Sunday, April 21, 2013

ደሀውን ያልጠቀመ እድገት?! ክፍል 1


ማስተዋል ደሳለው በፌስቡክ ፔጁ የሀገራችን እድገት የኑሮውድነቱን እንዳላቃለለና ለደሀው ያመጣው የረባ ለውጥ ስላለመኖሩ ወቅሷል$ ያነሳው ገንቢ ክርክር ነው ብዬ ስላመንኩ እድገቱ ሰብአዊ ልማት እያመጣ ያለና እና ደሀውን እየጠቀመ ስለመሆኑ ማመላከት ፈልጌ ነው መልስ ፈጻፍ የመረጥኩት$ ሀሳቤን በሁለት ክፍል አቀርባለሁ የመጀመርያው እነሆ

ሲጀመር በደሀውና በሀብታሙ መሀከል ያለው ምጣኔ በአለም የተሻለ ምጣኔ አላት ከሚባልላትም ከቻይና የተሻለ የሚባል ነው$ የቻይና ምጣኔ 0 ነጥብ 38 ሲሆን የሀገራችን ደግሞ 0 ነጥብ 34 እንደሆነ በቅርብ የወጣ የዩኤንዲፒ መረጃ ያመለክታል$ የኢትዮዽያ ማደግ አለማደግ አነጋጋሪ የሆነባቸውን ወቅቶች አለፈናል ተመስገን$ አሁን ያለው ጭቅጭቅ እድገቱ እውነት 11 በመቶ ነው ወይስ ከዚያ በታች እና እድገቱ እነማንን እየጠቀመ ነው የሚለው ነው$

ሀገራችን እድገት እድገት እያስመዘገበች መሆኑ የሚያከራክር አደለም$ ሆኖም ግን በጅምር አካባቢ ምርቱ ሲጨምር አርሶአደሩ በመንገድ እና በትራንስፖርት እጦት ምርቱ ዋጋ ሳያወጣ የቀረበት$ በሌላ ግዜ ደግሞ ድርቅ በሚፈጥረው የምግብ እጥረት ለርሀብ የተዳረገባቸው ግዜዎች ነበሩ$ ኢህአዴግም ወጥ የሆኑ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፍ እድገት ማስፈጸምያ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቀርጾ ሀገራዊ ልማትና እድገቱን ያልመራበት የጅምር ወቅቶች ነበሩ$

በኢህአዴግ ደረጃ ታምኖባቸው በውይይት ዳብረው የኢኮኖሚና ማህበራዊ መመርያ የሆኑ ፖሊሲዎች መፈጸም ከጀመሩበት 1995 2005 ዓም ሀገሪቱ ማስመዝገብ የቻለችው ለውጥ በርግጥም አስደሳችና ተስፋ ሰጪ ነው$

እንደ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚንስትርና እንደ አለም ባንክ አይኤምኤፍ እና ዩኤን ያሉ ተቋማት የሀገራችን በጀት ደሀ ተኮርና ድህነትን ለመቀነስ የተነጣጠረ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ይሰጣሉ$ ቁምነገሩ ይሄ ደሀ ተኮር የተባለው አበጃጀትና አፈጻጸም በተግባር የየትኞቹን ድሆች ህይወት ቀይሯል ነው$

ድህነትን ለመቅረፍ ያለመ በጀት
በአፍሪካ ደረጃ በማንኛውም መመዘኛ ሲታይ የሚያስመሰግን ደሀውን የህብረተሰብ ክፍል ለመለወጥ የሚያልም አበጃጀት ነው የምንከተለው$ 70 በመቶ በላይ በጀት ድህነትን ለመቅረፍ በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነው$ የአንደኛ እና ሁለተኛ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባታ ዋና ስራው ያደረገ በጀት ነው$ በርግጥ ይሄ ምግብም ልብስም መጠለያም አይሆንም በየትኛውም መስፈርት የዛሬውን ችግር የመቅረፍ ፋይዳ የለውም$

ያን የመሰለውን ሀብት የሚፈጥር አቅም የሚገነባው በትምህርት የተገነባ ማህበረሰብ ያለን እንደሆነ መሆኑ ግን አያጠያይቅም$ በዚያ ሲመዘን ገጠሬውን ደሀውን ለዚያውም ከሰማንያ በመቶ በላዩን ኢትዮዽያዊ የሚቀይር ዘላቂ ስራ በማከናወን ረገድ አጋጥሞታል ከሚባለው የትምህርት ጥራትም ችግር ጋር ቢሆን የላቀ ውጤት እያስገኘ ያለ ስራ ነው$ እናም ድህነትን በመቅረፍ ረገድ መንገድ መጥረጊያ የሆነውን የብርሀን ያክል የሚቆጠረውን መሳርያ ትምህርትን እያስታጠቀ ያለ በጀትና አፈጻጸም በመሆኑ በርግጥም ድህነትን በመቅረፍ ረገድ አመርቂ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው$

ይሄን ድምዳሜ በማንኛውም የዩኤን ተቋማት አለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ በኩል የሚወጡ መረጃዎችም ያመላክታሉ$ ይሄን ማለት ያስፈለገኝ የመንግስት ተቋማትን እና ያንን መረጃ የሚቀበሉ አካላት የኢህአዴግን የተጋነነ መረጃ ያንቆረቁራሉ ተብሎ ስለሚታማ ነው$ በኔ እምነት እነዚህ የመንግስት ተቋማት ላለፉት አስርት አመታት ሲያወጧቸው የነበሩ መረጃዎች ትክክል መሆናቸውን በቅርቡ አለም ባንክ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በሚመለከት ያወጣው የአስር አመት ሪፖርት ያመላክታል$

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የተሿሚዎቹን ቤት እና የመዝናኛ ወጪ ለመሸፈን በሚሯሯጡበት እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገሮች ለመሪዎቻቸው በሚገርም መልኩ እስከ አስር ፕሬዚዴንሻል አውሮፕላን በሚያቀርቡበት በጀት ቅርጫ በሚመስለበት አህጉር በጀቱን በተጨባጭ ድህነትን ሊፈቱ በሚችሉ ዘላቂ የልማት አቅሞች ላይ በማዋል የምትታወቅ ሀገር ኢትዮዽያ ናት$ ይሄ ድምዳሜ ግን ችግሩን መፍታት በሚያስችል አስተማማኝ መንገድ ላይ ስለመሆናችን እንጂ ችግሮች ተፈተው ስለማለቃቸው የሚያሳይ አደለም$

የገጠሩን ታዳጊና ወጣት አይን የሚከፍቱ የማንበብ እና የመጻፍ ክህሎቶችና የተለያዩ የአካባቢ ሳይንስ እውቀቶች የገጠሩን  ማህበረሰብ ከመሬት የመንቀልና በተለያዩ ክህሎቶች በማጎልበት በንግድ እና መሰል ዘርፎች የማሰማራት አቅማቸው ቀላል አይደለም$ ጤናው የተጠበቀለት አብዛኛው ገጠሬም በአመዛኙ በግብርና ኤጀንቶቹ ታግዞ ስራው ላይ የሚያሳልፍ ከሆነ ባለፉት አመታት ያየነው ውጤታማነት ተጠናክሮ የማይቀጥልበት እድል የለም$

ግብርና
ባለፉት አመታት ከአስር በመቶ በላይ እድገት እያሳየ የመጣው የግብርናው ዘርፍ ስኬት ሀገሪቱ እየለማች ስለመሆኑ የገጠሬው ሀገሬ ህይወትም እየተለወጠ ስለመሆኑ ማመላከቻ ነው$ ይሄው ዘርፍ በዚህ አመት እንዳስመዘገበ ከሚታወቀውና ሀገሪቱ እንዲህ አይነት የግብርና እድገት ተቀባይነት የለውም ብላ የተቆጨችበት እድገትም ቢሆን በአፍሪካ ደረጃ ለማሳካት ከተያዘው የስድስት በመቶ እድገት አንጻር ሲመዘን ከፍተኛ የሚባል ነው$ 6 ነጥብ 9 በመቶ ያሰመዘገበችው ሀገራችን ከስከዛሬው የዘርፉ እድገቷ የቀነሰ ቁጥር የመጣ ቢሆንም ቀነሰ የሚባለውም ቁጥር በአፍሪካ ደረጃ ከተያዘው እድገት አንጻር አበረታች ነው$

አንድ በአፍሪካ ደረጃ የግብርና ስኬትን ባለፉት አስር አመታት ምን እንደሚመስል የገመገመ የተጠያቂነት ወትዋች አለማቀፍ ዘመቻ ቡድን ኢትዮዽያ ለግብርናው ዘርፍ ወደ 16 በመቶ በጀት በመመደብ በአፍሪካ በዘርፉ ሻንፒዎን ስለመሆኗ ያትታል$ ከስድሰት በመቶ በላይ እድገትም እንዲገኝ የሚጠይቀውም መስፈርት በማሟላት ቀዳሚዋ አገር መሆኗንም ይመሰክራል$

83 በመቶው ሀገሬ ገጠሬ አርሶ አደር ወይም አርብቶአደር በሆነባት ሀገር ለማደግ ይሄ የህብረተሰብ ክፍል የተሰማራበትን ዘርፍ ማሳደግ የግድ ነው$ በአርሶ አደር አገር ከተሜን ይዞ የትም ድረስ መሄድ አይቻልም$ ቀላሉ የለማ 83 በመቶ 17 በመቶውን ሲቀይረው እንጂ የለማ 17 በመቶ 83 በመቶ የኮሰሰን ገጠሬ ልጎትት ሲል አደለም$ ስለሆነም አርሶ አደሩና አርብቶአደሩ እየተለወጠ ከሆነ አፍ ሞልቶ አገር እየተለወጠ ነው ማለት ይቻላል$

ይሄ ማለት ዘርፉ የተጋረጠበትን ዘመናዊ መሳሪያ የማዘጋጀት የማዳረስ የማስለመድ የምርት ለውጥ በተጨባጭ የማስመዝገብ እና ያንን በየደረጃው እየገመገሙ እያሻሻሉ መሄድ መካድ ማለት አደለም$ የእርሻ ስራውንም በሚቻልባቸው አካባቢዎች ከዝናብ ጥበቃ የማላቀቅ እና በመስኖ እንዲሰራ ማድረግ ሌላው ወሳኝ ስራ ነው$ ይሄ በሚቀጥሉት አመታት ተጠናክሮ ከቀጠለ የተሻሉ ውጤቶች ማየታችን አይቀርም$

የሆነ ሆኖ ህይወቱ እየተቀየረ ስላለ ነው ገጠሬው ቤቱን በቆርቆሮ እየሰራ ልብሱን እየቀረየ የቤት እቃዎች እየሸመተ ወጣ ወጣም እያለ የመዝናናት አዝማሚያም እየተስተዋለበት ያለው$

የቤት ግንባታና ዙሪያ መለስ የስራ እድሎች
ከቤቶች ልማት አንጻር በአዲስ አበባ ብቻ እንኳ የተገነቡ ወደ 140 የሚጠጉ ቤቶች የቤት ችግሩን ከመፍታት አንጻር ካለው ሚናም በላይ በዙርያው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አነስተኛ እና ጥቃቅን ድርጅቶችን አሰልጥኖ በማሰለፍ ብድር አገልግሎት በመስጠት እቃ በማቅረብ በከተማ አካባቢ ያለውን ሰፊ የስራ አጥነት ችግር በመፍታትም ረገድ ሁነኛ ሚና ተጫውቷል$

ልማቱ ለዜጎች ያስገኘው ጥቅም አለ ለማለት የግድ ሁሉም ማህበራዊ ችግር የቤት ችግር የኑሮ ውድነት መፈታት አለበት ማለት አደለም$ በማንኛውም ሚዛን በመቶ የሚቆጠሩ ቤቶች በአዲስ አበባ ደረጃ ማቅረብ ግዙፍ ስራ መሆኑ መካድ የለበትም$ ይሄው ግዙፍ ፕሮጀክት በሂደት በርካታ ኮንትራክተሮች ባለሞያዎች በዚሁ ዙርያ የተደራጁ የስራ ማህበሮች በመፍጠር ረገድ ግዙፍ ሚና ተጫውቷል$

ለድሀው እና መካከለኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል ያስገኘውም ውጤት የምር የሚያበረታታ ነው$ እነዚህን ስኬቶቹን ማንሳት በሂደቱ ያጋጠሙ እጥረቶችን መካድ ተደርጎ መታየት የለበትም$ የጥራት የመጓተት የእጣ እና ቤት ያላቸውን ሰዎች ከሌላቸው መለየት አለመቻሉ በዚህ ረገድ የሚታዩ መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብሎ ማንሳትም ይቻላል$

በመሆኑም እድገቱ ሲጀመር ሁሉንም ችግሮች ያስወግዳል ተብሎ የሚገመት ባይሆንም እንደዚያ መገመቱም ስህተት ቢሆንም እድገቱ ግን በርግጥም ዘላቂ የሀገሪቱን ጥቅም ሊያስጠብቅ በሚችልበትና ድህነትን ሊቀረፍ በሚችልበት አግባብ እየተከናወነ ስለመሆኑ መካካድ ተገቢ አይሆንም$

የድህነት ቅነሳ
ኢትዮዽያ ከዛሬ አስር አመት በፊት 38 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎች ነበሯት$ ባለፉት ዘጠኝና አስር አመታት በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚንስትርም ይሁን በአለም ባንክ ሪፖርት መሰረት ሀገራችን የ9 ነጥብ 1 በመቶ የድህነት ቅነሳ ማድረግ ችላለች$ ይሄ ማለት ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚጠጋ ቁጥር ያለው ሰው በእድገቱ ከድህነት ወለል በላይ ሆኗል$ እንደ መረጃዎቹ ሀገራችን የዋጋ ግሽበትን ባለ አንድ ዲጂት አድርጋ ተጉዛ ቢሆን ኖሮ ከድህነት የሚወጣው ህዝብ ቁጥር ከዚህም የላቀ መሆን ይችል ነበር$

ከዚሁ ጋር አያይዘን ብናየው ጥሩ የሚሆነው ከእጅ ወደአፍ በሆነ መልኩ የሚኖረው አርሶ አደር በተለይም ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በአመዛኙ ሁኔታው ወደ ርሀብ የሚቀየርበት ሁኔታ የነበረ መሆኑ ይታወቃል$ እንደ ቦረና እና ሶማሊያ አካባቢ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚሰሩት ትላልቅ ግድቦች እንደተጠበቁ ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ድርቆችን ተከትሎ የሚከሰተውን የምግብ እህል እጥረት መንግስት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት የሚጠቀምበት የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ሲከሰትም ችግሩን ለመቅረፍ የሚጠቀመው መንገድ ከእህል ክምችቱና የጥምረት ስራው ጭምር ስኬታማ በመሆኑ በሌሎች ተመሳሳይ ችግሩ ባለባቸው የምስራቅ አፍሪካና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለመተግበር ልምድ እየተቀመረ መሆኑን አውቃለሁ$

መረጃዎቹን ከአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት የዚህ አመት ጉብኝትና ከቅርብ ግዜው የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የርሀብ አደጋ ወቀት ኢትዮዽያ የነበራት የተሻለ አፈጻጸም በተለያዩ አለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችና በአውሮፓ ህብረት ተደናቂነት ያገኘ መሆኑን ማስታወስ ይቻላል$ ይሄ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን መሰደድ ምክንያት የነበረን ችግር በዚህ መልኩ ማንም ከአካባቢው ሳይፈናቀል ድርቁ ወደ ርሀብነት እንዳይሸጋገር ማድረግና ከራሳችን መጋዘን አውጥተን መመገብ መቻል ትልቅ ስኬት ነው$ በርግጥ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ በዚህ ረገድም ቢሆን ግዙፍ መሆኑ ባይካድም$ ምክንያቱም ከመጋዘን ያወጣነውን ምግብ የሚተካ እስከ ስድስት ወር ተጓጉዞ የሚደረስ የምግብ እህል እርዳታ ይሰጡናልና$

ርሀብን በዚህ መልኩ መቆጣጠር መቻልና አርአያ ተደርጎ ሊታይ በሚችልበት ገጽታው መምራት የእድገታችን ማሳያና በግብርና ሚኒስቴር በኩል የሚሰራው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ ሁነኛ ለውጥ እያሳየ ስለመሆኑ አያጠራጥርም$

No comments:

Post a Comment