Tuesday, April 2, 2013

ታክሲ ያጣ ተሳፋሪ በተሰለፈባት አዲስ አበባ ስራ ፈቶ የተሰለፈ ታክሲ ማየት ሁለተኛ ክስረት ነው!


                                                                                      ዘርይሁን ካሳ
ዛሬ ጠዋት ወደ ስራ ስገባ ሰርቢሳችንን ስላልተጠቀምኩ ታክሲ መያዝ ነበረብኝ $
ወደ ቦሌ የሚሄድ ታክሲ አጥቼ ከገርጂ የመገናኛ ታክሲ በሽበሽ ስለነበር በዚያ መንገዴን ቀጠልኩ$
መገናኛ ስደርስ ሁለት ረጃጅም የታክሲ ሰልፍ አጋጠመኝና አማራጬን ማሰብ ጀመርኩ$
ከቦሌ በአቋራጭ ካሳንቺስና በሀያሁለት ፒያሳ ነው ባለረጃጅም ሰልፉ$

በመሆኑም የአራት ኪሎ ፒያሳ የብሪታንያ ኤምበሲ መንገድ ሰልፍ ስላልነበረው ያን በአማራጭነት ያዝኩና ወደ አራት ኪሎ አመራሁ$
አራት ኪሎ ደርሼ ከቱሪስት ሆቴል ወደ አምባሳደር ታክሲ ልይዝ ስሄድ የሸወድኩት የመሰለኝ ሰልፍ እዚህ የበለጠ ረዝሞ ጠበቀኝ$

በግምት ስምንት ታክሲ ያክል የሚፈልግ ተሳፋሪ ተሰልፎ እየጠበቀ ነው$ 90 እስከ 100 የሚሆን ተሳፋሪዎች ይሆናሉ$ ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ በግሬ ከመሄድ ሌላ ቆሞ መጠበቁን ተያያዝኩት$

ምናልባት ወደ 20 ደቂቃ ቆይቼ ተራ ደርሶኝ ተሳፈርኩና ችግሩ በርግጥም እውን የታክሲ ማነስ ነው? እያልኩ ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ መንገዴን ቀጠልኩ$

ይሄ እጥረት ካለ ግን ምነው ብር ያላቸው ሰዎች ታክሲ እየገዙ የማያሰማሩት ወይስ ሹፌሩን ወያላውን ተቆጣጥሮ አትራፊ መሆኑ ከባድ ይሆን? በሚል ራሴን እየሞገትኩ አምባሳደር ስደርስ ከፍልውሀ መታጠፍያ ጀምሮ ታክሲዎች ቆመው አያለሁ$

የመጨረሻው ፌርማ አምባሳደር ደርሼ ስወርድ በርካታ ታክሲዎች አፋቸውን ከፍተው ቆመዋል$
በግርምት ከላይ ከፍልውሃ መታጠፍያ ጀምሮ የቆሙትን ታክሲዎች አምባሳደር መዝናኛ አካባቢ እስካሉት ድረስ ቆጠርኳቸው$

16 ታክሲዎች አፋቸውን ከፍተው አምባሳደር ቆመው ቱሪስት ሆቴል ላይ መቶ የሚሆን ሰው ተሰልፏል$
ሌላው ቢቀር ከፊሎቹ ታክሲዎች ቱሪስት አካባቢ እንዲቆሙ ከፊሎቹ ከአምባሳደር እንዲነሱ በማድረግ ተሳፋሪውም ባለሀብቱም መጠቀም አይችሉም ነበር?

ባለንብረቶቹስ አፋቸውን ከፍተው ታክሲዎቹ ከሚቆሙ በዚህ መልኩ እንዲደራጁ ማድረግ ይሳናቸዋል?
ትራንስፖርት ቢሮና ባለንብረቶቹ አይታያቸው እንበል ሹፌሮቹስ ይህን ማስተዋል ተሰኗቸው ነው?
እሺ ይህም ይቅር ያለምንም በቂ ተግባር በየታክሲ ተራ ተገትረው ብር የሚሰበስቡ ወጣቶች እቺን ታክል እንኳ አስተዋጾ ማበርከት ተስኗቸው ነው?

ይሄ የምር እጅጉን  የወረደ የስራ እና የአገልግሎት ስርአት እንዳለን የሚያመላክት እኮ ነው$ ቢያንስ ያለውን እንኳ ከወዲህም ከወዲያም ከመነሻም ከመድረሻም ማስቆም አይቻልም ማለት ነው?
አዲስ አበባ መስተዳድር የትራንስፖርት ቢሮውን በአግባቡ ሊያየው ይገባል$ ቢያንስ የሚያንሰው እስኪሟላ ባለው የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ አይቻልም እንዴ?

ሁሌ ላልተሳካ ስራ ሰበብ ከመደርደር እንዲህ ያሉትን የተበላሹ የመነሻና የመድረሻ ቦታ አነሳስ እና አካሄድ መልክ ማስያዝ የሚቻል ይመስለኛል$
ተመሳሳይ ነገር ከካሳንቺስ ቦሌ መድሀኔ አለም እና ቦሌ ድልድይ መንገድ ይሰተዋላል ቦሌ ድልድይ መኪና ይሰለፋል ካሳንቺስ ተሳፋሪ ይሰለፋልእውን እቺን ታክል መፍትሄ ማሰብ ከብዶ ነው?ወይስ የግብር ይውጣ ስለሚሰራ?

ተመሳሳዩን ሌሎች ተሳፋሪዎች በየአካባቢያቸው ሊያነሱት እንደሚችሉና እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ $
እባካችሁ ቢያንስ ያሉትን ታክሲዎች በአግባቡ ማሰማራት ቢቻል ባለንብረቶቹም መኪናዎቻችሁ ከሚቆሙ ሊሰሩ የሚችሉበትን የተሻለ አደረጃጀት ብትከተሉ$

ይቆየን!

No comments:

Post a Comment