Wednesday, December 5, 2012

የኛ አገር ፖለቲካ


እኔ እንደሚገባኝ ችግሮቻችንን መላእክት አይፈቱልንም፡፡ እኛው ላቁጠን፣ ፈግተን እና ዋተን የምናመጣው እንጂ እነ እገሌ ምነው ይህን አድርገውት ቢሆን ኖሮ በሚል ጠባቂነት አደለም፡፡ በአገራችን ችግር ካለ እኔና አንተም ችግር ከሚፈጥሩቱ ወይም ችግሩን ለመፍታት ከማይሰሩቱ ስለምንሆን ከመጠየቅ አንድንም፡፡ እየሞከርክም ከሆነ ችግሩ እስካልተፈታ ዛሬም ትተቻለህ፡፡ ለለዉጡም በጥረትህ ልክ ከሚመሰገኑት እኩል ትመሰገናለህ፡፡

በርግጥም የምትሳበው ለሀገርህ እንደሚጠቅም የምታምንበትን እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ሁሌም ያንተን ሀሳብ የማይጋሩ ግን ደግሞ ለሀገሬ የሚጠቅማት መንገድ ይህ ነው ብለው ያንተን በመሰለ ተቆረቁዋሪነት መንፈስ የሚተጉ ሌሎች እንደሚኖሩ እረዳለሁ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ የብዙሀን ፓርቲ ስብስብ የሚሆነውንም እኮ ለዚህ ነው፡፡

ያም ሆኖ የኛ አገር ፖለቲካ በጡዘት የተወጠረ ይመስላል፡፡ እንዲህ ያለውን ልዩነት እንደመድረኩ ባህሪ ወስዶ ሲያበቃ ባሻገር ያለው ባለ ልዩው አቁዋም ቡድንም ሀገሬን ይጠቅማል ብሎ የሚያምንበትን አቁዋም መያዙን መቀበል ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ሌቦች ሆዳሞች የሚል ቅፅል በመጨመር ራስን ልዩ የሀገር ተቆርቁዋሪ አድርጎ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን የአላማዉን ልዩነት ገምግሞ አይጠቅምም ብለን የምናምነው አቁዋም በህዘቡ ተቀባይነት እንዳያገኝ መስራት ተገቢና ትክክል ነው፡፡ ይህን ብሎ መስራት ግን መሰዳደብና መወራረድ ለመተያየት ሁሉ መጠላላት መድረስ ማለት አደለም፡፡ ፖለቲካችን ይህን የመሰለ ስክነት ይፈልግ ይመስለኛል፡፡

ተቆርቋሪነቱ አበረታች ነው፡፡ የራስን ተቆርቋሪነት ልዩ አድርጎ ማየትና ሌሎችን ማንኩዋሰስ ግን ጎጂ ልምድ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡  የራስን እቅድ የተሻለ መሆን ማስረዳትና የህዝብን የላቀ ድጋፍ ለማግኘት መትጋት ይቻላል፡፡ የራስን የመፈጸም አቅምና ልምድ ማጉላትና የህዝብን አመኔታ ለማግኘት መትጋት አግባብነት አለው፡፡

በዚህ ደረጃ መረዳቱ ያለው ሰው ዳር ቆሞ እነገሌ ያደረጉትን እና ያላደረጉትን እየጠቀሰ ማሄስ እንደሚችል እረዳለሁ፡፡ ሆኖም ትችትን እንደሁነኛ ሚና መቁጠር ግን ትንሹ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ይጠቅማል ብለን የምናነውን ጉዳይ በሚመስለን ፓርቲ ተቀላቅለን መትጋትና አስተዋጾ ማበርከት ስንችል ከመአዱ እንዳባረሩት ሁሉ ራቅ ብሎ ማማረር በጎው ሚናችን ነው የሚል የዋህነት የለኝም፡፡ እናስ መቆርቆራችንን በተግባር መግለጽ አንችል ይሆን

ተወዳድሮ ያሸነፈን በአቁዋሙ የተለየን ፓርቲ የምንሻውን እንዲፈጽም መመኘት ሞኝነት ይመስለኛል፡፡ አሸናፊ ፓርቲ የተወዳደረበትን አቁዋሙን ከመፈጸም ወደሁዋላ  አይልም፡፡ ይህ እንደማይበጅ ካመን ያዋጣል የምንለውን አቁዋም ህዝብ እንዲቀበለን በማድረግ ገዢ ፓርቲን መርታትና በእምነትና አቁዋማችን ልክ መምራት እንጂ ዳር ቆሞ ማላዘን ከንቱነት ይመስላል፡፡ ለኔ ዳር ሆኖ ከሚወተውት ገብቶበት ለመስራት ሲሞክር የሚሳሳት ይሻለኛል፡፡ እናስ ትግሉን ብንቀላቀለው፡፡

ወደድንም ጠላንም አሸናፊ ፓርቲ ያመነበትን ይሰራል መሪያችንም ሆኖ ይቆያል፡፡ ሁኔታዉ የማያምር እንደሆነ ካመን የሚያምረንን ለማምጣት እየሰራን ለግዜው የሚመሩንን አክብረን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ መቃወማችን እንዳለ ሆኖ የሀገሬ መሪ ነዉ፡ አሸንፎ ነው ቦታዉን የያዘው ብሎ ማመን ይጠይቃል፡፡ ሁሌ እኛ ካላሸነፍን ተጭበርብሩዋል የሚለው ልቅሶ ሰሚ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡

ሲደመደም ዳር ቆሞ የመቦጨቅና የመተቸት ማበረታቻ እና ክብር ያለን አይመስለኝም፡፡ ለመፍትሄው ከሚተጉት መሀል መሆን ይመረጣል- በርግጥም እንደምንለው አገራችንን የምንወድ ከሆነ፡፡ ጥሩ ሚና ሲኖረን መልካም ፖለቲካ ሊኖረን ደካማ አስተዋጾ ሲኖረን ደግሞ ሽባ ፖለቲካ እንደሚኖረን አይጠረጠርም፡፡ ፖለቲካው እማያምረን ከሆነ አስተዋጾዋችንም አለማመሩን ማወቅ ትልቅ ስሌት የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡//

No comments:

Post a Comment