Sunday, April 21, 2013

ድሀውን ያልጠቀመ እድገት?! ክፍል 2


ሁለተኛው የመልሴ የማብራርያ ክፍል በማህበራዊና ዘርፍና በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የተገኙ ውጤቶችን ተመርኩዞ እንደሚከተለው ተሰናድቷል$ መልካም ንባብ$

ማህበራዊ ለውጦች እንደ እድገቱ ማሳያ
ሀገራችን ባለፉት አመታት ካሳየቻቸው ለውጦች ውስጥ መጠቀስ ያለባቸው ትላልቅ ስራዎች በኔ እይታ የማህበራዊ ዘርፉ ስራዎች ናቸው$ በተለይም ደግሞ ትምህርትና ጤና ያሳዩት ለውጥ$ ሶማሌ አፋር ጋምቤላና ቤኒሻንጉልን ትተን የሀገራችን የትምህርት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን መቶ በመቶ ሊባል በሚችል ደረጃ ተሳክቷል$

እየተነሱ ያሉ መሻሻል ያለባቸው የጥራት ጉድለቶች እንደተጠበቁ ሆነው ስለ ትምህርት የማይታሰብባቸው ገጠራማ አካባቢዎች በቅርባቸው ትምህርት ቤት እያገኙ ከመቆፈር የተለየ ስራ የማግኘት እድላቸውን ከማስፋትም በላይ ያንኑ የእርሻ ስራም ቢሆን በተሻሉ አሰራሮች የመምራት አቅሙና የአዲስ ቴክኖሎጂ አቀባበሉ የተሻለ ዜጋ በመፍጠር ረገድ ትምህርት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው$ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተማረ ህዝብ መብቱን የመጠየቅ የአካባቢዉን መሪዎች የመሞገት የመገምገም ጥቅሞቹን የማስጠበቅ አቅሙን እንዲያሳድግ ማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም$ አንዳንዶቹ ለውጦች በ10 አመትና በዚያ ግዜ የምናያቸው ባለመሆኑ ጉልህ ባይሆንም ጥንስሳቸው ግን የሚጭበረበር አይመሰለኝም$

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በየአካባቢው በማዳረስም ረገድ ከፍትሀዊነትም ይሁን ከብዛታቸው አንጻር የሚታየው ለውጥ በጎ የሚባል ነው$ ይሄ በየአካባቢው የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ በገበያና አካባቢውን በማነቃቃት ረገድ ያለው ሚና ቀላል አደለም$

በሚለንየሙ ግቦች ማብቂያ ግዜም ሀገራችን ከስምንቱ ግቦች ስድስቱን ማሳካት ከሚችሉ ወጤታማ ሀገሮች መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል$ ሁለቱ በዚሁ ግዜ የማይሳኩት የእናቶችና የህጻናትን ሞት የሚመለከቱት ግቦች ናቸው$

በርግጥ በዚህም ረገድ ሀገራችን የሞቱን ቁጥር ከግማሽ በላይ መቀነስ የቻለች ቢሆንም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት ሳይሄዱ በፊት ዶር ቴድሮስ እንዳሉት ለውጡ ግዙፍ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን የሞቱ መጠን ትልቅ ስለሆነ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይታወቃል$ በለውጡ መደሰታችን ባይቀርም የቀረንን ጉዞ ጨርሰን አንድም እናት በውልጃ ምክንያት አትሞትም የሚለውን ህልማችንን ማሳካት ይኖርብናል$ ይሄ ሀገሪቱ ከእድገቱ የተገኙ ተጫማሪ ሀብቶችን የማህበረሰቡን ጤና ለማሻሻል እያዋለች ስለመሆኑ ያመላክታል$ በቅርቡ ከወሊድ ጋር የተያያዘ ማንኛውም የመንግስት ጤና ጣብያ የማዋለድ አገልግሎትን ጨምሮ ነጻ እንዲሆን መደረጉ የዚሁ ጥረት አንድ ክፍል መሆኑን ማየት ይቻላል$

በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ይሞት የነበረውን ዜጋ ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰማሩት ከ34 ሺ የሚልቁ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በመታጠብ መዳን መጸዳጃ ቤት በመስራት መዳን የአመጋገብ ስርአትን በማሻሻል መዳን የእርግዝና ክትትል በማድረግ መዳን በጤና ጣብያ በመውለድ መዳን እንደሚቻል ያሳዩና በዚሁ ጥረት በርካታ ዜጎች በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች እንዳይሞቱ የተሰራው ስራ በተለያዩ አለማቀፍ መድረኮች በአለማቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶችም ሳይቀር የተሞካሸ ነው$ በመሆኑም ይሄ ከእድገቱ የተገኘውን ፍሬ 83 በመቶ ለሚሆነው ድሀውና ገጠሬው ሀገሬ በማዳረስ ረገድ የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ያመላክታል$

ከዚህ ሌላም በማህበራዊ ዋስትና ረገድ እየተፈጸሙ ያሉ ስራዎችም ተስፋ ሰጪ ናቸው$ አንደኛ በሴፍቲኔት ረገድ የተለመደውን እህልና ገንዘብ የማደል አዝማሚያ በመቀየር ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ማካሄድ በድርቅ በተደጋጋሚ የሚጠቁ አካባቢዎች ቋሚ ትምህርት ቤት ጤና ጣብያ ውሃ እና ሌሎች አስተዳደራዊ መዋቅሮች እንዲኖሯቸው በማድረግ አካባቢዎቹ በዘላቂነት የሚያጋጥሟቸውን ተደጋጋሚ ችግሮች እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየተሰራ ያለው አፈጻጸምም ይቀጥል ያሰኛል$

በመሆኑም ይሄም የሚሰጠው አመራር ወጤታማ እንደሆነና እድገቱ በፍትሀዊነት መከፋፈል የቻለ መሆኑን ያመላክታል$ ከዚህ ውጪም መንግስት በአቅሙ ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ለማገዝ በሙከራ ደረጃ ከተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየሞከራቸው ያሉ ፕሮግራሞች አሉት$ በሂደት እነዚም ቢሆኑ መንግስት 1 በመቶ የታክስ ገቢውን በጅቶ ሊፈጽማቸው የሚያስባቸው በመሆኑ የሚበረታቱ ናቸው$ ይሄም እድገትን ለድሀውና ለማህበራዊ ችገሮቹ መፍቻነት በማድረግ ረገድ የሚታዩትን ለውጦች የሚያመላክት ነው$

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ዛሬም ችግሮቿን አሟጣ ለመፍታት ካላት የህዝብ ብዛት አንጻር ረጅም መንገድ መጓዝ ያለባት ሀገር መሆኗን የሚያመላክት እንጂ የማዘናግያ ደወል አደለም$ ለውጥ እያመጣ ያለ ስራ መኖር የችግሮች ተሟጦ ማለቅ አዋጅ ተደረጎ መቅረብ የለበትም ልክ ለውጡ በዚያ እየተሳበበ መካድ እንደማይኖርበት ሁሉ$

የመሰረተ ልማት ግንባታ
የመንገድ መብራት የማመጨትና የቴሌኮም ማስፋፍያ ስራዎች ከፈጠሩት የስራ እድል ካነቃቁት እና ካሰማሩት በርካታ ቢዝነሶች አኳያ ሲለካ እድገቱ በዘላቂ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩር መደረጉን የሚያመላክት ስለመሆኑ አያጠራጥርም$ መንገዶቹ አንደኛ የትራንስፖርት ዘርፉን በማሳለጥ ረገድ ያስገኙት ጥቅም ሁለተኛ የንግድ ስራውን እና የአርሶ አደሩን ምርት ወደ ተጠቃሚው በማድረስ ረገድ የላቀ ሚና ያላቸው ናቸው$

ባንድ በኩል የመንገድ ስራውን ማካሄድ የሚችሉ ሀገራዊ ኮንትራክተሮችንና ባለሞያዎችን በማፍራት ሀብት መፍጠር የተቻለ ሲሆን በዚያው ሂደት የተሰሩት በሺዎች ኪሎሜትሮች የሚቆጠሩ መንገዶች ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት መፋፋም ወሳኝ የሆኑ አቅሞች ከመፍጠር ጎን ለጎን በዛሬውም ግዜያዊ ውጤቱ ትልቅ ሀገራዊ መነቃቃት የፈጠሩ ናቸው$ በርግጥ ይሄ በቀጥታ ወደያንዳንዳችን ኪስ የሚገባ ገንዘብ አይሆንም$ ግን እንቅስቃሴያችንን ቀላል በማድረግ ረገድ የራሱ ሚና አለው$

ቴሌኮሙ መስፋፋቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚኖረንን መረጃ ፈጣን ከማድረጉም በላይ በመላ ሀገሪቱና በአለም ዙርያ የሚከናወኑ ነገሮችን ለመከታተል የሚያሰችል በመሆኑ የማህበረሱቡን አስተሳሰብና ውሳኔ መረጃ ቀመስ በማድረግ ረገድ ላቅ ያለ ሚና ይኖረዋል$

በየገጠሩ እየገባ ያለው የመብራት አገልግሎትም ማህበረሰቡን ከኩራዝ ከመገላገሉም በላይ በየአካበቢዎቹ ቢዝነስ በማነቃቃት ረገድ የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል$ ይሄ ወደ ገንዘብ ሀብት ወደማፍራት በሂደት የሚመነዘር ይሆናል$ በየወረዳው እየገባ ያለው መብራት በርግጥም በዚህ አገር አገልግሎትን ለከተማና ለገጠር ያለ አድሎ የማቅረቡን አሰራር ይበልጥ እያጠናከረው የሚሄድ ነው$

በርግጥ ከነኬንያ አንጻር ሲታይ ሀገራችን በቴሌኮም ረገድ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የማቅረብ ችግር ቢኖርባትም ቴሌኮምን እንደ ልማት አንድ አብይ መሳርያ በመላው ሀገሪቱ በማዳረስ ረገድ ግን በማንኛውም መመዘኛ ጥሩ ስራ እየሰራ ያለ መሆኑን ያመላክታል$ ይሄ ስኬቱ ግን የድክመቶቹ መደበቂያ መሆን አለበት ማለቴ አደለም$

የሆነ ሆኖ ቴሌኮምን የከተሜው ብቻ እንዳይሆን በማድረግ በመላው ሀገሪቱ እንዲዳረስና ሁነኛ የልማት አቅም በማድረግ ረገድ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው$ በቅርብ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያመለክተው ቴሌ በሞባይል እንኳ ወደ 20 ሚሊየን ገደማ ደንበኞች ያፈራ መሆኑ ይታወቃል$ በቴሌ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት የሞባይል ደንበኞች ብዛት ከ40 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ግምቶች ያመላክታሉ$

እነዚህ ለውጦች በዘርፉ እየተደረገ ያለው ኢንቨስትመንት ማህበረሰቡ የተሻሉ የመገናኛ አገልግሎት እንዲኖረው ለማድረግ መንግስት እያወጣ ያለውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ኢንቨስትመንት የሚያሳይና ከለውጡ አብዛኛው ገጠሬ ኢትዮዽያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት የሚያሳይ ነው$ በዚሁ የቴሌ የማሰፋፍያ ስራ ከሚፈጠረው ገቢ ውጭ ከቴሌ ጋር ተከያያዙ ሽያጮች ቀላል የማይባል ገቢ እያገኙ ያሉ መኖራቸው አወያይ አደለም$ ከሞባይል ስልክ መሸጫ ጀምሮ በሲም ካርድና በአየር ሰአት ካርድ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ቀላል አደለም$ ለዚያም ነው በርካታ አለማቀፍ የሞባይል አምራች ድርጅቶች የሀገሪቱን የሞባይል ገበያ እየተሻሙት የሚገኙት$

በማብራት ሀይል ማመንጨት ረገድም ሀገሪቱ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማሟያነት ከመስራትም አልፋ ለአካባቢው ሀገሮች የሀይል ምንጭ ለመሆን እያከናወነች ያለችው ትላልቅ የውሀ ሀይል ግድብ ግንባታዎች በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ$ በአሁኑ ወቅት ጊቤ 3 እና ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሀገሪቱ ከመብራት ሀይል ወደ 7 ሺ 800 መቶ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት እየሰራች መሆኑ ይታወቃል$ 

የንፋስና ሌሎች ትናንሽ የውሃ ሀይል ማመንጫዎችን ደምረን ስናስብ ከስምት ሺ ሜጋ ዋት በላይ የመብራት ሀይል በሚቀጥሉት 5 አመታት ውስጥ እንደሚለማ ይታወቃል$ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ውስጥ እስከ 2000 ሜጋ ዋት የሚደርስ ሀይል ለአገልግሎት እንደሚደርስ አንዳንድ ግምቶች ያሳያሉ$ በፈጠረው የስራ እድል እንኳ ሲመዘን የመብራት ሀይል የማመንጨት ስራው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የስራ እድሎች መፍጠር የቻለ ነው$

ከዚያም በላይ ባሰገኘው የእውቀት ሽግግር ሲመዘን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሀገራዊ አቅም እንደፈጠረ መመልከት ይቻላል$ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ በጊቤ 2 እና በበለስ ሀይል ማመንጫ ስራ ላይ የተሳተፈው የሰው ሀይል በግዙፉና ውስብስቡ የህዳሴ ግድብ ላይ ያንን ልምድና ክህሎት ይዞ የተሰለፈ መሆኑና ስራውን በተሳካ መንገድ እየመራ መሆኑ ነው$

No comments:

Post a Comment