Tuesday, September 3, 2013

ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል- ክፍል አንድ


ባለፈው ግዜ ከነጃወር የተንሸዋረረ የማንነት እና የዜግነት ጥያቄ በመነሳት እቺ አገር ያለችበትን ሁኔታ የሚዳስስ ጽሁፍ ለማቅረብ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ በዚያው መሰረት ሀገራችን ሳትገነጣጠል ልትቆይ የሚያስችላትን አማራጭ በኔ እይታ አቅርቤዋለሁ፡ እንምከርበት እንሟገት፡፡

እንደ መግቢያ
በጥሬው ኢትዮጵያ እንዳትገነጣጠል ማሰብና በአንድነት አጽንቶ በእድገት አልቆ ሊያስቀጥል የሚችል ስርአትና አመራር መፍጠር የተለያዩ ናቸው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የሚመርጠው መሆኑ አነጋጋሪ አደለም፡፡ አንድነት ተጠብቆ ሊዘልቅ የሚችልበትን አማራጭ በመምረጥ ረገድ ግን ልዩነቶች ይስተዋላሉ፡፡


በወሳኝነት በፖለቲካው መድረክ ከዚህ አኳያ የሚፋለሙት አስተሳሰቦች ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ ኢህአዴግ ያቀረበው ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል አማራጭ ሲሆን ሌላኛው የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀነቅኑት በብሄር ሳይሆን በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እንዲተዳደሩ የሚለው አማራጭ ነው፡፡ ይህ አማራጭ ከክልሎቹ መዋቅር እስከ ፌደራል መንግስት መዋቅር ባህርያት ድረስ ቁርጥ ያሉ አማራጮች ያበጀ አይመስልም፡፡ በግርድፉ የሚያቀርበውን ሀሳብ ግን እንየው፡፡


ጂኦግራፊያዊ የፌደራል ስርአት አማራጭ
እንደ ኢዴፓ ያሉ ይህን አማራጭ የሚያቀርቡ ፓርቲዎች ህዝብ ብሄራዊ ማንነቱ ከግምት ሳይገባ እንደ አቀማመጡ አመቺነት ወሎ ጎጃም ሲዳማ ሀረርጌ አይነት ብለን  እንደ አመቺነቱ እናስተዳድር የሚል አማራጭ አይነት ነው የሚያቀርቡት፡፡ አማራጩ በርግጥ ጥርት ባለ መልኩ ተብራርቶ ባይቀርብም እነ ልደቱን ከመሳሰሉ ፓለቲከኞች ከሰማሁት ገለጻ ተነስቼ ስናገር በጂኦግራፊ ተከፍሎ ሲያበቃ የብሄሮችን በገዛ ቋንቋቸው የመጠቀም መብት ግን ያከበራል ይላሉ፡፡


በተጨማሪም የመሪዎች ምርጫ በህዝቡ የሚካሄድ ስለሚሆን በጂኦግራፊ መከፈሉ ችግር አያመጣም ይላሉ፡፡ ይሁንና ይህ አይነቱ ውሳኔ እንደ ኦሮምያ ሶማሊያና አፋር ለመሳሰሉ በርካታ ሌሎች ብሄሮች አርኪ መልስ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ጥያቄ ዋናው የማንነት እና የእኩልነት ጥያቄ ነውና፡፡ ይህ አማራጭ አጀንዳውን ተራ የፌደራል ስርአት የመመስረት እንጂ ከማንነት ራስን ከማስተዳደርና ከእኩልነት አንጻር ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር በማስተሳሰር ያጤነው አይመስልም፡፡


እንዲያውም ይህ አይነቱ አተያይ በጠባብ ከባቢያዊ አስተሳሰብ ድጋፍ ለሚሰበስቡ ፓለቲከኞች የሚያበረታታ አጀንዳ የሚፈጥርላቸው ይመስላል፡፡ የመገንጠል አጀንዳ የሚያቀነቅኑትም ዛሬም ቢሆን ራስህን ማስተዳደር ያልተፈቀደለህ ስለማትታመን ነው ዛሬም መብትህ አልተከበረም በሚል ዝማሬ ለማነሳሳት ይጠቀሙበታል፡፡ በጣም ቢዳከሙም ዛሬም መሰል የመገንጠል አስተሳሰቦች የራስ አስተዳደር በተከበረበትም ሲራመዱ የምንታዘበው ይህን የህዝቡን ፍላጎት ጠምዞ ለአጀንዳቸው ለማዋል ታስቦ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡



እንደ ህዝብ አትታመንም አንድ ላይ እንደ ብሄር መሰባሰብህ አደጋ ነው ብለው የሚያምኑ ጨቋኝ ሀይሎች በመኖራቸው ዛሬም በድንበር በጣጥሰው ነው የሚነግዱብህ የሚል ሙግት ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ይህን መሰሉን ሙግት አማራጩ መሻገር የሚያስችለው አቅም ያለው አይመስለኝም፡፡


ለዚህ አማራጭ ሊቀርብ የሚገባው እማይታለፍ ሙግት ህዝቦች አንድነታቸው የሚጣሰው እና የሚመሰረተው በመሬት አከፋፈልና አቀማመጥ ነው ወይስ አንድነት በሚያስገኘው ተገማች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ነው የሚለው ይሆናል፡፡
የሆነ ሆኖ ይሄ አመራጭ በተለይ በብሄሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ለመዳኘት ከፍተኛ የአመኔታ ችግር እንደሚገጥመው ይህ የማይጥማቸው ተቃዋሚዎችም ሰፊ ዘመቻ የሚከፍቱበት የሚንገዳገድ አቋም እንደሆነ አምናለሁ፡፡


በኔ እምነት ይህን አማራጭ የሚያቀርቡት ቡድኖች ይህን የሚሉት አንደኛ በየብሄሩ መተዳደር የመገንጠል ፍላጎቱን የማበረታታት በህዝቦች መካከል አለመተማመንና ገጭቶችን የመፍጠር ድክመት አለበት በሚል እምነት እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በአብነትም በተለያየ ግዜ የሚታዩ ግጭቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች የሚደርስባቸውን የቋንቋና ሌሎች ተጽእኖዎችን ሌላ የጭቆናና የመገንጠል ጥያቄ የሚያነስነሱ አብነቶች እንጂ ለብሄሮች መብት መከበር የቆመ መፍትሄ አደለም የሚል ክስ ያቀርባሉ፡፡


ክሱ በጣም ትንሽ እውነት አለው፡፡ ማለትም በሌሎች ክልሎች ያሉ አማርኛ ተናጋሪዎች (ብሄራቸው ድብልቅ ነው) ያለምርጫቸው ቋንቋ ተጭኖባቸዋል የሚለው አሳማኝነት ነው፡፡ ይህም ግን በሁሉም ክልል ያለውን ሁኔታ አይገልጽም እዚያውም ሳለ ያ መሆኑ ሌላ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን በተለያዩ ክልሎች በተለይም በከተሞች የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች በክልሎቹ ቋንቋ መማራቸው በክልሎቹ በሚኖሩ የስራ እድል ለመጠቀም የሚያስችል ከመሆኑ አንጻር ሲመዘን ሌሎች ብሄሮች በፌደራል ደረጃ ለሚኖሩ ስራዎች አማራኛን መልመድ ያለባቸውን ያክል በሚኖሩባቸው ክልሎች የሚኖሩ የስራ እድሎችን ለመጠቀም አማርኛ ተናጋሪዎችም ክልላዊ የስራ ቋንቋዎችን መልመዳቸው የሚስችላቸው ከመሆኑ አኳያ ከተመዘነ ጠቀሜታው ጎልቶ ይወጣል፡፡


በሌላ ገጹ ደግሞ ክልላዊ ቋንቋዎችን አማርኛ ተናጋሪው ወይም ሌላ ቋንቋ የሚናገር ማንኛውም ዜጋ ለመልመድ የሚኖርበት የቤት ስራ ለፌደራል ስራችን አማራኛን መልመድ ወይም ለአለማቀፍ ግንኙነታችን እንግሊዘኛን ለመልመድ አንድ ግለሰብ ከሚኖርበት ጫና የተለየ ባለመሆኑ በተጋነነ እና በተጣመመ መልኩ እየቀረበ ለጉንጭ አልፋ ተራ የፖለቲካ ጉንተላ ማካሄጃነት መዋል የለበትም የሚል አቋም አለኝ፡፡


እናም ችግሮቹን በወጉ ሳያጤኑ በወሳኝነት በሁሉም ክልሎች መፍትሄ የሆነን እና ሳይንሳዊ አቀራረብ የተከተለን የቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ የተቃውሞ አጀንዳ ስር እያካተቱ ህገመንግስታዊ ድንጋጌውን ስህተት አድርጎ ለማቅረብ መጣደፍ ተገቢ አደለም፡፡ ይልቅ በብሄራዊ ማንነቱ ምክንያት በሚኖሩ የስራ እድሎች ላይ ማዳላት እንዳይፈጸም ከደም በመነሳት በተለያዩ ክልሎች በሚኖሩ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ማዳላት እንዳይፈጸም ነው መታገል፡፡ ሲፈጽምም ያንን የመሰለውን አድሏዊ አሰራር ለመናድ ነው መትጋት፡፡


ከዚህ አለፍ ባለ ገጽታውም ሁኔታውን ካጤን በቅርብ በማውቃቸው ደቡብ ክልል እና አማራ ክልል የሚታየው በክልሎቹ ያሉ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን የማስተናገድ ዝንባሌ በአብነት ሊጠቀስ የሚገባውና ሌሎቹም ክልሎች ሊቀስሙት የሚችሉት ልምድና አሰራር ነው፡፡ አማራ ክልል ከአማራኛ በተጨማሪ የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ባሉበት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እንዲዳኙና እንዲሰሩ ማድረጉ ደቡብ ክልልም ከክልል የስራ ቋንቋነት ጀምሮ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በየአካባቢው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በአማርኛም የመማር የመዳኘት እና የመስራት እድል መፍጠሩ ክልሉን ለሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያነት አመቺ አድርጎታል፡፡


ይህ የደቡብ እና አማራ ክልል ያለው ልምድ በሁሉም ክልል ቢለመድ ደግሞ የላቀ ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠትና የሁሉንም ብሄሮች ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በክልሎቹ ያለውን ሰፊ የስራ እድል ለመጠቀም ግን የክልሎቹን ቋንቋ መልመድ ወሳኝ መሆኑ ሳይረሳ ማለት ነው፡፡


በዚህ መልኩ እየተፈጸመ ያለ የፌደራል ስርአት በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ መስፈርት ቢመዘን በተጨባጭ ሊነሳ ከሚችል ማንኛውም እጠረት ጋርም ቢሆን እጅግ ለሚልቀው ኢትዩጵያዊ የተሳካ ስርአት እና ጥቅም አስገኝቷል፡፡ በመሆኑም ብሄሮች በቁንጮነት የሚጠቀሰውን ራስን የማስተዳደር መብት መጎናጸፋቸውና በብሄራዊ አስተዳደራቸው ቋንቋቸውን መጠቀማቸው ለበለጠ ብሄራዊ እርካታ የሚዳርጋቸው እና ኢትዮጵያዊነታቸውን የበለጠ እየወደዱ የሚሄዱበት እንጂ ለመገንጠል የሚያመች ለም መሬት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ በተግባርም የሆነው እንደዛ አደለም፡፡


ይሄ አስተሳሰብ እንደውም ሀገራችን አንድ ሆና የቆየችው አንድ ብሄር በአንድ የአስተዳደር ወሰን እንዳይኖር በማድረግ አንድነቱ እንዳይጠናከር ስለተደረገ አስመስሎ የሚያቀርብ አተያይ ነው፡፡ ለመሆኑ ሀገራዊ አንድነታችን ክልላዊ ወሰኖች የገመዱት ውህደት እንጂ ያስተሳሰረን ግዙፍ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ የጋራ እሴት የሌለው ነው ማለት ነው; ወይስ አንድነቱን በገዛ ፈቃዳቸው ተቀብለው እንደማይኖሩ የምንጠራጠራቸው ብሄሮች አሉ;


ይሄ አስተሳሰብና አማራጭ ሀገረሩን እና ዜግነቱን ተቀብሎ የሚኖረውን ዜጋ ሕሊናዊ ምርጫ የሚያራክስ አቀራረብ ነው፡፡ ዜጎች መሬት ላይ የተሰመረ ክልላዊ ወሰን በአንድነታቸው እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል ብሎ ማሰብ ሰውን ከመሬት አሳንሶ ከማቅረብ የሚመነጭ ነው፡፡ ሌላ ምንም መገለጫ ልንቸረው አንችልም፡፡ ይሄ ካልሆነ በቀር በዜጎች ሕሊናዊ ፍላጎት እና ምርጫ የሚወሰንን ጉዳይ ከጂኦግራፊያዊ ቅጥር አሰማመር ጋር አሰናስሎ ማቅረብ ባልተቻለም ነበር፡፡


ራስን በራስ ማስረዳደር እስከ መገንጠል…
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል በተባበሩት መንግስታት ህጎች እውቅና የተስጠው መብት በመሆኑ በአስራርና በፍልስፍና ደረጃ ችግር የለበትም፡፡ ተመድ ስላለው ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ብሄር/ህዝብ ራሱን የመምራትና የማስተዳደር ሙሉ ተፈጥሯዊ አቅምና ነጻ መብት ስላለው ይህን መብት ማክበር ለግጭቶች መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ልዩነቶችን የማድረቅ ሁነኛ መላ ስለሆነ ሲልም በተለያዩ ምክንያቶች አብረው መቀጠል የሚችሉበት እድል የመነመነና የሚያጠፋፋ እስከመሆን ከደረሰ በሰላም መለያየትን መምረጥ ስልጡንነት በመሆኑ ነው፡፡


እነዚህ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩት ክልሎች ግን በህገመንግስቱ እንዳስቀመጡት አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ በኢትየጵያ አንድነት ዙርያ ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ባህላዊና የላቀ ጠቀሜታ ያለው አማራጭ እንዳላቸው ከህገመንግስቱ መግቢያ ጀምረው ደንግገዋል፡፡


በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጠውንና በሀገሪቱ በአሁኑ ግዜ እየከሰመ ያለ ግን በስፋት ሲራመድ የነበረን የመገንጠል ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መንፈግ ወይም በህገመንግስታዊ ድንጋጌው አለማወቅ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ትልቁ ነገር የመገንጠል ጥያቄ በሚቀነቀንበት አገር በመብትነቱ የህገመንግስት እውቅና ሰጥተን ስናበቃ አንድነትም ዜጎች እውቅና የሰጡት ህዝባዊ ፖለቲካዊ ጥያቄና ህገመንግስታዊ ድጋፍ ያለው ሀቅ በመሆኑ ተጠብቆ እንዲኖር መትጋት ነው፡፡


ይህን ያክል ለአንድነቱ ቀናዒ የሆነ ዜጋ ያለን መሆኑ ደስ የሚያሰኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነት ግን አለማቀፋዊ እውቅና የተሰጣቸውን አለማቀፋዊ መብቶች በመካድ የሚጠበቅ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው፡፡ በሌላም በኩል ይሄን መብት ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ ያለብን አዋጭ አደለም የምንለውንና በመጨረሻ አማራጭነት ሕዝብ ሊጠቀመው የሚችልን ከነጻ ፍላጎት የሚመነጭ አማራጭ መብት በማፈን ሳይሆን በመብትነቱ ተቀብለን እና ህገመንግስታዊ እውቅና ሰጥተነው ስናበቃ አንድነት በተሻለ አማራጭነቱ ተወዳድሮ እንዲያሸንፍ በማድረግ መሆን ይኖርበታል፡፡


ደምቆ በህገመንግስቱ እንደ ተብራራው የኢትየጵያ ብሄር በሄረሰቦች አንድነታቸውን ለማስቀጠል የሚያበቃ የጋራ ታሪክ የምንጋራው ባህልና አብሮ የመቀጠል ፍላጎት ስላለን በአንድነታችን የምንቀጥል ሆኖ አንድነታችንን የምንመርጠውና የመረጥነው ግን መገንጠል መብት ሆኖ ሳለ ከአንድነት በእጅጉ የሚያንስ አማራጭ በመሆኑ ነው፡፡ አንድነትን የምንመርጠው መገንጠልን ስለምንጸየፍ ወይም ስለምንፈራ ሳይሆን አንድ ሆነን በመቀጠል የምናሳካቸው ግዙፍ ጥቅሞች ስላሉና ስለሚፈጠሩም ጭምር ነው፡፡


የመልማት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብር መንግስታዊ ስርአት መመስረት የግድ መገንጠልን ስለማይጠይቅና የህዝቡም ፍላጎት አሁን ባለንበት ሁኔታ አንድነቱን ጠብቆ የሚመኘውን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሂደት መገንባት በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም አንድነትም መገንጠልም በህገመንግስቱ ታውቀው ሲያበቁ አማራጩ ለሀገራችን ህዝቦች ቀርቦ አንድነት በአማራጭነት ማሸነፍ የሚሳነው ይመስል በዚህ ደረጃ መገንጠል ሕገመንግስታዊ እውቅና ስለተሰጠው ብቻ መብከንከን አግራሞት ይፈጥራል፡፡

በአንድ በኩል የሀገራችን ህዝቦች የሚመርጡትና ለዘመናት እውቅና የሰጡት ለአንድነት ነው የሚል ክርክር በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ አገር ሊገነጣጠል ነው ብሎ መስጋት የሚጋጭ ነው፡፡ ሕዝቡ ለአንድነቱ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጠው የሚረዳ ዜጋ አንድነትን ለመጠበቅ እና የአንድነትን አዋጭነት ለማስረገጥ እንዲችል ራስን በራስ ማስረዳደር እስከ መገንጠል መብት እውቅና የተሰጠው መሆኑ እንቅፋቱ ምኑ ላይ ነው፡፡

እንዲያውም የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሳውን ቡድን ወደ አማራጭ ፖለቲካ በማስገባት ተወዳድሮ እየተሸነፈ በሂደት አመለካከቱን እየቀየረ ከአንድነት በመለስ ባሉ ቁምነገሮች ላይ እንዲታገል ለማድረግ የሚቻልበት እድል ይፈጥራል፡፡ አቋሙን ባይቀይር እንኳ በአማራጭነት እየተወዳደረ እየተረታ ይቀጥላል፡፡ ህዝብ በምርጫነት የሚቀበለው ከሆነም ህገመንግስታዊ አግባቡን ተከትሎ የሚሆነው ይሆናል እንጂ ህዝብ በዚህ ጥያቄ ዙርያ ነፍጥ እየተማዘዘ እየተዳማ መኖር የሚኖርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

ሁሉም ራሱን ማስተዳደሩ ነውሩ ምኑ ላይ ነው፡፡ አማራውን ኦሮሞው ኦሮሞውን ትግሬው ትግሬውን ደቡቡ ሲያስተዳድረው ነው ማለት ነው ህዝቡን ጸጥ ሰጥ አድርጎ ስለአንድነቱ ብቻ እንዲያስብና እንዲያቀነቅን አድርጎ መኖር የሚቻለው፡፡ እኔ በበኩሌ ከየትኛውም ክልል ማንም መጥቶ ለአንድነት ያለኝን እምነት እንዲያጣራ አልፈልግም አንድነቱን ስለምመርጠው እኖራለሁ አያዋጣኝም ብዬ ሳምን ደግሞ ተሟግቼ በህገመንግስቱ መሰረት የመገንጠል መብቴን ለማስከበር እጥራለሁ እንጂ ማንም በውክልና ከሌላ ክልል መጥቶ አቋሜን እየተከታተለ የስለላ ስራ ስላከናወነ አንድነቴን ያስመርጠኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ይሄ የዜጎችን ህሊናዊ መብት መናቅ ነው፡፡


አንድ የምንሆነው መገንጠል በአመራጭነት የማይቀርብበት አለም እና ሀገር ስለሆነ ሳይሆን ያ ሆኖ ሲያበቃ ህዝቡ የአንድነት አማራጩን አልቆ ስለሚያየውና በላቀ አማራጭነቱ ስለተቀበለው ነው፡፡ ያ ባይሆንማ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ህወሀት በትግራይ ህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ያክል የነበረው ኦነግ ባልከሰመ ነበር፡፡ ይሄ የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የመገንጠል ኢትዮጵያዊነትን የመጥላት ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበሩለት ማድረግ ስለነበርና ያ ደግሞ በተግባር መረጋገጡን ሲያየው ትግል የሚያደርግበት አጀንዳ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ ይልቅ ትግሎቹ ከዚህ በመለስ ባሉ የዴሞክራሲ የኢኮኖሚና የመልካም አስተዳደር ጉዳዩች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡


ተመሳሳዩ በሶማሌ ክልል ይንቀሳቀስ በነበረው ኦብነግ ላይ እየሆነ ያለው ሶማሌ ክልል የዘገየ ቢሆንም የልማቱና የሰላሙ ተጠቃሚ እየሆነ በመሄዱ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ ሊያሳካ የሚችለው የሚጨበጥ ጥቅም በሌለበት አንድነትን በመገንጠል ተክቶ ሊሄድ የሚችልበት አንዳች ምክንያት አለመኖሩን ነው፡፡ መገንጠል አማራጭ ሆኖ ሊቀርብና ሊነሳ የሚችለው ህዝብም በዚያ ዙርያ ሊሰባሰብ የሚችለው አብሮ መኖር መዳማት መበደል  ካልሆነ በቀር ጠብ የሚያደርገው ጥቅም የሌለ እንደሆነ ነው፡፡


በመሆኑም በሀገሪቱ እየተጠየቀ የነበረን የመገንጠል ጥያቄ መድፈቅ አልነበረም አማራጩ፡፡ አማራጩ እንዲያውም እንዲህ አይነቱ ጥያቄ የሚነሳው ህዝብ በአንድነት የሚኖርበት ስርአት መፈናፈኛ ያሳጣው እንደሆነና አንድነቱ ሊያስገኝለት የሚችለውን ጥቅም ያላስገኘለት እንደሆነ ነው፡፡ ህገመንግስቱ በሚጸድቅበት ግዜ ጉዳዩን ለመራዳት ህጻን ብሆንም ዛሬ የነበረውን ሁኔታና የተወሰደውን አማራጭ በመመልከት ስገመግመው የህዝብን የመገንጠል መብት ወይም ህዝብ በተሟላ መልኩ ባያሳምኑ እንኳ ቡድኖች የያዙትን መብት በመካድ ሊገኝ የሚችለው ስኬት አይታየኝም፡፡


መገንጠል በአማራጭነት የሚቆምበትን ረድፍ የምንረዳ ቢሆንም ህዝቦች በሙሉ በመተማመን በተለያዩ ምክንያቶች ከመረጡት ግን መከልከል ያለበት መብት አደለም፡፡ አንድነታችን መጠበቅ ያለበትም እንዲያ ያለውን መብቱን ህዝቡ ስለማያውቀው ወይም ስለተነፈገ ሳይሆን አንድነት በአማራጭነቱ የበለጠው አማራጭ ስለሆነና ህዝባችን በመከባበር ከጭቆናው ጋርም ቢሆን አብሮ የኖረ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም የገነባው የጋራ እሴት ያለው በመሆኑና አካባቢው እንኳንና ተለያይተን አንሰን አደለም እንዲህ አንድ ሆነንም ከጸጥታም ከፖለቲካም ከኢኮኖሚም ከድርቅም አንጻር ሰፊ ችግሮች የተደቀኑበት በመሆኑ አብሮ ሆኖ መስራቱ የላቀ ተሰሚነት ተፈሪነት እና አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡


ህዝቡ ይህን የመሰለውን ጉዳይ ማወቅ የለበትም ህዝቡ ቢያውቅም መነፈግ አለበት የሚለው አካሄድ የህዝብን የማወቅ መብት የሚጋፋና የህዝብን ሕሊና የሚያንቋሽሽ ነው፡፡ ስለሆነም መገንጠልን በመብትን አውቃ ስታበቃ ሕዝቡ አንድ አድርጎ ሊያስቀጥለው የሚችል ታሪክና ባህል ያለው እንደሆነ በህገመንግስቱ በማጉላት የሚሻለውን አማራጭ ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ የፖለቲካ መሪዎቹን ዴሞክራሲያዊነትነሰ አንድነቱን ይህም መብት ተከብሮ ሲያበቃ ለማስቀጠል ስለመቻላቸው ያላቸውን በራስ መተማመን ያመላክታል፡፡ ከፍ ሲልም ሕዝቡ የተሸለ አማራጭ እስከቀረበለት ድረስ የሚያውቀውን እና በህገመንግስቱ የተደነገገለትን የመገንጠል መብቱን ችላ ብሎ ሌላውን እና የተሻለውን አማራጭ አንድነትን የሙጥኝ ብሎ እንደሚኖር መገንዘብንም ይጠይቃል፡፡


በተቃራኒው ደግሞ የመገንጠል መብት በህገመንግስቱ አለመደንገጉ የሚኖረው ፋይዳ ምንድንነው፡፡ እንዲያውም ባይደነገግ መገንጠል ሲያቀነቅኑ የከረሙ ቡድኖች የህዝቦች መብት ላለመከበሩ የሚያቀርቡት ማሳያ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡


በሌላም መልኩ አንዳንድ ግለሰቦች የብሄር ጥያቄና የመገንጠል ጥያቄ መነሳት የጀመረው ህገመንግስታዊ እውቅና ከተሰጠው ግዜ ጀምሮ ያስመስሉታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የመነገንጠል አቋሞችን ልንሰማ የበቃነው ህገመንግስታዊ ድንጋጌው እውቅና ከዳረገለት አንስቶ ይመስላቸዋል፡፡ ሲቀነቀን ስለከረመና አለማቀፋዊ እውቅና ተሰጥቶት የከረመ በመሆኑ እውቅና መንፈግ በተለይ እኛ በምንኖርበት ከባቢያዊ ፖለቲካ አንጻር ሲመዘን ፍጹም ብልህነት ነበር፡፡


በርግጥ ውስጥ ውስጡን ይብላላ የነበረውን የብሄርና የመገንጠል ጉዳይ ኢህአዴግ በማፈን ለውጥ እንደማይመጣ በማመኑ ቡድኖች የመሰላቸውን አቋም ያለስጋት በአደባባይ እንዲናገሩት የሚያስችል ሀሳብን የመገለጽ መብት አጎናጽፏል፡፡ የሆነ ሆኖ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ የሚታወቀውን እና ህዝቡ ለረጅም ግዜ የኖረውን አንድነትን ከገንጣይ አቋሞች ጋር ተሟግቶ ማሸነፍ የማይችል የፖለቲካ ፓርቲ ከጠፋ ድክመቱ ብቁ ፓርቲ ያለመኖር እንጂ አለማቀፋዊ እውቅና የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት ማጽደቃችን ተደርጎ መወሰድ አይገባውም፡፡


የመገንጠል አቋም ስለተቀነቀነ አገር ተገነጠለ ማለት አደለም፡፡ ሰሜን አየር ላንድ ለዘመናት ከብሪታንያ ለመገንጠል የሚሰሩ ቡድኖች እና አቀንቃኞች ቢኖሯትም አንድነቱን በሚሹት ተሸንፎ እስካሁንም ድረስ ሰሜን አየርላንድ ከብሪታንያ ጋር ለመቆየት በቅታለች፡፡ በሌላም በኩል የስፔን ፌደራል ስርአት አልጣመንም በማለት የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱና አልፎ አልፎም ሽምቅ ውጊያ የሚያካሂዱ ቡድኖች አሉ፡፡ የሆነ ሆኖ አንድነትን የሚያበረታታው ሕጋዊ መዋቅርና አንድነትን የሚሹት በመበራከታቸው ስፔን አንድነቷን አስጠብቃ መኖር ችላለች፡፡ የመገንጠል መብትን ህዝብ ማወቁ የግድ መገንጠልን የሚያስከትል ቢሆን ኖሮ ስፔን በርካታ ክልሎቿን ባጣች ነበር፡፡


ትልቁ ነገር የግድ መለያየት የሚጠይቅ ነገር እንኳ ቢኖር ያን መመለስ እና ማስተናገድ የሚችል ህገመንግስታዊ አሰራር የተዘረጋ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ ደግሞ የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱትን በዲሞክራሲያዊ ውድድር እየረቱ ለመቀጠል ብቁ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ እና ትጉህ ፓርቲ ሆኖ መገኘት፡፡


በዚህ ሚዛን ሲለካ ኢህአዴግ ከመመስረቱ ቀድሞ ለሚቀነቀነው ጉዳይ የብሄሮችን ማንነት በሚያከብር በቋንቋ መጠቀም የሚያስችል እና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚፈቅድ መንግስታዊ መዋቅር መፍጠር መቻሉ በለጋ እድሜው ያሳካው ትልቅና ዘመን የሚሻገር ድሉ  እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment