Tuesday, September 3, 2013

እዚህ አገር ብዙ ችግር አለ




አዎ እዚህ አገር ችግር አለ፡፡ ችግሩን ደግሞ በየእለቱ በየሰአቱ በየደቂቃው እየኖርነው ነው፡፡ በአንድ በኩል የመሰረተ ልማት እጦቱ መሰረተ ልማቱ ሲኖርም በአግባቡ አለመስራቱ የሚፈጥርብንን ምሬትና ጉዳት በሌላ በኩል በየለቱ የሚሞቱት ሕጻናት እና እናቶች በየግዜው መመገብ ያልቻልናቸው ነገሮችና ልናገኝ ያልቻልነው የህክምና አገልግሎት የበለጠ ያሳምመናል በቀላሉ፡፡ ልናገኝ ስንችል ያላገኘነው መንግስታዊም ግለሰባዊም አገልግሎት ይጎዳናል ያስመርረናልም፡፡


ቁምነገሩ ግን እንደማንኛውም አንድ ግለሰብ ማማረርና የችግር አለ ትርክት ማሳመርና ማስዋብ አደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በፖለቲካውና በኢኮኖሚው በንቃት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሁነኛ ሀላፊነት የችግሩን ምንጭ በአስተማማኝ ጥናት መለየት ምንጮቻቸው ለታወቁ ችግሮች ተገማች እና ሳይንሳዊ መፍትሄ መቀመር እና ይሄው መፍትሄ ተተግብሮ እሚፈለገው ለውጥ እንዲገኝ ማድረግ ነው፡፡


ከመደበኛው ማህበረሰብ እኩል ችግር አለ እያሉ ለማስተጋባት ከሆነ በፓርቲ ደረጃ የምንሰባሰበው ይሄ ፋይዳ የለውም፡፡ መሰባሰብ እንደ ፓርቲ መቆም የፖለቲካ አጀንዳ ነድፎ መንቀሳቀስ ጠቃሚ የሚሆነው መደበኛው ግለሰብ አጥንቶ ሊደርስባቸው የማይችላቸውን ጉዳዩች በተደራጀ መልኩ አከናውኖ ችግሮች የሚፈቱበትን አግባብ የሚቀመር ከሆነ እንጂ ከመደበኛው ግለሰብ እኩል ችግር አለ ለማለትማ በፓርቲ ደረጃ መሰባሰብ አያስፈልግም፡፡ ያንማ ሰለማዊ ሰለፈኛም ያደርገዋል፡፡ ቁምነገሩ መፍትሄውን አፈላልጎ ማግኘት በዚያ ዙርያ ድጋፍ አሰባበስቦ ሕዝብን አሳምኖ ምርጫ ማሸነፍና የመሪነቱን ሚና ተቀብሎ ሕዝብ ይገባዋል የምንለውን ጥቅም ማሳካት መቻል ነው፡፡


በምን ስሌት ነው ችግር አለ ብሎ የምናውቀውን ችግር ስለተረከልን አንድን የፖለቲካ ድርጅት ሀገር የመምራት ሀላፊነት የምንሰጠው፡፡ ጥያቄው የመፍትሄ እንጂ የችግሮች መኖርን ክሽን ባለ ቋንቋ የማቅረብ ያለማቅረብ ጉዳይ አደለም፡፡ ችግር እንዳለ ኑሯችንን ጠቅሰው አስረዱን እንበል ይሄን ማድረጋቸው የሚባለውን ችግር የመፍታት ሁነኛ መነሻውን የመለየት እና የተበጀውን መፍትሄ የመተግበርና የማስተግበር ድርጅታዊ አቅማቸውንና አቋማቸውን ሊያሰየን ይችላል እንዴ? አይችልም፡፡ የፓርቲ ሁነኛ አላማም ህዝብ የሚማረርበትን ችግርና አሁን ካለው ቁመና አንጻር ወደፊት ሊገጥሙት የሚችሉትን ተገማች ተግዳሮቶች በመተለም ችግር የሚፈታና ሀብት መፍጠር የሚችል አመራር መስጠትና ማስተግብር እንጂ ችግር ተራኪ ድምጽ መሆን አደለም፡፡


የፓርቲዎቻንን ዲስኩርና ቁመና ከችግር አለ ወደ የችግሮቹ ምንጮች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህን ሁነኛ ማነቆዎች እየፈታን ስንሄድ ችግሮቹ በዚህ መልኩ በዚህን ያህል ግዜ በዚህ ደረጃ በዚህ ምጣኔ እየተፈቱ ይሄዳሉ ወደሚል ይዘት መቀየር የሚኖርባቸው ይሆናል፡፡ ችግርማ አለ ችግር ሁሌም መኖሩ አይቀርም፡፡ ደሀ ያደረገን ግን የችግር መኖር አደለም፡፡ ዋናው ችግር ችግሮችን በተጠና መልኩ በሂደት መፍታት የሚችል አቅምና ሀይል አለመፍጠራችን ነው፡፡

ችግር ፈቺዎቹ ፓርቲዎች ከወዴት ናቸው
ችግር በለሙ ሀገሮችም አለ፡፡ የለሙ ሀገሮች የተለየ ውበት ችግር አለመኖሩ አደለም፡፡ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ችግሮችን ተጋፍጠው መፍትዬ የሚያበጁ ችግሮችን በጥናት ላይ በመመስረት ወደ ሀብትነት እና ልማታዊ አቅምነት የሚቀይሩ ግለሰቦችና ተቋሞች መፈጠር መቻላቸው ነው፡፡ አገሮች ለምተዋል የሚባሉት ችግሮችን በመፍታት አቅማቸውና ችግሮች ከመፈጠራቸውም ቀድመው በመገመት ለችግሮቹ መፍትሄ የሚሆኑ እሴቶች ሀብቶች እንዲሁም ተቋማዊ ግለሰባዊና መዋቅራዊ አቅሞች በመፍጠራቸው ነው፡፡


ችግር እንዳይከሰት ያደረገ ችግርን ያጠፋ ወይም ችግሮች እንደተከሰቱ ወዲያውና ባንዴ መፍታት መቻል አደለም የለሙት አገሮች መገለጫ፡፡ መገለጫቸው ችግሮችን በመፍታት ረገድ በመንግስታዊም በኮርፖሬት ደረጃም ይሁን በግል አቅም መመደብ የሚችሉት ካፒታል በሂደት መፍጠራቸው ችግሮችን የሚፈቱ አቅሞች ያደራጁና በታቀደ መልኩ በየእለቱ የሚሰሩባቸው መሆኑ ሲለጥቅም ችግሮችን ከደንቃራነት ወደ ሀብትነት መቀየር የሚያስችል የደረጀ ሀብትፈጠር አመለካከት እና አደረጃጀት መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡


አለበለዚያ የጤናው ይባል የትምህርቱ የማህበራዊ ደህንነቱ የወጣቶች በአጋጉል ልምዶች መጠመድ የመጠለያ የምግብ እና በተወሰነ ደረጃ ፍትሀዊ ብያኔዎች ያለማገኘት እና በዚያውም የማማረር አዝማሚያ አለ፡፡ ይህ ባለበት እንግዲያው ለምን ለሙ እንላቸዋለን? መልማት የሚገለጸው በችግር አለሞኖር ከሆነ::


ሀቁ መልማት ማለት ችግሮችን በተጠና መልኩ የመፍታት አቅም የማደርጀት በተመሳሳይ መልኩ ሀብትን አቅደውና አልመው መፍጠር የሚችሉ አቅሞች በግለሰቦችም በተቋሞችም ማደለብ ለነዚህ ዘርፎች ገንዘብ በድጎማም በብድርም በኢንቨስትመንት መልክም ማቅረብ የሚችል የዳበረ የፋይናንስ አቅም መፍጠራቸው ነው ትልቁ የመልማታቸው ማሳያ፡፡ ይህን አቅም በማንቀሳቀስ የስራ እድል መፍጠር የመልማትና ችግር የመፍታት አቅሞቻቸውን የበለጠ የመገንባት ለችግሮች በጥናት ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎች በተከታታይ እና በተሻለ ቴክኖሎጂ ማቅረብ መቻላቸው በዚሁ ሂደት የህዝቡን ገቢና ተጠቃሚነት በተከታታይ እና ያለማቋረጥ እያሳደጉ መሄዳቸው ነው፡፡


ልማት ከዚህ አኳያ ነው የሚመዘነው፡፡ እድገት በዚህ መነጽር ነው የሚታየው፡፡ ለዚህም ነው በለሙት ሀገሮች ያሉት ፓርቲዎች ሁነኛ ክርክር እና አማራጭ ለነዚህ አቅሞች በሚያቀርቡት ድጋፍና በሚያቀርቡት አቅጣጫ ዙርያ የሚያጠነጥነው፡፡ የሆነ ሆኖ አላማዬ በለሙ አገሮች ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ተቃራኒን ማጣጣልን እንደ ታክቲክ የሚጠቀምም ቢሆን የሚያቀርባቸውን ኢኮኖሚያዊ የፖሊሲ እና የአፈጻጸም ተስፋዎች ከሞላ ጎደል ዘርዘር አድርጎ በማቅረብ የሚካሄድ መሆኑን ማመላከት ነው፡፡


ለምን ብሎ ህዝብ ታዲያ ችግሩን ሊፈታለት ለማይችል በስም ብቻ አማራጭ ሆኖ ለቀረብ ፓርቲ ድምጹን ይሰጣል፡፡ ፓርቲ ሊመረጥ የሚችልበት ቃል ኪዳን ህዝብ የተቸገረባቸውን አንገብጋቢና መሰረታዊ ችግሮች ሊፈታ የሚችል እቅድ አቅጣጫና ፖሊሲ ካልሆነ በቀር ምን ሊሆን ይችላል፡፡ 


አማራጭ ፓርቲዎችም ሀገር የገጠማትን ችግሮች በመፍተት ረገድ የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮችን ተልመው ያ ፖሊሲ በምን አግባብ በነማን እንዴትና መቼ እንደሚተገበር በማቅረብ ከህዝብ ድጋፍ የመሰብሰብ እና አሸናፊ መሆን ነው፡፡ ለጥቀውም ፕሮግራሞቻቸውን በቃላቸው መሰረት መተግበር እንጂ የፖለቲካ ስልጣን ወቀሳ መጥመቅ ለተሳካላቸው ቡድኖች እንደዘበት የሚቸር ሀላፊነት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡


ሲጠቃለል እዚህ አገር ያለው ትልቅ ችግር ችግርን መፍታት እንደ ግብ የያዘ ተቃዋሚ ፓርቲ የሌለን መሆኑ ነው!

No comments:

Post a Comment