሚያነሳ የሚጥላቸው ጉዳዩች ስለሚኖሩት ስለራሱ በማውራት የራሱን ፕሮግራም በማነጻጸር ይጠመዳል፡፡ የሌሎቹን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አማራጮች አዋጭ አለመሆን የሚያነሳው አማራጩን ሲያስተጋባ በማሳያነት ወይም በማነጻጸሪያነት ሲያነሳው እንጂ ነጋ ጠባ ስለባላንጣው ሲያወራ የሚከርምበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡


ስለ ባላንጣቸው በማውራት የሚጠመዱ ፓርቲዎች ዋነኛ ችግር ስለባላንጣቸው ያላቸው የከፋ ጥላቻ አደለም፡፡ ትልቁ ችግር ለሀገራቸው የሚያቀርቡት አማራጭ ራእይ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ አጀንዳ ያለው ቡድን ስለሌሎች ለማውራት ግዜ አይኖረውም፡፡ በሚያገኛት የተወሰነች የሚዲያ አጋጣሚ የፓርቲዉን መልእክት በማስተላለፍ ስራ ላይ ብቻ ይጠመዳል፡፡ በተቃራኒው ላይ የሚያተኩር ቡድን ውድቀት እንደ ፓርቲ የሚታገልበት ጥርት ያለ አላማ እና የተተነተነ እቅድ አለመኖር ነው፡፡

እንዲህ ባለ ተደጋጋሚ ትችት እንኳ አላማ ቢቀርጽ ደግሞ ጥቅል ፓለቲካዊ ፍልስፍናው የአፈጻጸም ስትራቴጂው እና ታክቲኮቹ የማይመጋገቡ ሆነው ነው የሚገኙት፡፡ ይሄ ይሄ ነው እንግዲህ ለፓርቲዎች ያላቻ ጋብቻ መነሻ እየሆነም ያለው፡፡ ይሄ ይሄ ነው እንግዲህ ማንም ብድግ ብሎ ፓርቲ እንዲያቋቁም መነሻ እየሆነ ያለው ምክንያቱም በኛ ሁኔታ ፊርማ ማሟላት እና መናገር ብቻ ፓርቲ እንደሚያደርግ ከቋሚዎቹ ፓርቲዎች አብነት ወስደዋልና፡፡ ለዚህ ነው ወደ 90 ገዳማ ፓርቲ ሊኖረን የቻለው፡፡


የለውጥ ቃልኪዳን ተቀናቃኛችን ማሳካት ያልቻለውን ጉዳይ የሚያሳካ ትልም ሲኖረው በርግጥም መገመት እና ማሳመን የሚችል ፕሮግራም ሲኖር በዚያ ቃልኪዳን ዙርያ ሕዝብን ማሰባሰብ የሚያስችለው አቅም ይኖረዋል፡፡፡ ብቁ አማራጭ ከመያዝ በኋላ የሚለጥቀው ደግሞ ያን አላማ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማስተዋወቅ ህዝቡ እንዲረዳው እንዲገዛው እንዲደግፈው ማድረግ ነው፡፡ የተሳካ ቃልኪዳን የማሻሻጥ ብቃት እና የተግባር እንቅስቃሴ ለጥቆ የሚመጣው ጉዳይ ነው፡፡


ለማንኛውም ፓርቲ መነሻው ባላንጣው ሊሆን አይችልም፡፡ መነሻ ሁሌም ውስጣዊ አላማ እና ተጨባጭ ሀገራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ የአንድ ፓርቲ ዋነኛ ጠላትም ሀገራዊ ችግሮቹ እንጂ በተፎካካሪነት የቀረበ ፓርቲ አደለም፡፡ በተፎካካሪነት የቀረበው ፓርቲ ከተመሳሳይ ሀገራዊ ችግሮች የተነሳ በተመሳሳይ የዜግነት ቁጭት ሀገር እለውጣለሁ በሚል እምነት ወደ ፖለቲካው የገባ ነው፡፡ ልዩነቱ ችግሮቹን የሚያነብበትና ለነዚያው ሀገራዊ ችግሮች የሚያቀርባቸው መፍትሄዎች ላይ ነው፡፡


አንዳንዱ ልዩነት ከፖለቲካ ርዕዩትአለም የሚመነጭ ሌላው ደግሞ ችግሮቹን ከምናይባቸው አተያዩች የሚነሳ ይሆናል፡፡ የሆነ  ሆኖ ቁምነገሩ ችግሮቹን በቅጡ መረዳት መነሻዎቻቸውን በአግባቡ መለየት የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች የሚያጠነጥኑባቸውን  ጥቂት ግን ወሳኝ ጉዳዩች በመለየት ለነሱ የምናቀርበው ሁነኛ መፍትሄ ጥቅል ሀገራዊ ችግሮቻችንን እንዴት እንደሚንዳቸው በቅጡ መገንዘቡ ነው፡፡


ይህን በማብራራት ረገድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሰሯቸውን የሁኔታ ግምገማም የርዕዩተአለም ዝንፈትም ሌላም መነሻ እያመላከትን ካሉት ፓርቲዎች በተሻለ ሀገራዊ ጉዳዩችን መረዳት እና መፍትሄ ማቅረብ እንደቻልን ለመራጩ ህዝብ ማሳየት መቻል ነው፡፡ ይሄ በሆነበት ተቃራኒው ፓርቲ ምንም ይሁን ምን በጉዳዩች ዙርያ በቂ ዝግጅት ያደረገ ፓርቲና ያንን ያለማሰለስ ለህዝቡ ያሻሻጠ ፓርቲ አሸናፊ መሆኑ አይቀርም፡፡


በመሆኑም ቁምነገሩ ስለባላንጣ በማሰብ ግዜ መግደል አደለም፡፡ እንደ አማራጭ ፓርቲ ለሀገር ልናደርገው የምንፈልገውን ነገር የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ሊፈታ በሚችል መልኩ ቀምረን አስተዋውቀን በዚያ ቃልኪዳን ዙርያ መተማመን ፈጥረን የህዝብን ድምጽ መግዛት መቻል ነው፡፡


ይህ ነው ለህዝብ የሚቀርበው የፓርቲ ፖለቲካዊ ቃልኪዳን ቁመና፡፡ እንጂ ተፎካካሪ ፓርቲን ሲያጣጥሉ በመዋል በዚያ ብቃት ሀገር የመምራት ሀላፊነት ለመረከብ መሞከር ህዝብንና ሀገርን መናቅ ነው፡፡ ፓለቲካዊ ስራን በወጉ ካለመረዳት ፉክክሩ በዋናነት ሀገር ከገጠማት መሰረታዊ ችግር ጋር እንጂ ከአማራጭ ፓርቲዎች ጋር አለመሆኑን አለማወቅ ነው፡፡


የፖለቲካ ሀላፊነት እንደ ሀብት መፍጠርያ ቃልኪዳን
መሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ በወጉ የተከበሩለት ማህበረሰብ ሊሰጠው የሚገባ ዋና ቃልኪዳን ሀብት መፍጠር የሚያስችል ፕሮግራም የሚያስተዋውቅ ቃልኪዳን ነው፡፡ ምንም ያክል ዜጋ መብቱ ይከበርለት ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቱቹ ለአደጋ የሚጋለጡ ከሆነ ቆየም ፈጠነም ለአመጽ መነሳሳቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው በአውሮፓ ከሚታየው ወቅታዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተያይዞ ህዝቡ በተለያዩ ግዜያት ሰልፍ በመውጣት አልፎ አልፎም ነውጥ በመፍጠር ቅሬታውን ሲገልጥ የነበረው፡፡


ይሄ እንግዲህ መብት ብቻውን ፋይዳ አልባ ስለመሆኑ ያመላክታል፡፡ የመብት ዋናው ጥቅሙ ሀብት መፍጠር ማስቻሉ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ ይሄን ማሳካት ባልተቻለበት ምንያክል ዴሞክራሲ ይኑር ህዝብ ሀብት መፍጥር እንደሚችል ተስፋ በማያደርግበት ስርአት በዝምታ ሊኖር አይችልም፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ነጻነት ማጠንጠኛው ዞሮ ዞሮ ኢኮኖሚያዊ ነጻነት እና ተጠቃሚነት ነው የሚባለው ለዚሁ ነው፡፡


ስለሆነም የፓርቲዎች አብይ ጉዳይ እዚህም እዚያም ለትችት የሚሆን ኮስማና የመብት ጥያቄዎች ላይ መንጠልጠል ሳይሆን ለዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ማበብ በራሱ ትልቅ ሚና የሚጫወተውን የኢኮኖሚ ነጻነት ለማረጋገጥ መትጋት መሆን ይገባወዋል፡፡
በኛ ሀገር ከኢኮኖሚ አንጻር ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተካኑበት ቃልኪዳን ቢኖር ያው የተመዘገበውን እና ለወትሮው እድገቱን የሚጠራጠሩት አለማቀፍ ተቋማት እንኳ ሳይቀር ያመኑትን አመታዊ የእድገት ምጣኔና ልማት መካድ ነው፡፡ የቁጥር ጨዋታ ነው፡፡ ውሸት ነው፡፡ ኢህአዴግ በቁጥር መጫወት ይወዳል የሚሉት መዝሙሮች ናቸው የተቃዋሚዎቹ አማራጭ ቃልኪዳኖች፡፡


አላማው ሀገር የሚጠቀምበት አግባብ መፍጥር ከመሆኑ አንጻር ሲመዘን የተመዘገበን እድገት መካድን ምን ይሉታል፡፡ የሆነውን ተቀብሎ ሲያበቃ የዚያ ፓርቲ አማራጭ ከዚህ የመሪነት ሚናውን ከያዘውም ፓርቲ የተሻለ የሚሆንበትን እድል ማሳየት አይሻልም ነበር፡፡ የሰለጠነ ተፎካካሪ ፓርቲ ባህርይም ያ ነበር መሆን የነበረበት፡፡ በኛ ሁኔታ ተቃዋሚዎቹ የሚያቀርቡት አማራጭ የኢኮኖሚ ቃልኪዳን ኢህአዴግ አሳካሁት የሚለውን እና አስገኘሁት የሚለውን ለውጥ ማጣጣል ነው ፡፡


ይሄ እየሆነ ያለው በኔ እምነት ፓርቲዎች መነሻ ቃልኪዳናቸው እና ሁነኛ አላማቸው ወቀሳን መጥመቅ በመሆኑ ነው፡፡ ወቀሳ ጠማቂዎች ከገንቧቸው ቀድተው ለህዝቡ ሊያቀርቡለት የሚችሉትም ጠላ ከሰየሙት ገንቦ ባህሪ የሚለይ ሊሆን አይችልም፡፡ ወቀሳ ጠማቂዎቹ ወቀሳን ከማስጎንጨት ያለፈ ለህዝብ ሊያቀርቡ የሚችሉት ተጨባጭና ተገማች አማራጭ እስካሁን ማቅረብ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ይሄ ጎራ ሁለት የቤት ስራ ይኖረዋል፡፡


አንደኛ የፖለቲካ ጉዳይ መጥመቂያ ገንቧቸውን ለወቀሳ መጥመቂያነት ከማዋል ወደ ሀገራዊ ጉዳዩች መፍትሄ መፈተቻነት ቢያዘዋውሩት፡፡ ሲለጥቅ ደግሞ እነዚህ ሀገራዊ ጉዳዩች በስርአት ሀገራዊ ችግሮችን በመረዳት ለነዚያ ሀገራዊ ችግሮች መፍቻነት የሚውሉ ርእየተአለማዊና አለማቀፋዊ ልምዶችንና አሰራሮችን ከግምት አስገብተው በወጉ ተሰናድተው እንዲቀርቡ፡፡


ሁለተኛ ፓርቲዎቹ ሰፊ ሜዳም ሲገኝ ይሁን ጠቧል በሚሉት ሜዳ ሊያተኩሩበት የሚገባቸው የንግግር እና የውይይት አጀንዳቸው ይኸው ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሌም በመልእክታቸው ዙርያ አተኩረው ይበልጥ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው በሚችል የራሳቸው አማራጮች ዙርያ መልእክቶቻቸውን እስካልቀመሩ ድረስ ሲያወሩ መስማታችን ባይቀርም ሳንገዛቸው እነሱም ሳይሸጡ የሚመኙትን የፖለቲካ ስልጣን ሁሌም ህዝቡ እንደነፈጋቸው ይዘልቃሉ፡፡


ለመነፈጋቸው መነሻው ግን ራሳቸው ናቸው፡፡ ሕዝብ የሚያጓጓ ሀገራዊ መፍትሄ በማቅረብ ጥሩ ተወዳዳሪ አለመሆናቸው ነው ሁሌ የምርጫ ተሳታፊ ከመሆን በዘለለ አሸናፊ ሳይሆኑ እንዲቀሩ የሚያስገድዳቸው፡፡ ድምጽ ባገኙባቸውም አጋጣሚዎች እንኳ ህዝቡ ድምጽ ሲሰጣቸው አማራጭ አግኝቶና አማራጫቸው አርክቶት ሳይሆን ኢህአዴግ ሊሰራ ሲገባው ባላሳካቸው ጉዳዮች በመበሳጨት የቸራቸው ነው፡፡


ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን በዚህ ደረጃ ወቀሳ ጠማቂ በመሆን ሳጣ ቆየኝ ሆነው መኖር አለባቸው፡፡ ህዝብ አማራጭ አላገኘም አንዱን ብቁ ፓርቲ ግን ከነእጥረቶቹ ከምርጫ ወደ ምርጫ ሀላፊነት እየሰጠ እያስቀጠለው ነው፡፡ አማራጭ መሆን አማራጭ እሆናለሁ ብሎ የተነሳ ቡድን የቤት ስራ ስለሆነና ብቁ ተፎካካሪ ለፖለቲካችን መዳበር ወሳኝ በመሆኑ ብቁ አማራጭ የሚሆን ፓርቲ እንፈልጋለን፡፡ ያን ለማሳካት ደግሞ ከመነሻው ወቀሳ ጠማቂ አለመሆን ነው ቁምነገሩ፡፡   


ዛሬ ባይኖሩም በሂደት የቤት ስራቸውን በአግባቡ የጨረሱ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚኖሩን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይቆየን፡፡
 

No comments:

Post a Comment