Friday, April 19, 2013

መለስ ተኪ የሌለው መሪ አደለም




አንዳንዴ አድናቆታችንን እና ፍቅራችንን ስንገልጽ ከተፈጥሮ ጋር የሚጋጭ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሞት ጋር በተያያዘ የሚገለጹ ሀዘኖች አንዳንዴ መለስን የመሰለ ታላቅ መሪ ያፈራችውን ሀገር ከመለስም በፊት ታሪክ በተለያየ ስራቸው የሚያደንቃቸውን መሪዎች ያፈራችን አገር ካሁን ወዲህ ሌላ መለስን የሚመስል መሪ ማፍራት አትችልም የሚል መርገመት እንመርቃታለን።

መለስን ያፈራችው ምድር ብዙ መለሶችን ማፍራት ትችላለች። መለስ ራሳቸውም ቢሆኑ ሀገራቸው ባለብዙ መለሶች እንድትሆን እንጂ በላቀ አስተዋጾዋቸው የሚታወሱ መሪ እሳቸው ብቻ እንዲሆኑ የሚመኙ አይነት መሪም አልነበሩም። እንዲያውም ስለራሳቸውና ስለቤተሰቦቻቸው የሚያወጉበት ግዜ አልነበራቸውም። ቁምነገሩ ከመፍትሄው እንጂ መፍትሄ ለማምጣት የሚጥረውን ሰው ከማሞካሸቱ ስላልሆነ።

ፓርቲያቸው ኢህአዴግም ብዙ መለሶችን የማፍራት አጀንዳ እንዳለው በጠራራ ጸሀይ እያወጀ ባለበትና የመለስ ህልፈት ሚሊዮኖች ፈጥሯል በሚልበት የአንዳንድ አድናቂዎች የተዛባ አድናቆት መታረም አለበት። መለስ ለአይተኬነት የሰራ መለስ እሱን የመሰሉ ተደናቂ መሪዎች እንዳይፈሩ የሰራና ከተፈጥሮ ጋር መጋጨት የሚመርጥ ሰው አልነበረም።

እንዲያውም በተፈጠረው የተሻለ አጋጣሚ ተጠቅመው ከትላንቱ እጅጉኑ በላቀው ቴክኖሎጂ ታግዘው ከሳቸው የተሻለ አመራር እና አፈጻጸም ያላቸው የላቁ ብዙዎችን የመፍጠር ሀሳብ ያላቸው ናቸው። 

እንቅልፋቸውን ሰውተው የግል ህልሞቻቸውን ትተው ሀገራዊውን ህልም የሳቸውም ህልም አድርገው የተጉት ሀገር የተሻሉ ነገዎች እንዲኖሩዋት እንጂ እሳቸውን መድገም የማይችል ቀሽም ዘመን ለሀገራቸው ተመኝተው አደለም። እሳቸውን ካፈራቸው ሀምሳዎቹና ስልሳዎቹ አለያም ይበልጥ ከቀረጻቸው ሰባዎቹ የማይሻሉ ሁለት ሺ አምስቶች ሁለት ሺ አስሮችና ሀያዎች አስበው ነው የሚል ቅዠት የለኝም።


መለስን የመሰሉ መሪዎች በብዛት እንደልብ አይገኙም አሳማኝ ነው። በተለያዩ ዘርፎች የምናደንቃቸውን ታላላቅ ሰዎች የሚመስሉ ብዙዎች እንደሌሉ ይታወቃል። እነሱን የመሰሉ ታላላቅ ሰዎች ግን አይፈጠሩም ማለት አደለም። ታዲያ እንግዲያማ ሌጌሲ ወይም ትሩፋት ማለት ለመለስ የምናስነግርላቸው ውዳሴ እኮ አደለም። ፈጽመን የምንኖረው ሆነን የምንገልጠው መለስን የሚደግም ትጋት እንጂ ትረካ አደል። 

አንዳንዴ አድናቂዎች ከምናደንቀው ሰው ጋር የማይሄዱ እንዲያውም የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ ባንደርስ። መለስ ከትላንት የተሻለ ዛሬን ለመፍጠር ከዛሬዎቻችን የሚልቁ ነገዎችን ለማነጽ ይህንኑ ተከትሎ ከትላንቱ የላቁ ስብእናዎችና መሪዎች እንዲፈጠሩና ለዘመኑ የሚመጥን ተግባር እንዲፈጽሙ በዚያ የማያቋርጥ ሂደት አገር እንድትለወጥ እንጂ ላበረከቱት አስተዋጾ ሀውልት እንዲቆምላቸው አደለም የሰሩት።

ዛሬ ፍቅራቸውን ለመግለጽ አድናቂዎቻቸውና ወዳጆቻቸው መትጋታቸው አንድ ነገር ሆኖ ይህንንም ቢሆን የሚያደርጉት ለላቀ አስተዋጿቸው መታሰቢያነት እንጂ እሳቸውን የመሰለ ዳግም እንደማይፈጠር ለማመላከት አደለም።

አገር መለስን የሚመስሉ ትጉሀን እንዲፈጠሩ ትፈልጋለች አገር መለስን የመሰሉ ትጉሀንም ትፈጥራለች አገር መለስን የሚመስሉ መሪዎች በመፍጠሯም ዘመን በዛ ይጠቀማል። ከንቱው መለስን የመሰለ ጎበዝ መሪ አይፈጠርም የሚለው አተያይ ነው። ወዳጆቼ መሪ መርጦ ነው ራሱን ለሚበጀው አላማ የሚቀርጸው የሚያዘጋቸው። ተፈጥሮ ቀጥቅጣ የቀረጸችውና በገጸ በረከትነት ያበረከተችው መሪ የለም።

መሪዎች የምርጫቸው ውጤት እንጂ የተፈጥሮ ስሪቶች አደሉም። ተፈጥሮም ሰርታቸው እንኳ ቢሆን መደጋገሙን ታውቅበታለች። ብዙ መለሶች ለሀገሬ ብዙ መለሶች ለህዝቤ ይባላል እንጂ ሟርት ጥሩ አደለም።

ባለቤቱ በቃሉ የማይተካው የማያልፈው ትግልና አታጋይ ድርጅት እንጂ የማይተካ የሚባል ግለሰብ የለም ብሏል። ቋጨሁ።

No comments:

Post a Comment