Monday, June 24, 2013

አገር የባለአፍ ሳይሆን የባለአገሩ ናት

አንዳንዴ በየከተማው ጥጋጥግ ይዘው የሞቀ እየበሉና የጣፈጠ እየጠጡ ያለእኛ ባለአገር ያለ እኛ የህዝብ እና የሀገር ተቆርቋሪ የለም የሚሉን የቃል ዘማርያን ያጋጥማሉ$ 

በቁምነገሩ በየለቱ በሬ ወለደ ማለታቸው የጀግነታቸው ሀውልት ሆኖ በየወቅቱ ሚዛኑን ያልጠበቀ ወቀሳቸው ለሀገራቸው የሚያበረክቱት ትልቅ ፋይዳ ሆኖ እነሱ እንጂ ሌላ ጀግና እዚህ አገር እንደሌለ እንዳወጁ ይኖራሉ$ ቀሽም ቁምነገራቸው ነው$

ባላገሩ አፍ ያለውና ያወራ አደለም$ ባለጉዳዩ የወቀሰና የተቸው አደለም$ እውነትም እየተወራጨ ከሚያወራና ከሚያለቃቅስ ጋር ትሆናለች ማለት አደለም$ የኛ የከተሜዎች ጫጫታ ሲደራ አንዳንዴ ይሄ አገር የአርሶ አደር አገር መሆኑ ይጠፋኛል$

እዚህ አገር የጠናው ችግር የትኛው ነው? ዋናው የሀገሬው እሮሮ የሀይ አትበሉን የእንዳሻን እንሳደብ እንጻፍ እና እናጣጥል ዝንባሌና ተግባር ነው ወይስ የባላገሩ መሰረታዊ ጉዳዩች?

እኔ ጋዜጦቻችን መጽሄቶቻችን እና አብዛኛው ሚድያ ሲልም የተማረ የሚባለው ኢትዩዽያዊ ሀገሩን ያውቃል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ$ እቺ አገር የገጠሬ አገር እቺ አገር የአርሶአደርና የአርብቶአደር አገር መሆኑዋን በቅጡ እናውቃለን? እናም የገጠሬው ችግር እኛ ድዳችንን የምናለፋበት ወልካፋና ቀርፋፋ ጉዳይ ስለመሆን አለመሆኑ አስበን እናውቃለን?

በቀን 700 መቶ ህጻናት እንደ ዶሮ በየጓሮው በሚቀበሩበት አገር በሺዎች የሚገመቱ እናቶች በሚሞቱባት አገር እውን የሚያንገበግበን ጉዳይ ጉንጭ አልፋ ቀደዳ ነው ወይስ ለውጥ የሚያመጣ የህጻናት እና እናቶች ክብካቤ? ንጹህ የመጠጥ ውሀ ለዘመናት ያላየውን ገጠሬ ተጠቃሚ በማድረግ ከውሀ ወለድና ከንጽህና ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎችን የመከላከል ጉዳይ ነው አንገብጋቢው ወይስ የእገሌን አስተያየት ማጣጣል ነው?

እውን አንገብጋቢው ጉዳይ የእርሻ ስራችንን በቅጡ እየተከታተሉ ተግባሮቹ እና ቁሳቁሶቹ የሚሻሻሉበትን መላ መምከር ነው ወይስ አጉራዘለል አስተያየት እየሰጡ እራስንን እንደ ጀግና መቁጠር ነው? ጀግና በወጉ የዜጎቹን ህይወት መቀየር የሚችል ስራ የሚያከናውን ዜጋ እንጂ የወሬ አርበኛው ሁሉ አደለም$

ባላገሩን የሚመለከተው ይሄ ይሄ ጉዳይ እያለ የገሊት ቀሚስ ያምራል እገሌ ሊያገባ ነው ሰርጉ ላይ እንዲህ አይነት መኪና ይኖራል ታምራት እዚህ ባንክ ይሄ አለው አዜብ እዚህ ባንክ ይሄን ያህል ሀብት አላት የሚል ዝባዝንኬ ማውራት እንመርጣለን$ በርግጥ ያወራ ሁሉ ባላገር ይሆን ቢሆን ይሄ ገጠሬ በጠፋ ነበር$ በወጉ የሀገሩን ገጠር የማያውቅ ሚድያ እዚህና እዚያ ስላለው የተሰረቀ ገንዘብ የማወቅ እድሉ ጠባብ ነው$

ባላገሩ ከመሬት እግሩና እጆቹ የሚነቀሉበትን የትምህርት ስራና የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ሲያብጠለጥል የሚውል ባወራና በወቀሰ ልክ አስተዋጾ ያበረከተ የሚመስለው ዜጋ የከንፈር ላይጌጥ መሆን ቢችልም መሬት የሚነካ ለውጥ ማምጣት ይሳነዋል$ ባላገሩን 83 በመቶውን ህዝብና መሬቱን የማያውቅ የጋዜጣና የፌስቡክ ዲስኩር አገር የሚቀይር አቅም አይኖረውም$ የሽባ ፖለቲካ ሁነኛ መገለጫ የማያውቀውን ህዝብ ነጻ ለማውጣት መቋመጡ ነው$

ባላገሩ ገጠሬው ባላገሩ አርሶአደሩ ነው$ አርሶ አደሩን የሚመለከት የመሰረተ ልማት ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ የማይከታተል ሚድያና የወቀሳ ሱስ ያናወዘው ግለሰብ አገር አይቀይርም$ አገርም ሲጀመር ማን እንደሆነ አያውቅም$ በአርሶ አደር አገር የከተማውንም ሰው አንድ የማያደርግ ሽባ አጀንዳ ይዘው እንጣጥ እንጣጥ የሚሉ ተቃዋሚዎችም ይሁኑ የዚያው አቋም ካድሬዎች የሚያመጡት ፋይዳ አይኖርም$


ባላገሩን የማያውቅ ካድሬና ፓለቲካ ባላገሩ የሚያንገበግበውን የለተለት ችግር መነሻ የማያደርግ ቅኝት የትም አይደርስም$ ገና ሲጀመር ወሳኙን ባለ ሀገር ስለረሳ የተረሳ የትም የማይደርስ ፉርሽ የፖለቲካ ቁማር እንደሆነ ይገባናል$ አገሬ ለማለት አገራችን የገጠሬ የአርሶአደር የአርብቶአደር አገርና የከተማ ደሀ አገር መሆኗን ማወቅ ይጠይቃል$ 

ፈረንጆቹ አገር ሲሆን የሰማነው ሁሉ እዚህ አይሆንም$ አገርህን እወቅ በርግጥም ትግል አምሮህ ከሆነ ለዚህ ገጠሬ ታገል$ ግዙፍ ችግሮቹ ሲፈቱለት ግዙፍ ሀብት መሆን የሚችል አቅም ነውና$ አገር የባላገር አገር የገጠሬ እንጂ የዘራፍ ባዩቹ አደለም$

No comments:

Post a Comment