Tuesday, October 8, 2013

አዋጭ ፖለቲካዊ ባህርያት



  • ጎደለ ወይስ ሞላ
ፖለቲካ በአማራጮች ሲዋጅ እስከ ግማሽ ጎዶሎ ነውን በእስከ ግማሽ ሙሉ ነው ይተካል፡፡ ይሄ የአባባል ለውጥ አደለም፡፡ የአጀንዳ ለውጥ ነው፡፡ ሊሞላ ሊጨምር እና ሊያሳካ የሚመኘው ያንንም ለማሳካት የቀረጸው ፕሮግራም ያለው በመሆኑ ስለጎደለው ሳይሆን እንደሚሞላ ስለሚተማመንበት እና ዝግጅት ስላደረገበት ጉዳይ በማንሳት ይጠመዳል፡፡
በራስ መተማመኑ የሚመነጨው በባላንጣው ጉድለቶች ላይ ሳይሆን በራሱ ጥንካሬዎች ላይ በመሆኑ ስለጎደለው ሳይሆን የቀረው ስለሚሞላበት አግባብ እና ያን ለመሙላት ስላደረገው ዝግጅት በማስረዳት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡

ስለሚሞላው ነገር ምንነት ስለጉድለቱ መነሻዎች እና ሊሞሉት ስለሚችሉ ቁሳቁሶች ምንነት ያን እንዴት እንደሚያፈላልግ እና እንደሚያሟላ ስትራቴጂክ ትልሞቹን እየነገረ ስለሚሞላው ነገር በአባላቱ በደጋፊዎቹና በጥቅል ማህበረሱ ላይ እምነት እየፈጠረ ይሄዳል፡፡

ለእንደዚህ አይነት ፓርቲዎች ጉድለት መንጠላጠያ የትችት ማዝነቢያ ሰንሰለት ሳይሆን በአማራጭ ፓርቲነት የቀረበው ቡድን መፍትሄ የሚፈልግለት ተጨባጭ መመዘኛው መሆኑን አይስትም፡፡ ለዚህ ተጨባጭ ክፍተትም መፍትሄ በመፈለግ ድርጅታዊ ብቃቱን ለጉድለቶች መሙያ የሚሆኑ መፍትሄዎችን እና መላዎችን ማቅረብ እንደሚችል ያረጋግጣል፡፡
ይሄ ድርጅታዊ የመሙላት አቅም እና ዝግጁነት ነው አንድን ፓርቲ አማራጭም ተመራጭም ሊያደርገው የሚችለው፡፡ 

በመሆኑም ኢህአዴግ መሙላት ስላልቻለ እና ጎዶሎ ስላለበት ምረጡኝ ከማለት ወደ የመፍትሄው ባለቤት ነኝ ላልተሞሉት ችግሮች መፍትሄ ያበጀሁላቸው በዚህ አግባብ ነው ጉድለቶቹም የተፈጠሩት በነዚህ መነሻዎች መሆኑን ለይቻለሁ ሊሞሉ የሚችሉትም በዚህ አግባብ ስለመሆኑ ይህን የመሳሰሉ መረጃዎች አሉ በሚል ይቀርባል፡፡

ያኔ ስለጎደለ ልምረጥ ማለት ይቀርና የመሙያውን ቁልፍ የያዝኩት እኔ ስለሆንኩኝ ምረጡኝ ወደሚል በሁለት እግሩ የቆመ አማራጭ ይወስደናል፡፡ በመሆኑም አማራጭ ፓርቲዎች ጉድለቶችን መፍትሄ የማፈላለጊያ አማራጭ የመጠቆሚያ ተጨባጭ መነሻዎች እንጂ የወቀሳ መንጠላጠያ አያደርጓቸውም፡፡

እግረ መንገድ ግን እንዴት ሙሌቱን እንደሚፈጥሩ ሲያመላክቱ ገዢው ፓርቲ ቀዳዳዎቹን እንዴት እንደፈጠረ ወይም ሊለያቸው እንዳልቻለ ከየትኛዎቹ ፕሮግራሞቹ ወይም ፖለቲካ ፍልስፍናዎቹ እንደሚመነጩ ከፓርቲው ፍልስፍና እንኳ የማይመነጩ ከሆኑ ደግሞ እንዴትና ለምን ጉድለቶቹን ሊሞሏቸው እንዳልቻለ በመጠቆም ከገዢውም ከሌሎቹም ፓርቲዎች ለምን የተሻለ አማራጭ እንደሆኑ ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡

ዋናው ነገር ግን መፍትሄ ማበጀት መቻላቸው እና ሙላት የሚሆኑ ሀሳቦች አሰራሮች እና ፕሮግራሞች ያሉዋቸው መሆናቸውን ማስተዋወቅ በመሆኑ በራሳቸው ጥንካሬና ፕሮግራም ዙርያ አተኩረው የጎደለውን የሚሞሉ እንጂ በጎደለው ሰበብ የስልጣን ርካቡን የሚንጠላጠሉ አለመሆናቸውን ማስረገጣቸው ነው፡፡

ስለጉድለት አውስተው የሚወዳደሩ ሳይሆኑ በሚሞላው መፍትሄ መሆን በሚችለው ተወዳዳሪ ፖሊሲዎች ፕሮገራሞች እና አደረጃጀታቸው ተጫርተው በተሟላ የህዝብ እምነት ለመፍትሄው ወደስልጣን የሚመጡ መሆናቸው ነው፡፡
ይህን ለመሰሉ ፓርቲዎች ጥማታቸው ወንበር አደለም፡፡ ጥማቸው ሀገራዊ መፍትሄ መበጀቱ ነው፡፡ በዚህ ሂደት መፍትሄውን ማበጀት የሚችል ቡድን በህዝብ ሀላፊነት እስከተሰጠው ድረስ የስልጣን ጥማቸው ሆዳቸውን በልቷቸው ለነሱ መሰልጠን ሲባል ሰላማዊው ሂደት እንዳይደፈርስ በጽናት የሚቆሙ ናቸው፡፡ ውድድሩን ፖለቲካዊ ምህዳሩን የሚመዝኑት በውድድሩ አሸናፊ በመሆናቸው ሳይሆን ውድድሩ ዴሞክራሲያዊ  እሴቶችን ሊያንጽ በሚችል አግባብ እየተመራ ነው ወይስ አደለም በሚል ሚዛን ይሆናል፡፡

መሞላቱ ነው ቁምነገሩ፡፡ መፍትሄው ነው ዋናው ነገር፡፡ መፍትሄው እየተቀመረ እስከሄድ ድረስ ፖለቲካዊ ስልጣን መያዝ አለመያዝ የፖለቲካ ተሳትፏቸው መመዘኛ አደለም፡፡ ተሳትፏቸውን ማስገኘት በቻለው ጥቅል ፖለቲካዊ ጥቅምና እሴት ግንባታ እንጂ በታገሉለት ወይም በሚታገሉበት ፓርቲ ስልጣን ቆይታ ወይም መያዝ አደለም ማለት ነው፡፡


ይሄ ግን መሙላት ዋናው አጀንዳው የሆነ ፓርቲ ሲኖረን የሚከሰት ነው፡፡ በጉድለት ላይ መንጠልጠል ሳይሆን የጎደለን መሙላት ሚናቸው እንደሆነ የገባቸው እና በዚያው አግባብ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ያሉን እንደሆነ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment